Sunday, 12 September 2021 20:59

ጦሳችንን ይዞ ጥርግ ይበል!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንኳን ከዘመን ዘመን አሸጋገራችሁ፡፡
እንቁጣጣሽ እንኳን መጣሽ
በአበቦች መሀል እንምነሽነሽ
እየተባለ የሚዜምበት ዘመን ይሁንልንማ!
ነገ የአዲስ ዓመት የመጀመሪያ ቀን ነው። የአዲስ ዓመት ብቻ ሳይሆን የአዲስ ዘመንም መጀመሪያ ያድርግልን! የሰላም፣ የደስታና የፍስሀ ዘመን የመጀመሪያ ቀንም ያድርግልን! በእኛው በራሳችን ምክንያት የተዳከሙብን፣ አቅም ያጡብን፣ ሊጠፉ ጭል፣ ጭል የሚሉብንና ለይቶላቸው የተሸረሸሩብን መልካም እሴቶቻችን፣ በእኛ ቸልተኝነት ወይም የተዘዋዋሪ ይሁንታ ሌሎች እንዲሸረሸሩ ያደረጉብን መልካም እሴቶቻችን እንደገና ከቀድሞው በተሻለ አብበውና ፈክተው የሚመለሱበት ዘመን ያድርግልን፡፡ በማንም ሳይሆን በእኛው በራሳችን፡፡
“እውነት ይህ ሁሉ መከራ፣ ይህ ሁሉ ስቃይ የነበረበት ዓመት አልፈን ነው እዚህ የደረስነው?” እየተባባልን የምንደነቅበት ታሪክና ታሪክ ብቻ ሆኖ እንዲቀር ነው የምንመኘው፡፡ ተደንቀንም ያሳለፍነውን አይነት ዘመን ዳግም እንዳይመለስ ጠብበን ሳይሆን ሰፍተን ተመካክረን፣ በአስተማማኝ በሩን የምንከረችምበት ዘመን እንዲሆን ነው የምንመኘው፡፡
ጦሳችንን ይዞ ጥርግ ይበልና!
ከብረው ይቆዩኝ ከብረው
በዓመት ወንድ ልጅ ወልደው
ሠላሳ ጥጆች አርደው
ከብረው ይቆዩኝ ከብረው
ይባል የነበረው አሪፍ ምኞት ነበር፣ ነውም። የሆነ ቦታ ላይ ዘመን ሀዲድ ሳተብንና፣ ወይም እኛ ራሳችን አሳትነውና፣ ወይንም ‘እኛ የውስጠኞቹ ከእነሱ የውጨኞቹ’ ጋር በተዘዋዋሪም ቢሆን አብረን ዘምነን ሀዲዱን አሳትነውና እውነተኞች፣ ከምንም ጋር ያልተሳሰሩ የልብ የሆኑ የመልካም ምኞት መግለጫዎች የሚናፈቁ ሆኑ፡፡
ክፋት ገንኖ፣ “ምን የቆረጠው ነው ጫፌን የሚነካኝ፣” በሚል ተንሰራፍቶብን የነበረበት ዓመት ነው፡፡ ድንገት የሆነ መሰናክል ያደናቀፈውን እንደ ቀድሞው የመተሳሰብ ባህላችን “እኔን ይድፋኝ!” ብለን ደገፍ ከማድረግ ይልቅ “እያየህ አትሄድም እንዴ፣ ይድፋህ!” ስንል የከረምንበት ዓመት ነበር። በፈጣሪ ቤት ሄደን እኮ “እሱን በአጭር አስቀርተህ ካላሳየኸኝማ!” “እሷን እራቁቷን መንገድ ለመንገድ ካላንከራተትክልኝማ!” አይነት ባህሪይ ይዘን ነው የከረምነው፡፡ ‘አዋቂ’ የሚባሉት ዘንድ እየሄድን ለራሳችን “እንትን ስጠኝ፤ እንትን አብዛልኝ፣” ከማለት ይልቅ የሌላውን፣ አርፎ ቤቱ የተቀመጠውን እኛ ላይ አይደለም እጁን ሊያነሳ በክፉ ዓይን አይቶን የማያውቀውን “ሹካ ማንኪያ ሳትቀር ንሳው!” ማንም ዘንድ ሳትደርስ ቤተሰቧን ለመንከባከብ የምትዳክረውን “ሙልጭ አድርገህ ባዶዋን አስቀራት!” አይነት ባህሪይ ይዘን የከረምንበት ዓመት እኮ ነው፡፡
ጦሳችንን ይዞ ጥርግ ይበልና!
አሁንም 2013 ጦሳችንን ይዞ ጥርግ ይበል፣ ለትውስታ እንኳን እንጥፍጣፊውን አያስቀረው። የዘንድሮው አይነት ዓመት መቼም መቼም ቢሆን በዚች ሀገር ላይ ደግሞ እንዳይመጣ ያድርግልን፡፡
በቀድሞ ጊዜ ቃል የምንገባባቸው ነገሮች...አሉ አይደል... “በአዲሱ ዓመት...
...ሲጋራ ማጤስ አቆማለሁ፡፡
...መጠጥ እርም ብዬ እተዋለሁ፡፡
...ከአጓጉል ሰዎች ጋር መግጠሜን አቆማለሁ።
የመሳሰሉት ነገሮች ነበሩ፡፡ አሁን ዘመን ተለወጠና ከግል ድክመቶቻችን ይልቅ የሀገርና ህዝብ ጉዳይ ቀድመዋል፡፡ መሆንም ያለበት እንዲሁ ነው፣ መቀጠልም ያለበት በዚህ መልኩ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ጣታችንን በሌላው ላይ ብቻ መቀሰራችንን አቁመን ወደ ራሳችንም የመጠቆሙ ድፍረት ሊኖረን ይገባል። ምክንያቱም አንዱ ግዙፍ ችግራችን ሁላችንም ሀዋርያ ሆንንና ቡራኬውም፣ እርግማኑም ድብልቅልቁ መውጣቱ ነው፡፡
ሁላችንም ሊያስብል በሚባል ደረጃ ለድክመታችን፣ ለጥፋታችን፣ ጀርባችንን አዙረን ሁሉንም ነገር ሌሎች ላይ ስናላክክ የነበርንበት ዓመት ነው፡፡ እኛ ሌሎችን ስንተች ‘ትክክል’ ሆነን፣ ሌሎች እኛን ሲተቹን ‘ስህተት’ የሆነበት ዓመት! “እኔ ነኝ ጥፋተኛ፣ በእኔ ምክንያት ነው የተበላሸው፣” ማለት ራስ ላይ የሆነ መሳሪያ እንደ መደገን እየተቆጠረ በዳይ ብሩክ፣ ተበዳይ እርጉም የነበረበት ዓመት!
ጦሳችንን ይዞ ጥርግ ይበልና!
የምር ግን ስሙኝማ… በአዲሱ ዓመት “የበደልኳችሁ ሁሉ ይቅር በሉኝ!” የሚል ሰው እውነትን ለማየት ድፍረቱ ያለው ሰው ነው ማለት ነው፡፡ የምር ግን... ያጎደልነውን፣ ያበላሸነውን እያወቅን፤ ሰዉ ሁሉም እያወቀብን “ሆነ ብዬ ያደረግሁት ስላልሆነ ይቅርታ አድርጉልኝ፣” ማለት ማንን ጎዳ! እኛ ይቅርታ መጠየቅ ሳንችልበት እኮ ነው “ሌሎች ይቅርታ አልጠየቁንም፣” ብለን ግንባራችንን የምንአለሽ ተራ በረባሶ የምናስመስለው፡፡ ከልባችን...
ይቅርታ እለምናለሁ፣ ጥፋቴን አውቄያለሁ
የምንልበት ዘመንን ያፍጥንልንማ! የችግሮች መፍትሄ የመጀመሪያው እርምጃ ይሆናልና!
ማሪኝ ብዬሻለሁ እሞትብሻለሁ
ማለት ማንን ከዙፋን አወረደ? ማጥፋቱን አውቋል፣ እንዳስቀየማት ያውቃል። በመጨረሻም ማሪኝ አላት፡፡ እንዲህ ማለት የሚችሉት በራሳቸው የሚተማመኑ ናቸው።  ለተሠራ መልካም ያልሆነ ሥራ ምህረት መጠየቅ ታላቅነት እንጂ ራስን የማሳነስ ምልክት አለመሆኑ የገባቸው ናቸው፡፡ እንዲህ አይነት ሰዎችን ያብዛልንማ! አለን የእኛ ቢጤዎች “ይቅር በለኝ!” ማለት “ማሪኝ!” ማለት እንኳን ልንቀመጥበት በአጠገቡ እንኳን አልፈን ከማናውቀው ዙፋን ላይ መውረድ የሚመስለን! ልቡናውን ይስጠን፡፡
ጥፋት እንዳለብኝ ይቅርታ
ንገረኝ ምንድነው ቅሬታ
ማለት በራስ የመተማመን፣ የትልቅ አስተሳሰብ ጥግ ነው፡፡
ነገሬ ብላችሁ እንደሁ አዲሰ ዓመት ሲመጣ በግለሰብ ደረጃ ብዙዎቻችን የምንናገረው ስለማቆም፣ ስለመተው፣ ስለማቋረጥ ምናምን ነገር ነው እንጂ የሆነ ነገር ስለመጀመር አይደለም።
“ሲጋራ አቆማለሁ፣” ነው እንጂ “ሲጋራ አቁሜ ሌሎችም እንደ እኔ እርግፍ አድርገው እንዲተዉ የበኩሌን እሞክራለሁ” አይደለም።
በነገራችን ላይ ብዙዎቻችን “ሀሜት የሚባል ነገር ያለበት ቦታ ሁለተኛ ዝር አልላትም፣” ማለት ሳያስፈልገን አይቀርም፡፡ ምናልባት ነገሬ ሳንለው እኮ በተለይም በማህበራዊ ሚዲያ በመሳሰሉት መድረኮች ‘ሀሜት ስርጭቱ’ ውስጥ ዘው ብለን ገብተንበታል፡፡ ሀሜቱን መጀመሪያ የሚናገረው ብቻ ሳይሆን፣ ያንን ሰምተን “እከሌ እኮ እንዲህ አለ፣” ብለን የምናስተላልፈውም እኩል ጥፋተኞች ነን። ያ ሰው የነገረን ሀሜት መሆኑን እያወቅን እንደገና ማራባቱ ለምን አስፈለገ!
“አንድ ሊትር ዘይት ስምንት መቶ ብር ሊገባ ነው አሉ!” እንላለን፡፡ “ከየት ያገኘኸው ኢንፎርሜሽን ነው?” ብሎ ጣጣ የለም፡፡ እንደዛ ብሎ የሚጠይቅ ከመጣም መልሱ አንድ ነው… “ሰው ነገረኝ” ነው የሚባለው። እዛም ብትሄዱ፣ ወዲያም ብትሄዱ “ሰው ነገረኝ፣” ነው፡፡ እኔ የምለው ይህ “ሰው” የሚባለው  ሰውዬ…አለ አይደል…እየዞረ ለሁሉም የሚነግረው አይደክመውም እንዴ! ማነው ቀለብ የሚቆርጥለት? ቂ…ቂ…ቂ…
ክረምት አልፎ በጋ መስከረም ሲጠባ
አሮጌው ዓመት አልፎ አዲሱ ሲገባ
በአበቦች መአዛ ረክቷል ልባችሁ
ህዝቦች ሁሉ በጣም እንኳን ደስ አላችሁ
ተብሎ ተዚሟል፡፡ እንዲህ ሁላችንም በትንሹም በትልቁም፣ በቁም ነገሩም በፌዙም...ካባ ለካባ መተያየታችን ቀርቶ ከልባችን “ህዝቦች ሁሉ በጣም እንኳን ደስ አላችሁ” የምናባባልበት ዘመን ፈጥኖ ይምጣልን!
የወጣው ዓመት ጦሳችንን ይዞ ጥርግ ይበልልንማ!
መልካም በዓል!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1214 times