Saturday, 04 September 2021 13:31

በምሥራቅ ወለጋ ታጣቂዎች ጥቃት ሰንዝረው እስረኞችን ማስመለጣቸው ተነገረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ሳሲጋ ወረዳ፣ ታጣቂዎች በአንድ ፖሊስ ጣቢያ ላይ በፈጸሙት ጥቃት እስረኞችን አስመልጠው በርካታ የፖሊስ አባላትን ማቁሰላቸው ተነገረ።
ቢቢሲ ከአካባቢው ነዋሪዎችና ከሆስፒታል ምንጮች ማረጋገጥ እንደቻለው፣ ጥቃቱ የተፈጸመው ማክሰኞ ነሐሴ 25 ቀን 2013 ዓ.ም ነው። ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር እያለ የሚጠራውና ከወራት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪ ድርጅትነት የተፈረጀው፣ መንግሥት ሸኔ እያለ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን ጥቃቱን ስለመፈጸሙ አስታውቋል።
በሳሲጋ ወረዳ የጋሎ ከተማ ነዋሪ የሆኑ አንድ ግለሰብ ጥቃቱን በተመለከተ ለቢቢሲ ሲናገሩ፤ ማከሰኞ ረፋድ 3፡30 አካባቢ በከተማዋ የተኩስ ድምጽ መሰማት እንደጀመረ ገልጸዋል።
የተኩስ ልውውጡም በአካባቢው በነበሩ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎችና ታጣቂዎቹ መካከል መሆኑንና ይህም እስከ እኩለ ቀን መቀጠሉን ይናገራሉ። ታጣቂ ቡድኑ ጥቃት የፈጸመው በሳሲጋ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ ላይ ሲሆን በዚህም ጥቃት እስረኞችን ማስመለጡን ነዋሪው ይገልጻሉ።
“ከእስር ቤቱ ያመለጡ ስድስት ሰዎች እኔ ወደ ምሠራበት ቦታ ሸሽተው ገብተው ነበር። ክፍት በር ሲያገኙ ነው ዘልቀው የገቡት። ከዚያ በኋላ ወጥተው ሄዱ። እኔም የሥራ ቦታዬን ዘግቼ ከአካባቢው ሄድኩ” በማለት የገጠማቸውን  ገልጸዋል።
የታጣቂ ቡድኑ ቃል አቀባይ በተረጋገጠው የትዊተር ገጽ ላይ፣ ቡድኑ በሳሲጋ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ ላይ ጥቃት ስለመፈጸሙ አስፍሯል። በዚህም ጥቃት “ከ100 በላይ የፖለቲካ እስረኞች ተለቀዋል” ብሏል።
ቢቢሲ ከእስር ያመለጡ እስረኞችን ትክክለኛ ቁጥር ከገለልተኛ ወገን ማጣራት አልቻለም።
ጥቃቱን ተከትሎ በቁጥር ከ40 በላይ የሚሆኑ የአካባቢው የፖሊስ አባላት፣ የተለያየ ጉዳት ደርሶባቸው ለሕክምና ወደ ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል መምጣታቸውን ከሆስፒታሉ ማረጋገጥ ተችሏል።
ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ስድስት የፖሊስ አባላት ቀዶ ሕክምና እንደተደረገላቸውና ሌሎች ስምንት የፖሊስ አባላትም የቀዶ ሕክምና እንደሚደረግላቸው  የሆስፒታሉ ሠራተኛ ለቢቢሲ ተናግረዋል። በተጨማሪም “ስድስት ሰዎች ደግሞ ወደ አዲስ አበባ ሪፈር ተብለዋል” በማለት ለተጨማሪ ሕክምና ወደ ሌላ የጤና ተቋም የተላኩ የፖሊስ አባላት መኖራቸውንም ጨምረው ተናግረዋል። በዚህ ጥቃት ሕይወቱ ያለፈ የፖሊስ አባል ስለመኖሩ እስካሁን ማወቅ አልተቻለም።
የኦሮሚያ ክልል ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ባልቻ ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው፤ “እኔ አላውቅም። በዚህ ጉዳይ ላይ መረጃ የለኝም” በማለት ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥተዋል።
(ቢቢሲ አማርኛ)

Read 13473 times