Print this page
Saturday, 28 August 2021 14:10

ከአፍጋኒስታን በሳምንታት ውስጥ 2.2 ሚሊዮን ሰዎች ተሰድደዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  • 3.5 ሚሊዮን ሰዎች ተፈናቅለው በድንበር አካባቢዎች ይገኛሉ
          • ሲአይኤ እና ታሊባን በድብቅ መወያየታቸው ተነግሯል


             ታሊባን ከ20 አመታት የትጥቅ ትግል በኋላ ዳግም ወደ ስልጣን ከተመለሰ በኋላ በነበሩት ያለፉት ሳምንታት ብቻ 2.2 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ከአፍጋኒስታን ሸሽተው መውጣታቸውንና ሌሎች ተጨማሪ 3.5 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ደግሞ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው በድንበር አካባቢዎች እንደሚገኙ መነገሩን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በአገሪቱ ያለው አለመረጋጋትና መጪው ጊዜ ያሰጋቸው እጅግ በርካታ አፍጋኒስታናውያን ወደ ጎረቤት አገራት ለመሰደድ የካቡል አውሮፕላን ጣቢያን ባጨናነቁበትና በድንበር አካባቢዎች በሚንከራተቱበት የጭንቅ ሰሞን፣ የድንበር መስመሮችን በጥብቅ ቁጥጥር ስር ያዋለው ታሊባን ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው ጥብቅ መግለጫ አፍጋኒስታናውያን አገራቸውን ጥለው መውጣት እንደማይችሉ ማስጠንቀቁን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ታሊባን ወደ አፍጋኒስታን መመለሱን ተከትሎ ከአገሪቱ የተሰደዱ ሰዎችን በብዛት በመቀበል ቀዳሚነቱን በምትይዘው ጎረቤት አገር ፓኪስታን 1.5 ሚሊዮን ያህል አፍጋኒስታናውያን እንደሚገኙ ያስታወቀው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን፣ ከሰሞኑ 780 ሺህ ያህል ስደተኞችን የተቀበለቺው ኢራንም በግዛቷ የምታስተናግዳቸው አጠቃላይ አፍጋኒስታናውያን ስደተኞችን ቁጥር ወደ 3.5 ሚሊዮን ማድረሷን ጠቁሟል፡፡
በተያያዘ ዜና ደግሞ፣ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አሜሪካውያን ወታደሮች እስከ መጪው ማክሰኞ ድረስ አፍጋኒስታንን ሙሉ ለሙሉ ለቅቀው እንደሚወጡ ማስታወቃቸውን ተከትሎ የተለያዩ አገራት ጦሩ ጥቂት እንዲቆይ በአሜሪካ ላይ ጫና ማድረግ በጀመሩበት በዚህ ሰሞን፣ የአሜሪካው የስለላ ተቋም ሲአይኤ ዋና ዳይሬክተር ዊሊያም በርነስ አፍጋኒስታንን ከተቆጣጠረው ታሊባን መሪ ሙላህ ባራዳር ጋር በመዲናዋ ካቡል ሚስጥራዊ ውይይት እንዳደረጉ እየተዘገበ ነው፡፡
ሁለቱ መሪዎች በሚስጥር እንደተወያዩ የሚያመለክቱ መረጃዎችን ማግኘቱን አሶሼትድ ፕሬስ ቢዘግብም፣ ከሁለቱም ወገን በጉዳዩ ዙሪያ እስካሁን ምንም አይነት ምላሽ አለመሰጠቱ የተነገረ ሲሆን፣ ዋሽንግተን ፖስት በበኩሉ ምናልባትም ውይይቱ የአሜሪካ ወታደሮች ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከአፍጋኒስታን ይወጣሉ በተባለው ጉዳይ ዙሪያ ያተኮረ ሊሆን እንደሚችል አስነብቧል፡፡
የታሊባን ቃል አቀባይ ባለው ማክሰኞ በሰጡት መግለጫ፣ በተለያዩ የሙያ መስኮች ተቀጥረው የሚሰሩ የአገሪቱ ሴቶች ለደህንነታቸው አስጊ ያልሆነ ሁኔታ እስኪፈጠር ድረስ ከቤታቸው እንዳይወጡ የቡድኑ ቃል አቀባይ ማስጠንቀቃቸውንም ሮይተርስ ዘግቧል፡፡


Read 988 times
Administrator

Latest from Administrator