Monday, 30 August 2021 00:00

አቤል ተስፋዬ በ70 ሚ. ዶላር የገዛው መኖሪያ ቤት አነጋጋሪ ሆኗል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የበርካታ ታላላቅ አለማቀፍ ሽልማቶች ባለቤት የሆነውና ዘ ዊክንድ በሚል ቅጽል ስሙ የሚታወቀው ትውልደ ኢትዮጵያዊው የዘመናችን የአርኤንድቢ ሙዚቃ ኮከብ አቤል ተስፋዬ በቅርቡ በ70 ሚሊዮን ዶላር በሎሳንጀለስ የገዛው እጅግ ያማረና ቅንጡ የመኖሪያ ቤት የበርካታ መገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል፡፡
አቤል ከሆላንዳውያን ባለጸጎች በ70 ሚሊዮን ዶላር የገዛውና ቤቨርሊ ሂልስ በሚባል አካባቢ በ33 ሺህ ስኩየር ጫማ መሬት ላይ ያረፈው ይህ መኖሪያ ቤት፣ በዚህ አመት በሎሳንጀለስ ከፍተኛ ገንዘብ ወጥቶበት የተሸጠ እጅግ ውድ ቤት እንደሆነ ዎል ስትሪት ጆርናል ዘግቧል፡፡
መኖሪያ ቤቱ ዘጠኝ የመኝታ ክፍሎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ፣ ሁለት መዋኛ ገንዳዎች፣ ሰው ሰራሽ ፏፏቴ፣ ሲኒማ ቤት፣ ጂምናዚየም፣ የሙዚቃ ስቱዲዮና ጨምሮ የተለያዩ ደረጃቸውን የጠበቁ የመዝናኛ ስፍራዎች እንዳሉትና በተክሎች የተዋበው ግቢው በእጅጉ ማራኪ ገጽታ እንዳለውም ተዘግቧል፡፡
የ31 አመቱ የሙዚቃ ኮከብ አቤል ከጥቂት አመታት በፊት በዚያው አካባቢ በ25 ሚሊዮን ዶላር በገዛው መኖሪያ ቤት ውስጥ ይኖር እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ ብላይንዲንግ ላይትስ የሚለው አዲስ ነጠላ ዜማው በቢልቦርድ የሙዚቃ ሰንጠረዥ ለ88 ሳምንታት በመሪነት የቆየለት አቤል ተስፋዬ በዚህም ከሳምንታት በፊት ለረጅም ተከታታይ ሳምንታት ቢልቦርድን በመምራት አዲስ የአለም ክብረ ወሰን ማስመዝገቡን ጨምሮ አስታውሷል፡፡

Read 2927 times