Print this page
Saturday, 28 August 2021 13:09

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(0 votes)


                          ‹‹መጀመሪያ እንደ ሰው፤ ከዚያ እንደ ፈረንሳዊ አስባለሁ››
                           
            “Back to virginity” የምትል የቆየች የእንግሊዝኛ ግጥም ነበረች፡፡ ርዕሷን እወደዋለሁ፡፡ ምናልባት ሊታሰብ እንጂ ሊሆን የማይችል ነገር ስለሚመስል ይሆናል:: ነገር ግን ‹አይሞከሩም› የተባሉ ብዙ ነገሮች ‹መሞከር› ብቻ ሳይሆን ተችለዋል፡፡ ሀሳብ ላይ ደግሞ ቀላል ነው፤ አሳማኝ እስከ ሆነ ድረስ…!!
ወዳጄ፡- በኑሯችን ውጣ ውረድ ወይም በሕይወት ጉዟችን ላይ ‹‹እንደዚህ መሆኑን አላወቅሁም፣ ተሳስቼ ነበር፣ ተፀፅቻለሁ፣ አሁን ገባኝ›› የምንለው ትናንት ሳንረዳ ያለፈውን እውነት ዛሬ ላይ ስናውቅ ይመስለኛል፡፡ ‹በፊደልም ሆነ በአሳር› ከልምድ መማር እንደገና መወለድ ነው፡፡… እንደገና ድንግልና!!
ድንግል መሬት፣ ድንግል ጨረቃ፣ ድንግል ሐሳብ፣ ድንግል ቀን፣ ድንግል ሰማይ … ሁሌም አለ፡፡ ሕይወት ዙሪያ ገባዋ ድንግል ነው፡፡ ለውጥ እስካለ ድንግልና አለ:: እየመላለሱ አዲስ መሆን፡፡… እየታመሙ መዳን፤ እየሞቱ መነሳት… እንደ ኢየሱስ፡፡… እንደ ዘር ፍሬ!!
ወዳጄ፡- የምትጠቀምበትን የእጅ ስልክ ወደ ፋብሪካው ሞድ ልትመልሰው ትችላለህ:: አሮጌው አፓራተስ ተመልሶ አዲስ አይሆንም፡፡ አሰራሩ ወይም ሲስተሙ ግን የተጫኑበትን አፕሊኬሽኖች፣ መዛግብትና ምስሎች ጠራርጎ በማስወገድ እንደ አዲስ ‹ሀ› ብሎ ይጀምራል… Restart!
ሜሞሪው ባዶ ከሆነ ስልኩ እንደ ወንበርና ጠረጴዛ የሚቆጠር ዕቃ ነው፡፡ በውስጡ ሀሳብ የለም፡፡ ወደ ውጭ ሲደውል ወይም ወደ ውስጥ ሲቀበል ግን መመዝገብ ይጀምራል:: የመዘገበውንም ከዓመታት በኋላ ሲጠየቅ አስታውሶ ያሳውቃል፡፡ ሰውም የተማረውንና በልምድ ያከማቻቸውን ሀሳቦች ውንፍ፣ ዝንፍ ሳይል ማስታወስ ሲችል ‹ያውቃል› ይባላል፡፡ የማወቁ ጥቅም የሚለካው ግን በሚያስታውሳቸው ነገሮች ላይ ተመስርቶ በሚፈጥረው አዲስ ነገር፣ ፈልፍሎ በሚያወጣው ግኝት፣ በሚያቀርበው አሳማኝ ምክንያትና በቀጣይነት ሊከናወን የሚገባን ድርጊት ከወዲሁ ማመላከት ሲችል ነው፡፡ የተማረውንና በልምድ ያካበተውን ዕውቀት ሊያስታውስ ካልቻለ ግን ሚሞሪው እንደ ተደመሰሰ ስልክ ‹ዕቃ› ብቻ ይሆናል፡፡ ወይም ባዶ ሰው፡፡ ‹ቅል ራስ› (empty headed) እንደሚሉት፡፡
አንድ የድሮ ቀልድ ነበረች፡፡ ሰውየው በመርሳት ሕመም ስለተቸገረ ሃኪም ዘንድ ይቀርባል፡-
‹‹ምን ሆንክ?›› ሲለው
‹‹ትንሹንም ትልቁንም እየረሳሁ ተቸገርኩ››
‹‹መቼ ነው የጀመረህ?›› ሲባል ምን እንዳለ ታውቃለህ? …መጨረሻ ላይ መልሱን እነግርሃለሁ፡፡
ወዳጄ፡- በብዙ አገራት የኮሌጅ ተማሪ ትምህርቱን በተገቢውን መንገድ (formal withdrawal) ቢያቋርጥም፤ እንደገና ወደ ትምህርት ገበታው መመለስ የሚችለው ወይም የሚፈቀድለት (readmission) እስከ አምስት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ ነው:: ያ ጊዜ ካለፈ የመጨረሻ ዓመት ተማሪ የነበረ እንኳን ቢሆን ወደ ኋላ ተመልሶ፣ እንደ አዲስ እንዲጀምር ይደረጋል። አንዳንድ ቦታ ደግሞ አጠቃላይ ፈተና ተዘጋጅቶ ይሰጠውና የደከመባቸውን ኮርሶች መልሶ ይወስዳል:: ይኸ የሚደረገው ተማሪው የቀሰመውን ዕውቀት ማስታወስ መቻሉን ለማረጋገጥ ነው፡፡
የጊዜ መርዘም ወይም የዕድሜ መግፋት አዕምሯችንን በኑሮ ውጣ ውረዳችን ውስጥ በሚመላለሱ ሀሳቦች፣ የደስታና የብስጭት ስሜቶች፣ የቤተሰብ፣ የስራና የዜግነት ተግባራትን በሚመለከቱ ጉዳዮች ያጨናንቀዋል፡፡ እንኳን በይድረስ ይድረስ፣ አስረግጠን የተማርነውን ነገር እንኳን ለማስታወስ ይቸግራል፡፡ በተለይ የተሰማራንበት የሥራ መስክ ከተማርነው ትምህርት ጋር ካልተዛመደ ወደ ኋላ ተመልሶ ማስታወስ ከባድ ይሆናል፡፡
በኮምፒውተር ቋንቋ ‹RAM› የምንለው ሶፍትዌር ወይም የአእምሮ አካል ይደክማል። ስለዚህ በግል ጥናት ንባብና ምርምር ዕውቀታቸውን ማዳበር ላቃታቸው ተሃድሶ ወይም ክለሳ ማድረግ ተገቢ ነው … Restart!
ወዳጄ፡- ወደ ወቅታዊ ጉዳያችን ስንመጣ፤ ኮሮናን ማሸነፍ የመኖርና ያለ መኖር ጥያቄ ሆኗል፡፡
ወረርሽኙ የፈጠረው ቀውስ አለማችንን እያመሳት ነው፡፡ ይኸ ሃቅ በቦታው ሆኖ ‹‹ሳይደግስ አይጣላም›› እንደሚባለው፣ ኮሮና በኛ አገር ዐውድ ያስታወሰችን ወይም ‹Restart› እንድናደርግ ያገዘችውን ዕውነት መካድ አይቻልም፡፡
ይኸ የችግር ወቅት ሲታለፍ ኮሮና ‹‹A blessing in disguise›› መሆኗ ሳይወሳላት አይቀርም::  እንደገና ወደ ድንግልና መልሳናለች ይባልላታል፡፡ የዛ ሰው ይበለንና!!
…ኮሮና ጥንታዊውን ሰላምታ አስታውሳናለች፡፡ ኮሮና ከምንም ነገር በላይ ‹ሰው› መሆን እንደሚበልጥ፣ በመከራ ጊዜ ማንም ሆነ ማንም እንደ ‹ሰው› ለማሰብ እንደሚገደድ አሳይታናለች፡፡
‹‹መጀመሪያ እንደ ሰው፣ ከዚያ እንደ ፈረንሳዊ አስባለሁ›› በማለቱ ነበር ቮልቴር የተሰደደው፡፡ ኮሮና ለኛዎቹ ጎሰኞች መማሪያ ናት፡፡ ኮሮና ‹‹አንድነት ሃይል ነው›› የሚለውን፣ የረሳነውን ሳይንሳዊ መርህ Click በማድረግ፣ ያገራችን ሰዎች የተቆለፈባቸውን ሳጥን ሰብረው፣ እርስ በርሳቸውም ሆነ ከመላው ዓለም ሕዝብ ጋር ‹‹ሕመምህ ሕመሜ›› እንዲባባሉ ሰበብ ሆናለች፡፡ ኮሮና ሕይወት ‹‹ፎርሙላ›› እንደሌላት፣ በሚቀጥለው ደቂቃ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ማንም እንደማያውቅ፣ ሞታችንን በጉያችን ይዘን እንደምንኖር አሳውቃናለች፡፡
ኮሮና ራስን መግዛትን፣ ትዕግስትን፣ ደግነትን፣ መተሳሰብን፣ ለቤተሰብ ጊዜ መስጠትን አስተምራናለች:: ኮሮና የየዕምነቶቻችንን አስተምህሮት በጥልቀት እንድንረዳና ማንነታችንን በተግባር እንድንፈትን ዕድል ሰጥታናለች፡፡
ኮሮና ስለ ድንገተኛ አደጋ ዝግጁነት፣ የጤናና የህክምና አገልግሎት ተደራሽነት፣ የክፉ ቀን ስንቅ በጐተራችን ስለማስቀመጥና ገበያ ስለሚያረጋግጉ መሠረታዊ ሸቀጦች ክምችት እንድንጨነቅ አድርጋናለች፡፡
 ኮሮና ሕዝብና መንግሥት ከተደማመጡ በአገር ጥቅም፣ ሉዐላዊነትና ህልውና ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን በቀላሉ መመከት እንደማያስቸግር አንቅታናለች፡፡ ከሌሎችም ብዙ ነገሮች በላይ ደግሞ ኮሮና የመደመርን ፍልስፍና ገቢራዊ  ገጽታ አሳይታናለች፡፡
ወዳጄ፡- ሰዎች አንድን አስተሳሰብ ወይም ፍልስፍና ‹‹መርህ›› አድርገው የሚቀበሉበት የተለያየ ምክንያት አላቸው። ፕራግማቲስቶች ብዙውን ጊዜ እንደ ‹‹ሎጂክ›› በመሳሰሉ ሃሳባዊ የችግር አፈታት ስልቶች ላይ አያተኩሩም፡፡ ይልቁንም የሕዝቦች እርስ በርስ ግንኙነትና አኗኗራቸው የበለጠ ያስጨንቃቸዋል፡፡
ይበጀናል የሚሉትን ፍልስፍና የሚቀበሉት ፍላጐታቸውን በማሳካትና ሽንቁር ኑሯቸውን በመድፈን ረገድ የሚያተርፍላቸው ጥቅም እንዳለና እንደሌለ መርምረው በሚያገኙት ውጤት ነው፡፡ በግብር ያልተፈተነ ፍልስፍናም ሆነ ዕውቀት ምናልባት ‹‹ሰማያዊውን ዓለም›› ተስፋ ለሚያደርጉ ‹‹አማንያን›› ካልሆነ በስተቀር ምድር ላይ አሳራቸውን ለሚያዩ ጐስቋሎች ምናቸውም አይደለም ባይ ናቸው፡፡
Logic and Sermons never convince,
The damp of the night drives deeper into my soul…
Now I reexamine philosophies and religions.
They may prove well in lecture rooms,
Yet not prove at all under the spacious clouds,
And  along the land scape and flowing currents.
 …በማለት የሚያረጋግጥላቸው ደግሞ ታላቁ ገጣሚ ዋልት ዊትማን ነው - ‹‹Leaves of Grass›› በሚለው ግጥሙ፡፡ እኔ ደግሞ ለዛሬ ‹‹ነገ›› የምትለዋን የቆየች ግጥም እጋብዛችኋለሁ፡፡ ‹‹ነገ›› ድንግል ቀን ናት፡፡
ጓዙን አግተልትሎ
‹እኔን› መስሎ ደግሞ
ይጠቃቅሰኛል፣
ያ…የምናፍቀው ቀን
የማላውቀው ‹ነገ›
‹ዛሬ› ነኝ ይለኛል
ይኸው ፊቴ ቆሞ፡፡
***
እባክህ አትምጣ
እኔው እመጣለሁ
ደግሞ ዛሬ ብዬ
እሞኝብሃለሁ፡፡
* * *
ወደ ቀልዳችን ስንመለስ፡- ሰውዬአችን ሃኪም ቤት ሄዶ፡-
‹‹ትንሹንም ትልቁንም እየረሳሁ ተቸግሬአለሁ ምን ይሻለኛል?›› ብሎ ሃኪሙን ሲያማክረው ሃኪሙም፡ - ‹‹መቼ ነው የጀመረህ?›› በማለት እንደጠየቀው ተጨዋውተናል፡፡ አጅሬው ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው?
‹‹ምኑ!?››
ወዳጄ፡- እዚህ ጋ ‹‹Restart›› ማድረግ መፍትሔ የሚያስገኝ አይመስልህም?...ወይስ…
ሠላም!!
ምንጭ፡- (አዲስ አድማስ ዌብሳይት፤ "የሃሳብ መንገድ"፤ 21 አፕሪል 2020)Read 462 times