Saturday, 04 September 2021 13:26

በወረባቦ ሰርጎ ገብቶ የነበረው ቁራጭ የህወሓት ሃይል እየተደመሰሰ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 በወረባቦ ወረዳ ሰርጎ ገብቶ የነበረው ቁራጭ የህወሓት  ሃይል እየተደመሰሰ መሆኑን የወረዳው አስተዳደር የህዝብ ሰላምና ደህንነት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ መሃመድ ሰይድ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ ተንቀዥቅዦ ወደ ወረዳው ገብቶ የነበረው ቡድን በመከላከያ፣ በአማራ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ አባላትና በማህበረሰቡ እየተደመሰሰ ነው፡፡
ቡድኑ  ወረዳውን ለቆ መሸሹን የገለጹት ሀላፊው÷ የጸጥታ ሃይሉ በገባበት እየተከተለ እየቀበረው መሆኑን ነው የገለጹት።  በየትኛውም በኩል ማምለጫ የሌለው የጁንታው ሃይል፣ አማራጩ መደምሰስ ብቻ መሆኑን አቶ መሃመድ ተናግረዋል።
 ወጣቶች በግንባር ለሚገኘው የጸጥታ ሃይል ከኋላ ደጀን በመሆን ከከተማው ማህበረሰብ ምግብ በማሰባሰብ ግንባር ድረስ በማድረስ ለሰራዊቱ ያለውን ደጀንነት በተግባር እያሳዩ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም ከጠላት ሃይል ጋር በሚደረገው ፍልሚያ የወረዳው ወጣቶች በከፍተኛ ወኔና ተነሳሽነት ያላቸውን መሳሪያ በመያዝ በጦር ግንባር ድረስ በመግባት ከጠላት ሃይል ጋር እየተፋለመ ይገኛል፡፡
በተመሳሳይ ዜና፤ በከሃዲው ጄኔራል ምግበይ ሀይለ እየተመራ በማይጠብሪ ግንባር በደባርቅና ዳባት ወረዳዎች አዋሳኞች በጫንቅ፣ ጭና እና ወቅን አካባቢዎች የመጣው የአሸባሪው የህወሓት ቡድን ተደመሰሰ፡፡ የመከላከያ ሰራዊት መረጃ እንዳመለከተው፤ ይህ ወራሪና ዘራፊ የህወሓት ቡድን የእነ ወዲ ረዳን ሒሳብ የማወራረድ ስሌት ይዞ የመጣ ነው፡፡
ከግንባሩ አዛዦች መካከል አንዱ ኮሎኔል ሀብታሙ ምህረቴ እንደገለጹት፤ በሠራዊታችን አባላት መሪነት በግንባሩ ከተሰለፈው የወገን ሀይል ጋር በሳምንቱ ጠላት የከፈተውን ተደጋጋሚ ጥቃት በመመከትና ወደ ማጥቃት በመሸጋገር የመጣውን ጠላት ለመደምሰስና ድል ለመቀዳጀት ተችሏል፡፡
በወቅን ጭና የተሰለፈው የወገን ሀይል በወሰደው እርምጃ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የህወሓት ሀይል የተደመሰሰና የተማረከ ሲሆን÷ ፀረ-ታንክ፣ ዲሽቃ ፣ ብሬን፣ ላውንቸር እና ስናይፐርን ጨምሮ የተለያዩ የነፍስ ወከፍና የቡድን መሳሪያዎች ፤ ከ15 ሺህ 600 በላይ የተለያዩ ጥይቶች፣ የመገናኛ ሬዲዮና የእጅ ስልኮች እንዲሁም የብር ኖቶች ከጠላት ተማርከዋል፡፡
(ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት)


Read 1011 times