Monday, 06 September 2021 00:00

የሽግግር ምልክት፣ ሽግሽግ ነው።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

 ለክፉም ለደጉም ነው-ነገሩ። ሽግሽግ፣ የሽግግር ሁሉ ምልክት ነው - ለስኬትም ለውድቀትም፣ ለመደላደልም ለመፈናቀልም፣ ለስርዓትም ለስርዓት አልበኝነትም።
ጥቃቅኗን ሽግሽግ ልብ ካላልናት፣ እርምጃችን ወደ ከፍታ ይሁን ወደ ዝቅታ፣ ክፉውንና ደጉን መለየት ይሳነናል። መልካም ሽግግር ያመልጠናል። መጥፎ ሽግግር፣ ይገጥመናል። ዱብዳ ይሆንብናል።
ምልክቶቹን ካወቅን ግን ድንገተኛ አይሆንብንም። ሳይረፍድብን ለማምለጥ፣ ቀድመን ለመጠንቀቅ ጊዜ ይኖረናል ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?
አሳፋሪ የነበሩ አባባሎችና ንግግሮች፣ እንደዋዛ መወራትና መደመጥ በጀመሩ ጊዜ፣
የሚስቀወቅሱና የሚያስቀጡ ተግባራት፣ እንደዘበት መታየትና መደረግ በጀመሩ ጊዜ፣
አስጸያፊ ባህሪዎችና ወራዳ ዝንባሌዎች፣ ያለተግሳጽ አደባባይ መውጣት በጀመሩ ጊዜ፣… ተጠንቀቁ። የመጥፎ ሽግግር ምልክቶች ናቸው።
መልካም የአዝመራ ሲሳይ የሚመጣውም ቀስ በቀስ  በሽግሽግ ነው - ጊዜውን ጠብቆ። ተዘርቶና  ለምልሞ፣ አብቦና አፍርቶ ነው ለአዝመራ የሚደርሰው። ደረጃ በደረጃ አድጎ ነው - ወደ ጎተራ የሚሸጋገረው።
የስራ ስኬትም ሆነ የአገር ብልፅግና፣ የእህል አዝመራም ሆነ የባሕል ስልጣኔ፣ እውን የሚሆነው፣ በዘፈቀደ ወይም በድንገት አይደለም። በትንሽ በትንሹ እየተራመደ፣ ወደተቃና መንገድም እየተስተካከለ፣ ከረዥም ጉዞ በኋላ ነው፤ ገዝፎና ደምቆ ለመታየት የሚበቃው። በጥቃቅን ሽግሽግ አልፎ ነው፣ የእመርታ ሽግግር ላይ የሚደርሰው።
መልካም ለውጥ እንደ ዓመት በዓል ነው። እያንዳንዷን እለት ልብ ላንላት እንችላለን። ነገር ግን፣ በእለት ተእለት፣ በስንዝር በስንዝር ሽግሽግ ነው፣ ትልቅ ሽግግር የሚፈጠረው። እለታት ተቆጥረው፣ ወራትም ተከታትለው፣ የዓመት ዑደት ይሟላል። የአዲስ ዓመት መሸጋገሪያ በዓል ይመጣል - በዓውደ ዓመት።
የዝንባሌና የባሕል አዳዲስ ለውጦች፣ ለየብቻ በተናጠል ስናያቸው፣ ክብደት የሌላቸው ጥቃቅን ለውጦች ሊመስሉ ይችላሉ። እንዲያውም፣ ልብ አንላቸውም። ልብ ብንላቸው እንኳ፣ እንደ ቁምነገር አንቆጥራቸውም። ነገር ግን፣ ወደ ከባድ ሽግግር የሚያደርሱ ምልክቶች ናቸው። ለክፉም ለደጉም፣ የድንበር ሽግሽግ ናቸውና።
የድንበር ሽገግሽጎች- በዝምታ እያዘናጉ መስመርን ያሻግራሉ።
አነሰም በዛ፣ የስነ-ምግባርና የባህል፣ የህግና የስርዓት ድንበሮች፣ ሁሌም ይኖራሉ። እውነትና አሉባልታ፣ ግብረ-ገብና ጋጠ-ወጥ፣ ጥሩን መጥፎ፣ ጨዋና ባለጌ፣ በጎና ክፉ፣ ሥርዓት አዋቂና ሥርዓት አልበኛ፣ ሕግ አክባሪና ሕገወጥ፣ ግብይትና ዝርፊያ፣ ሰላማዊና አመፀኛ፣ ንፁህና ወንጀለኛ፣… የሚሉ ፈርጆችን ተመልከቱ። የንግግር፣ የተግባርና የባህርይ ድንበሮች ናቸው - “የኑሮ መርሆችና ልማዶች” ልንላቸው እንችላለን።
የኑሮ መርሆችና ልማዶች (ወይም ድንበሮች)፣ በቅጡ የተስተካከሉ፣ የጠሩና የጠነከሩ ጊዜ፤ እርስበርስ እየተደጋገፉ፣ በውህደት፣ ብሩህ የህይወት መንገድ ይሆናሉ።
የኑሮ መርሆችና ልማዶች (ወይም ድንበሮች)፣ በዘፈቀደ የተዛቡ፣ የደፈረሱና የመነመኑ ጊዜ፣ እርስበርስ እየተጣረሱ፣ ወደ ጨለማ የጥፋት እንጦሮጦስ የሚወስዱ ይሆናሉ።
የመልካም ባሕል ጥሩነቱ፣ የክፉ ባህል መጥፎነቱ፣…. በአጭር ጊዜና በቀላሉ የማይለወጥ መሆኑ ነው። የአገር ባሕል፣…. የእልፍ ነገሮች ድምር፣ የረዥም ጊዜ ውቅር ነው። እንዲያም ሆኖ፣ ጨርሶ አይለወጥም ማለት አይደለም። ቋሚና ዘላለማዊ አይደለም። እንዲሁ የሚተማመኑበት መሪ ወይም የማይጋፉት ገዢ አይደለም - ባሕል። ይበላሻል፤ ይሻሻላል።
ብሩህ የህይወት መንገድ፣ ካላከበሩትና ካላበለጸጉት፣ ቆሞ አይጠብቅም። ከተዘናጉ ስንዝር በስንዝር እየተንሸራተተ እየራቀ ያመልጣል፤ የህይወት መንገድ ቀስ በቀስ ይጨልማል - ወደ ጥፋት ወደ እጦሮጦስ ይሻገራል።
ጨለማ የጥፋት ቁልቁለትም፣ ከነቁበትና ከጣሩበት፣ ዘላለም እያዳፋ አይዘልቅም። በእውቀትና በትጋት ተቋቋመው ካስተካከሉት፣ ወደ ብርሃን ሊሸጋገር ይችላል - ወደ ሕይወት መንገድ።
ይሄ እውነት ነው። ግን፣ እንደ ንግግር አይቀልም። የልማትና የጥፋት ባሕላዊ ሽግግር፣ “ይሄውና እመርታ፣ ይሄውና ሽግግር” ብለው እዚያው በዚያው ማየትና ማሳየት የሚችሉት ነገር አይደለም።
እንደ ጉርምስና እንደ እርጅና አስቡት። “እዩዋቸው ሲጎረምሱ፣ እዩዋቸው ሲያረጁ” ብሎ ማየትም ማሳየትም አይቻልም። የእለት ተእለት አካላዊ ለውጦችን ለይቶ ማስተዋል ይከብዳል። የወራት የዓመታት ባለብዙ ገፅታ ሂደት ናቸው - የጉርምስናና የእርጅና ሽግግሮች።
የውድቀትና የትንሳኤ፣ የስልጣኔና የኋላቀርነት ሽግግር ደግሞ፣… ከጉርምስናና ከእርጅና ሽግግር የላቀ፣ የረዥም ጊዜ ፈርጀ ብዙ ሂደት ነው - ለግንዛቤ የሚከብድ።
እዚህ ላይም ነው፤ የግንዛቤና የትንታኔ ዘዴዎች ጠቃሚነታቸው።
“የድንበሮች ሽግሽግ” የሚለው ፍሬ ሃሳብ፣ አንድ የግንዛቤና የትንታኔ ዘዴ ነው - “Shifting boundaries”።
እያጠጋጉ ማቆንጀት፣ እያሸጋሸጉ ማናናቅ
“የተናቁና የተከበሩ”፣ “የተጠሉና የተወደዱ”… ብለን የፈረጅናቸው፣ ድንበር ያሰመርንላቸው ነገሮች፣ በአጭር ጊዜ ወይም በቀላሉ አይለወጡም። “የተናቀ” ነገር፣ በአንድ ጀንበር፣ “የተከበረ” ተብሎ የማዕረግ ሽግግር አያገኝም።
ነገር ግን፣ ለበርካታ ዓመታት “የተጠላ”፣ “የተናቀ” ተብሎ የተፈረጀ ነገር፣ ቀስ በቀስ በሽግሽግ፣ ትንሽ ትንሽ ቦታ ማግኘት ይችላል። “መጥፎ ነገር”፣ ቀስ በቀስ፣ “በቸልታ መታየትና በዝምታ መታለፍ” ከጀመረ፣ የድንበር ሽግግር ባይሆንም፣ አንድ የድንበር ሽግሽግ ነው። “እንደ ተራ ነገር መቆጠር” ከጀመረም እንዲሁ።
ከዚህም የባሰ ይመጣል። ለመጥፎ ተግባር ለመሟገትና ጥብቅና ለመቆም የሚሞክሩ ብቅ ብቅ ይላሉ።
“ምን ያድርግ? ወዶ አይደለም!”፣ “ምን ታድርግ? ተመችቷት አይደለም” የሚል መከራከሪያና ማመካኛ ይደረድራሉ። ይሄ ሌላ የሽግሽግ ለውጥ ነው። ከዚያስ? መጥፎ ሰውን ለማቆንጀት፣ ጥሩ ሰዎችን የማናናቅ ፈሊጥ ይፈጥራል። ለምሳሌ፣ “ሌላውስ ሰው በምን ይበልጣል? ሁሉም ያው ነው” የሚል ሃሳብ እየተለመደ ከመጣም፤ የድንበር ሽግሽግ ነው። ምን ይሄ ብቻ! ጥፋተኞችን የማወደስ አባዜ ይዘወተራል። ጥፋተኛ አይደሉም ከሚል ሙግትም የባሰ አይን ያወጣ ስብከት ይስፋፋል። ጥፋተኛ አይደሉም።
“እንዲያውም፤ ተጎጂ ሚስኪኖች ናቸው። የተገፉ የተበደሉ ናቸው። ክፋቱና ጥፋቱ፣ የሌሎች ሰዎች ነው- ክብር ማዕረግ የተሰጣቸው ሰዎች ናቸው ግፈኞች በደለኞች” የሚል ሃሳብ እየተዘወተረ እየገነነ፤ የድንበር ሽግሽጉ ቁልቁል ይንሸራተታል። ይኸኔ፣ ወደ ትልቅ ሽግግር፣ ወደ ገደል አፋፍ የሚያደርስ የድንበር ሽግሽግ ተፈጥሯል ማለት ይቻላል።
“መጥፎ ነገር”፣ በዝምታ እየተፈቀደ፣ በይሁንታ እየታየ፣ ቀስ በቀስም ድጋፍ እያገኘ፣ ከዚያም አልፎ ለመቀስቀሻ እየተመረጠ፣ አርማና መፈክር የሚያበጁለት፣ ሆ ብለው የሚዘምሩለትና የሚዘምቱለት፣ የክብር ምልክት፣ የማዕረግ ዘውድ ወደ መሆን ይሸጋገራል።
“የተናቀ ነገር”፣ በሂደት “የተከበረ ነገር” ወደ መባል እስኪሸጋገር ድረስ፣ በመሃል በርካታና ዘገምተኛ የድንበር ሽግሽጎችን ይጓዛል።
“የሚዘባበቱበትና የሚዝቱበት ነገር”፤ እያጠጋጉ እያሸጋሸጉ እየሸፋፈኑ እየደጋገፉ ካንፏቀቁት ብቻ ነው፤ ከጊዜ በኋላ፣ “የሚዘምሩትና የሚዘምቱለት ነገር” ወደመሆን የሚሸጋገረው።
“መጥፎ”፣ እዚያው በዚያው፣ ወደ “ቆንጆ” አይሸጋገርም - በማሸጋሸግ ነው። “መልከ ጥፉን በስም ይደግፍ” ተብሎ የለ? በስም እየደጋገፉ ያሸጋሽጉታል። ከወዲያ ማዶም “ውበት እንደተመልካቹ ነው!” እያሉ “የቁንጅናን ድንበር” እየሸረሸሩ በማሸጋሸግ፣… ቀስ በቀስ ነው ሽግግር የሚከሰተው።
ሽግሽጉ፣ ሂደት ነው - በጥቂት በጥቂቱ።
ሽግግሩ፣ ክስተት ነው - የተደማመረ ውጤቱ።
ለከፋ እና ጭርት እየቀረ፤ የዘረኝነትና የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ ልክፍት እየባሰ።
በሁሉም ከተሞች ባይሆንም፣ በአዲስ አበባና በበርካታ ከተሞች፣ ኋላቀር “የለከፋ” አመል፣ ከመቼ ወዲህ እየቀረ እንደመጣ እቅጩን ማወቅ ያስቸግራል። ከሱቅ መስኮት አጠገብ ቆሞ፣ “አንቺ! ነይ!” ብሎ ሴት ተማሪዎችን ማመናጨቅ፣ ከዚያም አልፎ ማሰቃየት፣ በጣም የተለመደ ትዕይንት ነበር - ከበርካታ ዓመታት በፊት። ጋጠወጥነትን የሚፈቅድ የኋላቀርነት በሽታ ነው። የቀበዝባዛ ውሻ ባሕርይ፤ እየቀነሰ መምጣቱ፣ ተመስጌን ነው።
የታክሲ ውስጥ ጭቅጭቅና የመንገድ ዳር ድብድብም፣ የዘወትር ገፅታ እንደነበረ አስቡት። አካላዊ ነገሮችንም መጥቀስ ይቻላል። ጭርት፣ ቋቁቻ፣ እከክ፣ ቅጫም፣ ፎሮፎር፣…. ዛሬ እንደድሮ አይደለም። ትልቅ ሽግግር ነው።
እንዴት እንዴት፣ ከምን ወደ ምን እየቀነሰ እንደመጣ፣ አንድ በአንድ መዘርዘር፣ የእለት የእለቱንና ጥቃቅን ለውጦቹን፣ “ይሄው፣ ይሄው” ብሎ ማሳየት ግን ይከብዳል። የወሊድ ብዛት መቀነሱ፣ የወላጆች የትምህርት ደረጃ መሻሻሉ፣ የከተሜነት አኗኗር መስፋፋቱ፣ የግል ትምህርት ቤት መበራከቱ፣…. ለመልካም ሽግግር አስተዋፅኦ ያደረጉ ጉዳዮች፣ በርካታ ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን፣ ከጥቃቅን ሽግሽጎችና ከረዥም ጊዜ ሂደት የሚመጣ ነው - እያንዳንዱ መልካም ሽግግር።
መጥፎ ሽግግርም፣ እንደዚያው ነው - በረዥም ጊዜ ሂደት በጥቃቅን ሽግሽግ የሚከሰት። የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካና የዘረኝነት ልክፍት፣ ቀስ በቀስ እየተዛመተና እየሰረፀ፣ የቱን ያህል እየተለመደ በአገራችን እንደተንሰራፋ አስቡት።
በዚህም ተባለ በዚያ፣ ለክፉም ለደጉም፣ የሽግግር ለውጦች፣ የሽግሽግ ውጤቶች ናቸው።
መልካም ሽግግር እንዳያመልጠን፣ መጥፎ ሽግግርም እንዳይገጥመን ከፈለግን፣ ጥቃቅኖቹን ሽግሽጎች ልብ ብለን ማስተዋል ይኖርብናል።
በሌላ አነጋገር፣ መልካም የኑሮ መርሆችን፣ ደረጃ በደረጃ እየተገበሩና መንገዱን እያቃኑ፣ በእውን እያስፋፉ፣ መልካም ሽግሽጎችን ወደ መልካም ሽግግር ለማብቃት በእውቀት መትጋት ያስፈልጋል።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ ቀስ በቀስ የሚዛመቱና የሚስፋፉ መጥፎ መርሆች፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚፈጥሩትን ጥቃቅን ሽግሽግ ልብ በማለት፣ በጊዜ ለመከላከልና ለማስተካከል መጣር ያስፈልጋል።
መንገዳችን የሚበራውም የሚጨልመውም፣ ኑሯችን የሚሰምረውም የሚሰናከለውም፣ ቀስ በቀስ በሽግሽግ ነው።
ችግሩ ምንድነው? ሽግሽጎቹን ልብ ለማለትና ለመገንዘብ የሚረዳ፣ የሽግሽግ መቁጠሪያ ቀመር የለንም።
የእለት ተእለት ሽግሽግና የዓመት ሽግግር።
በአንድ በኩል ተመልከቱ። አንድ ዓመት፣ የ365 ቀናት ሂደት ነው - ሽግሽግ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ የአዲስ ዓመት በዓል፣ የ1 ቀን ክስተት ነው - ሽግግር ነው።
የ365 ሽግሽጎች ማሳረጊያ መለያ ታርጋ ነው - የዓመት መሸጋገሪያ እለት።
የአገር፣ የባህል፣ የታሪክ ሽግግርም እንዲሁ፣ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ፣… የብዙ ሽግሽጎችና የረዥም ጊዜያት ውጤት ነው።
የወራትና የቀናት መቁጠሪያባይኖረን አስቡት። ዓመቱ መጋመሱን ወይም ወደ ሽግግር መቃረቡን ለማወቅ አንችልም ነበር። የእለት ተእለት ሽግሽጎች፣ የት ድረስ እንደተጓዙ፣ ካለፈው ሽግግር የቱን ያህል እንደራቁ፣ ለመጪው ሽግግር ምን ያህል እንደቀራቸው መገመትም ይከብዳል (የእለት ተእለት ሽግሽጎችን የምንመዘግብበት የቀን መቁጠሪያና ቀመር ጥበበኞች ባፈጥሩልን ኖሮ)።
የቀን መቁጠሪያ ቀመር፣ ሌላ ትርጉም የለውም። ሽግሽጎችንና ሽግግርን አዋህዶ ለማየት የሚያገለግል ጥበብ ነው። እለታዊ ጥቃቅን ሽግሽጎች፣ የዓመታዊ ትልቅ ሽግግር ምልክቶች ናቸው። ይሄ እውነታ ላይ የተመሰረተ ነው - የቀን መቁጠሪያ።
የባህል ሽግሽግንና የባህል ሽግግርን አዋህዶ የሚያሳይ ጥበብስ? ምልክቶችን እየዘረዘረ
“የዚያን ጊዜ ተጠንቀቁ” እያለ የሚነግረን ጥበበኛ ምን ምን ሊለን እንደሚችል አስቡት።
አሳፋሪ የነበሩ አባባሎችና ንግግሮች፣ እንደዋዛ መወራትና መደመጥ በጀመሩ ጊዜ፣
የሚስቀወቅሱና የሚያስቀጡ ተግባራት እንደዘበት መታየትና መደረግ የጀመሩ ጊዜ፣
አስጸያፊ ባህሪዎችና ወራዳ ዝንባሌዎች፣ ያለተግሳጽ አደባባይ መውጣት የጀመሩ ጊዜ፣…
እንዲህ እንዲህ እያልን፣ ሽግሽጎችን ለመቁጠር መሞከር እንችላለን። የድንበር ሽግሽጎችን ለማስተዋልና ለማገናዘብ ግን፤ የድንበርን መስመሮች (መርሆች) ያስፈልጉናል።
እውነትና ሃሰት፣ ጥሩና መጥፎ፣ አልሚና አጥፊ፣ መልካምና ክፉ፣ ፍትህና ወንጀል…. ብለን ነገሮችን የምንፈርጅበት፣ ድንበሮችን የምናሰምርበት ዋና ቀመርና መርህ (ፍልስፍና) በጥራት ለመጨበጥ መጣር እንችላለን።

Read 2139 times