Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 08 September 2012 12:49

የጎረቤታማቾቹ ፍጥጫ በካርቱም

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ደቡብ አፍሪካ ለምታስተናግደው  29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ  በመጀመርያ ጨዋታቸው ዛሬ ካርቱም ላይ ሱዳን ከአትዮጵያ ሊፋጠጡ ነው፡፡ የአፍሪካ ዋንጫን ከመሰረቱት አራት አገራት መካከል የሚገኙት ጎረቤታማቾቹ ሱዳንና ኢትዮጵያ በሁሉም ውድድሮች ከዛሬ  ጨዋታ በፊት 24 ግዜ ተገናኝተዋል፡፡ 10 ጊዜ ሱዳን ስታሸንፍ በ8 ኢትዮጵያ ድል ቀንቷት በ6 ግጥሚያዎች አቻ ተለያይተዋል፡፡ ሁለቱ ብሄራዊ ቡድኖች ከዛሬው ፍልሚያ በፊት ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት ከዓመት በፊት በሴካፋ ውድድር ላይ ሲገናኙ 1 እኩል ወጥተው ነበር፡፡ ዋልያዎቹ በሚል ስሙ የሚታወቀው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ላለፈው አንድ ወር በባህርዳርና በአዳማ ከተሞች  ከፍተኛ ዝግጅት ነበረው፡፡ ከሁለት ሳምንት በፈት የአቋም መፈተሻ ግጥሚያውን ወደ ሰሜን አፍሪካ በመጓዝ ከሊቢያ ጋር  አድርጎ 2ለ1 ተሸንፏል፡፡

ከ55 ዓመታት በፊት የአፍሪካ ዋንጫ ሲመሰረት ግንባርቀደም ተዋናይ የነበረችው ኢትዮጵያ በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ ከበቃች 31 ዓመታት አልፈዋል፡፡ ዘንድሮ ተሳትፏዋን ለማሳካት የምትችልበት መልካም አጋጣሚ እንደተፈጠረላት እየተገለፀም ነው፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ከሳምንት በፊት ለብሄራዊ ቡድኑ አባላት ባስተላለፈው መልዕክት ወደ 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በማለፍ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት የተከፋውን ህዝብ እናፅናናው ብሏል፡፡ ፌደሬሽኑ ብሄራዊ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫው የመጨረሻ ዙር የማጣርያ ምእራፍ የምእራብ አፍሪካዋን ቤኒን ጥሎ ለማለፍ የበቃበትን ውጤት በማድነቅ  ለአባላቱ ከ5 እስከ 10ሺ ብር ሲሸልምም በቀጣይ በሚመዘገብ ውጤታማነት ላይ ተጨማሪ ቦነስ ለመስጠት ቃል ገብቷል፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ከወር በፊት ለወንድ እና ሴት ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኞች እና ረዳቶቻቸው የደሞዝ ጭማሪ፤ የመድህን ዋስትና እና የተለያዩ ድጋፎችን ለመስጠት እንደወሰነም ታውቋል፡፡ የዋልያዎቹ ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው አስቀድሞ ከነበረ ደሞዛቸው 13ሺ ብር ጭማሪ በማግኘት 30ሺ ብር ወርሃዊ ደሞዝ ሲታሰብላቸው ረዳት አሰልጣኝ የሆኑት ስዩም ከበደ በ5ሺ ብር ጭማሪ 20ሺብር እንዲሁም የቡድኑ ወጌሻ ይስሃቅ ሽፈራው በ2ሺ ብር ጭማሪ 5ሺ ብር በወር እንዲከፈላቸው ተወስኗል፡፡

ከ28 የአፍሪካ ዋንጫዎች  በዘጠኙ  ተሳትፎ የሚያውቀው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በውድድሩ ባስመዘገበው ውጤት 16ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በዚህ የተሳትፎ ታሪኩ 24 ጨዋታዎች ያደረገ ሲሆን በ7 አሸንፎ በ2 አቻ ወጥቶ በ15 ተሸንፏል፡፡ 28 ጎሎች አግብቶ 54 ጎሎች ገብተውበታል፡፡ 23 ነጥብ አግኝቶ በ33.3 % ውጤታማነቱ ተለክቷል፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ የተሳትፎ ታሪኳ ኢትዮጵያ 1 ግዜ ዋንጫውን ስተወስድ፤ 1 ግዜ ሁለተኛ፤ 1 ግዜ ሶስተኛ እንዲሁም ለሁለት ጊዜያት አራተኛ ደረጃ በማስመዝገብ በውድድሩ ታሪክ በ11ኛ ደረጃ ላይ የሰፈረ ስኬት አግኝታለች፡፡  ኢትዮጵያ በውድድሩ ላይ ለመጨረሻ ግዜ የተሳተፈችው በ1982 እኤአ ሊቢያ ባስተናገደችው 10ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ነበር፡፡

በ2008 እና በ2012 የአፍሪካ ዋንጫዎችን ለመካፈል የቻለችው ሱዳን በምስራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ለውጥ ካሳዩ ብሄራዊ ቡድኖች ግንባር ቀደሟ ናት፡፡   የሱዳን ብሄራዊ ቡድን የናይል አዞዎች በሚል ቅፅል ስያሜ ይታወቃል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ በአህጉራዊ የክለብ ውድድሮች ከፍተኛ ስኬት በማስመዝገብ ላይ ከሚገኙት ከአልሜሪክና ከአልሂላል ኦምዱርማን ክለቦች በተሰባሰቡ ተጨዋቾች የተዋቀረ ነው፡፡ ባለፉት 10 አመታት በሁለት የአገሪቱ ትልልቅ ሃብታሞች በአልሜሪክ እና አልሂላል ላይ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት መደረጉ ክለቦቹ በአህጉራዊ ውድድሮች ላይ ውጤታማ እንዲሆኑ አግዟል፡፡ ለብሄራዊ ቡድኑ በከፍተኛ ደረጃ ማደግና በአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎው ደካማ በነበረው የምስራቅ አፍሪካ እግር ኳስ የበላይነት ምክንያትም ሆኗል፡፡ ሁለቱ ክለቦች ያላቸው የፋይናንስ አቅም ከበርካታ የአፍሪካ አገራት ፕሮፌሽናል ተጨዋቾችን ለማሰባሰብ ከመቻላቸውም በላይ አገር በቀል ተጨዋቾችም ከእነሱ በሚያገኙት ልምድ በከፍተኛ ብቃት ላይ እንዲገኙ አድርጓቸዋል፡፡ሱዳን  በ1970 እኤአ ላይ በአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮን ለመሆን የበቃች ሲሆን ለመጨረሻ ግዜ ደግሞ ከ1 ዓመት በፊት ኢኳቶርያል ጊኒ እና ጋቦን ባዘጋጁት የአፍሪካ ዋንጫ በመሳተፍ እና ለሩብ ፍፃሜ በመድረስ አስደናቂ አቋም አሳይታለች፡፡ በወርሃዊ የፊፋ የእግር ኳስ ደረጃ 114ኛ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ  በሴካፋ ውድድር ለ4 ጊዜያት ሻምፒዮን ለመሆን ስትበቃ 103ኛ ደረጃ ላይ ያለችው ሱዳን ደግሞ 3 ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት ተሳክቶላታል፡፡

 

 

Read 32349 times Last modified on Saturday, 08 September 2012 12:53