Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 08 September 2012 12:44

በለንደን ፓራሊምፒክ ለኢትዮጵያ የመጀመርያው ሜዳልያ ተገኘ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ለ16ኛ ጊዜ በሚካሄደው እና ነገ በሚጠናቀቀው  የለንደን ፓራሊምፒክ ላይ ፓራሊምፒያን ወንድዬ ፍቅሬ የብር ሜዳልያ በመውሰድ ለኢትዮጵያ ፈርቀዳጅ ውጤት በማስመዝገብ ታሪክ ሰራ፡፡ ባለፈው ማክሰኞ በተካሄደው በ1500ሜ ውድድር ላይ አትሌት ወንድዬ  2ኛ ደረጃ ሲያገኝ ርቀቱን በ3 ደቂቃ ከ50.87 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ በመሸፈን የግሉን ምርጥ ሰዓት አስመዝግቧል፡፡ በፓራሊምፒኩ ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ የውድድር መደብ አራት ፓራሊምፒያኖችን ያሳተፈች ሲሆን ፓራሊምፒያኖቹ በየውድድር መደባቸው ጥሩ ተፎካካሪ ሆነዋል፡፡ በ1500 ሜትር በታሪክ የመጀመርያውን የኢትዮጵያ የፓራሊምፒክ ሜዳልያ ከወሰደው ወንድዬ ፍቅሬ ሌላ  ኢትዮጵያን የወከሉት አትሌቶች ተስፋለም ከበደ ፤ ኪሮስ ረዲ እንዲሁም በሴቶች የአጭር ርቀት ውድድሮች የተሳተፈችው የንጉስ አዘናው ናቸው፡፡

በ1500 ሜትር 5ኛ ደረጃ አግኝቶ ለፍፃሜ ያልደረሰው ተስፋለም ከበደ ባለፈው ሀሙስ በተካሄደው የ800 ሜትር ማጣርያ 5ኛ ደረጃ አግኝቷል፡፡ የንጉስ አዘናው በበኩሏ በ200ሜትር ተካፍላ 6ኛ ደረጃ ያገኘች ሲሆን በሳምንቱ አጋማሽ ላይ በተሳተፈችበት 100ሜትር ደግሞ 5ኛ ሆናለች፡፡

በ16ኛው የለንደን ፓራሊምፒክ በ21 የስፖርት አይነቶች 503 የውድድር መደቦች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ ከ165 አገራት የተወከሉ ከ4200 በላይ ፓራሊምፒያኖች በተሳተፉበት ፓራሊምፒኩ 15 አገራት በታሪክ የመጀመርያ ተሳትፏቸውን እንዳገኙበትም ታውቋል፡፡ ውድድሩ ሰባተኛው ቀን ላይ ሲደርስ  69 አገሮች ሜዳልያ ሰንጠረዥ ውስጥ የገቡ ሲሆን አፍሪካን የወከሉ 8 አገራት በድምሩ 40 (10 የወርቅ፤14 የብርና 16 የነሐስ) ሜዳልያዎች  በማግኘት ስኬታማ ሆነዋል፡፡ ስምንቱ አገራት ናይጄርያ፤ ደቡብ አፍሪካ፤ ግብፅ፤ቱኒዚያ፤ ሞሮኮ፤ አልጄርያ፤ ናሚቢያ እና ኢትዮጵያ ናቸው፡፡

16ኛው የለንደን ፓራሊምፒክ በውድድሩ የ52 ዓመታት ታሪክ ከፍተኛ የትኬት ሽያጭ  ማስገኘቱን ዓለምአቀፍ የኦሎምፒክ ኮሚቴ የገለፀ ሲሆን 2.5 ሚሊዮን ትኬቶች ተሸጠውበታል፡፡ የፓራሊምፒክ ውድድር በ1960 እ.ኤ.አ ሮም ላይ የተጀመረ ሲሆን ከለንደን በፊት  በተካሄዱ 15 የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች የውድድሩ መከታተያ ትኬቶች ባመዛኙ በነፃ ይሰጡ ነበር፡፡

በ2004 እ.ኤ.አ አቴንስ ባዘጋጀችው 14ኛው ፓራሊምፒክ 850ሺ ትኬቶች፣ በ2000 እ.ኤ.አ ላይ የአውስትራሊያዋ ሲድኒ ባዘጋጀችው 13ኛው ፓራሊምፒክ 1.2 ሚሊዮን ትኬቶች እንዲሁም ከ4 ዓመት በፊት ቤጂንግ ባስተናገደችው 15ኛው ፓራሊምፒክ 1.8 ሚሊዮን ትኬቶች ተሸጠው ነበር፡፡ኢትዮጵያ በፓራሊምፒክ ስትሳተፍ የዘንድሮው ለ6ኛ ጊዜ ነው፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ የተሳተፈችው በ1968 እኤአ ቴላቪቭ ላይ ነበር፡፡ በወቅቱ ሁለት ፓራሊምፒያኖች በአትሌቲክስ እና የጠረጴዛ ቴኒስ ውድድሮች ተሳትፈዋል፡፡ ከስምንት ዓመታት በኋላ ደግሞ በ1976 እኤአ እና በ1980 እኤአ ላይ አብርሃም ሃብቴ የተባለ አትሌት በአትሌቲክስ፤ በጠረጴዛ ቴኒስ እና በሎውን ቦውል ውድድሮች ተሳትፏል፡፡ ከ24 ዓመታት ቆይታ በኋላ በ2004 እኤአ ላይ በአቴንስ ፓራሊምፒክ ኪሮስ ተክሌ የተባለ አትሌት በአትሌቲክስ ለመሳተፍ ሲበቃ ከ4 አመት በፊት ደግሞ በቤጂንግ ሁለት ፓራሊምፒያኖች  ተሳትፈዋል፡፡

 

 

Read 3054 times Last modified on Saturday, 08 September 2012 12:47