Print this page
Saturday, 04 September 2021 17:40

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ጎባጣው ትዳሬ
                          በእውቀቱ ስዩም


           በየሳምንቱ ቅዳሜ አንድ መርህ አለኝ፤ ያገርቤትም ሆነ የውጭ አገር ፖለቲካ ዜና እጦማለሁ፤ ኪነጥበብና ማህበራዊ ጉዳይ ላይ እጣድና ነፍሴን አለመልማታለሁ፤ በዚህ መሰረት፥ ቅድም ዩቲዩብ ላይ ስርመሰመስ ቆየሁ፡፡
በቀደም አንድ የሞሮኮ ዜጋ የሆነ ዘፋኝ “ሊጋባው በየነ” የሚለውን ዘፈን በራሱ ቃና ዘፍኖ አስደምሞኝ ነበር ፤ ዛሬ ደግሞ ሸገር ውስጥ በስደተኝነት የሚኖር ሶርያዊ ዘፋኝ “ለዚህ ለዚህማ ምናለኝ አገሬ“ የሚለውን የጌቴ አንላይን ዘፈን ዘፍኖ አስለቀሰኝ::
ወደ ፌስቡክ ተመለስኩ፤ ባለፈው አንዱ “ላጤ” የሚለውን ግሩፕ እንድቀላቀል መጥርያ ልኮልኝ ነበር፤ ያለሁበትን ተጨባጭ ሁኔታ ለመሰለል ፈልጎ ይመስለኛል፤ እኔም ግሩፑን ቀስ ብየ በለሆሳስ እየተራመድኩ ሰለልኩት፤ ፍቅር የተራቡ "ሆርኒ” ወጣቶች የተደራጁበት ቡድን መሆኑን ደረስኩበት፤ ብዙም ሳይቆይ አንዲት ወይዘሮ "በትዳራችን ጉዳይ እንመካከር" የሚል ግሩፕ ላይ እንድሳተፍ መጥርያ ሰደደችልኝ፤ ይሄ ግሩፕ የመጨረሻ ተመቸኝ፤ የመጀመርያም ተመቸኝ። አብዛኞቹ የግሩፑ አባላት፥ የፍቅር ታሪካቸውን ተርከው፤ በትዳራቸው ላይ የገጠማቸውን ችግር ዘርዝረው፥ ካንባቢ ምክርና መፍትሄ ያማትራሉ፤ እንሆ እኔም ተሞክሮየን ለማካፈል ወሰንኩ፥
በውቄ እባላለሁ፤ ከባለቤቴ ጋራ የተገናኘነው ባጋጣሚ ነው፤ በጊዜው እሷ ሚስ ኢትዯጵያ ተብላ በቁንጅና ስትመረጥ እኔ አወዳዳሪው ነበርኩ:: የመጀመርያዎቹ ሀያ አመታት የትዳር ቆይታችን ጎረቤት የሚያስቀና ነበር:: ከቢሮ ስመጣ በደስታ በፈገግታና በውዝዋዜ ትቀበለኛለች፤ ኮቴን አውልቃ ወደ ላውንደሪው አፍ እየጨመረች “ምሳ እስኪደርስ፤ ክትፎ በቆጮ እየቀማመስክ ቆይ" ትለኛለች:: ከምሳ በሁዋላ ሶፋው ሳፋ እሲከመስል ድረስ ፍቅር እንሰራለን፤
ብዙም ሳይቆይ ጸነሰች፤ ከዘጠኝ ወራት ላልበለጠ ጊዜ በርግዝና ቆየች:: ያለ ብዙ ምጥ ወንድ ልጅ ተገላገለች፤ ልጃችንም ያለ ብዙ ለቅሶ ተገረዘ! ልጃችን በተወለደ በአንድ አመቱ ዶንኪቲዩብ ላይ እየቀረበ ለኢትዮጵያ ህዝብ ጠቃሚ ምክር መለገስ እና አቅጣጫ ማስቀመጥ ጀመረ:: ሰባት አመት ሲሞላው ካሮጌ ቅጥቅጥ ሚኒባስ ሂሊኮፍተር ሰራ:: አሁን ካዲስ አበባ ብሾፍቱ ራይድ እየሰራበት ይገኛል::
ከጥቂት ጊዜ በሁዋላ ባለቤቴ ጸባይዋ መቀየር ጀመረ:: የገቢ ምንጯና ለኔ ያላት ፍቅር በፍጥነት እየጨመረ ሄደ፤ ለልደቴ ፍልውሃ ያለውን ፓርክ ገዝታ በስጦታ አበረከተችልኝ::
በዚህ አይነት ሁሉን የሚያስቀና ትዳር ውስጥ እየኖርን እጅግ የሚያሳዝን ነገር ተከሰተ፤ ሄቲ ውስጥ የመሬት መንቀጥቀጥ ደረሰ ! ታሊባን አፍጋኒስታንን መልሶ ተቆጣጠረ፤ ይህ ግን በፍቅራችን ላይ የፈጠረው አሉታዊ ተጽኖ አልነበረውም::
አንባቢ ሆይ !! ትዳራችን ፈረሰ የሚለውን ለመስማት፥ ምክርና ከንፈር መጠጣ ለማዋጣት ሰፍ ብለህ እየጠበቅህ ነውን? በቃ ሼም የለህም? ለምን የሟርተኞችና የክፉ ታሪክ ናፋቂዎች ግሩፕ አታቋቁምም?


Read 1585 times
Administrator

Latest from Administrator