Tuesday, 31 August 2021 00:00

በአፍሪካ በ6 ወር ከ85 ሚ. በላይ የኢንተርኔት ጥቃት ተፈጽሟል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

     በአፍሪካ አገራት ላይ የሚፈጸሙ የኢንተርኔት ጥቃቶች መጨመራቸውንና በአህጉሪቱ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ከ85 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ አይነት የኢንተርኔት ቫይረስ ጥቃቶች መፈጸማቸውን ካስፔርስኪ የተባለው ተቋም ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው ጥናት አመልክቷል፡፡
በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ከአፍሪካ አገራት መካከል እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው የኢንተርኔት ቫይረሶች ጥቃት የተፈጸመባት ቀዳሚዋ አገር ደቡብ አፍሪካ መሆኗን የጠቆመው ጥናቱ፣ በአገሪቱ 32 ሚሊዮን ጥቃቶች መፈጸማቸውንም ገልጧል፡፡
ኬንያ በ28.3 ሚሊዮን ጥቃቶች በሁለተኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ፣ ናይጀሪያ በ16.7 ሚሊዮን ጥቃቶች፣ ኢትዮጵያ በ8 ሚሊዮን ጥቃቶች ሶስተኛና አራተኛ ደረጃን መያዛቸውንም አመልክቷል፡፡
ከኬንያ በስተቀር በሁሉም የአፍሪካ አገራት የኢንተርኔት ቫይረስ ጥቃቶች ጭማሬ ማሳየታቸውን የሚገልጸው ጥናቱ፣ በናይጀሪያ ከፍተኛው የ23 በመቶ ጭማሬ ሲመዘገብ፣ በኢትዮጵያ የ20 በመቶ በደቡብ አፍሪካ ደግሞ የ14 በመቶ ጭማሬ መታየቱን ያትታል፡፡
በ2021 የፈረንጆች አመት የመጀመሪያው መንፈቅ በአፍሪካ የተፈጸሙት ጥቃቶች ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ5 በመቶ ጭማሪ ማሳየታቸውን የጠቆመው ጥናቱ፣ ለዚህም በምክንያትነት የጠቀሰው የኢንተርኔት ወንጀለኞችና መረጃ መንታፊዎች በአፍሪካ አገራት ያለውን የዲጂታል ቴክኖሎጂ መስፋፋትና ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በቤታቸው ሆነው በኢንተርኔት አማካይነት ስራቸውን የሚያከናውኑ ሰዎች ቁጥር መበራከቱን በማጤን በአገራቱ ላይ ትኩረት ማድረጋቸውን ነው፡፡
ጥቃት ፈጻሚዎቹ የሚያሳራጯቸው ቫይረሶችና አደገኛ ሶፍትዌሮች ወደተጠቃሚዎች ኮምፒውተሮች፣ ላፕቶፖችና ሞባይል ስልኮች በተለያዩ መንገዶች እንደሚገቡ የጠቆመው ጥናቱ፣ ይህን ለመከላከልም ተጠቃሚዎች የማያውቋቸው ሰዎች የሚላኩላቸውን አጠራጣሪ ኢሜይሎችንና ሊንኮችን እንዳይከፍቱና ዳውንሎድ እንዳያደርጉ፣ ጸረ-ቫይረስ ፕሮግራሞችንና ሶፍትዌሮችን ዘወትር እንዲጠቀሙ፣ አፕሊኬሽኖችን ከታማኝ ድረገጾች ብቻ እንዲያወርዱ እንዲሁም ኦፐሬቲንግ ሲስተሞቻቸውንና አፕሊኬሽኖቻቸውን በየጊዜው እንዲያዘምኑ ወይም እንዲያድሱ ይመክራል፡፡

Read 7834 times