Saturday, 08 September 2012 12:26

ቴዎድሮስና ሰላማ፤ ዘውዲቱና ማቴዎስ፤ ኃይለሥላሴና ቴዎፍሎስ፤ መንግሥቱና መርቆርዮስ፤ መለስና ጳውሎስ

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(0 votes)

አንድ አባት ሰሞነኛ ስለሆነው የአገራችን የሀዘን ክስተት አንስተው በርዕሴ የተመለከቱት አምስት የአገር መሪዎችና አምስቱ የሃይማኖት አባቶች ከስደተኝነትና ከአማሟታቸው ጋር በተያያዘ የተጋሩት ታሪክ ምን አንደምታ ይኖረው ይሆን? በሚል ጥያቄ ሲያነሱ መስማቴ ለዚህ ጽሑፍ መፃፍ መነሻ ሆኖኛል፡፡ ከስተደኝነትና የአሟሟት ታሪካቸው በተጨማሪ ወዳጅነትና ባለራዕይነትን ለመጨመር እሞክራለሁ፡፡ “ዓፄ ቴዎድሮስ እና የኢትዮጵያ አንድነት” በሚል ርዕስ በታሪክ ፀሃፊው በተክለጻዲቅ መኩሪያ ተዘጋጅቶ በ1981 ዓ.ም በታተመው መጽሐፍ ውስጥ እንድርያስ የሚባሉ የ25 ዓመት ወጣት ግብፃዊ፤ አባ ሰላማ ተብለው በመሰየም በ1834 ዓ.ም በጳጳስነት ለማገልገል ወደ ኢትዮጵያ እንደመጡና አፄ ቴዎድሮስን የንግሥና ዙፋን ያስደፉት ወይም ያነገሷቸው እኚሁ ጳጳስ እንደነበሩ ያብራራል፡፡

ንጉሡና ጳጳሱ የዘመኑ ችግር የነበረውን “በኢትዮጵያ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ያለውን የቅባቶችና የፀጋዎችን ልዩነት ወደ አንድ የካራዎች መስመር ለማግባት የኃይል እርምጃ ወስደዋል” ከዚህ ባሻገር የሚሲዮናዊያኑን እንቅስቃሴ ለማስቆም በጋራ ብዙ ሰርተዋል፡፡

ይህ ወዳጅነት ግን መቀጠል አልቻለም፡፡ አቡነ ሰላማ “ቴዎድሮስን የተከተለ ገዝቻለሁ” እስከማለት የደረሱ ተቃዋሚ ሊሆኑ በቅተው ነበር፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ጥር 22 ቀን 1858 ዓ.ም ለንግሥት ቪክቶሪያ በጻፉት ደብዳቤ “ጳጳስ ነኝ ብሎ ከመጣ ግብጽ ጋር ሆነው ያደረጉኝን እግዚአብሔርን ከሚፈራ ሰው ጠይቀው ያግኙት” በማለት በአባ ሰላማ የደረሰባቸውን መከዳት አማረዋል፡፡

ተቃርኖው እየሰፋ በመሄዱም አቡነ ሰላማ የግዞት ታሳሪ ሆኑ፡፡ በመጀመሪያ ለለውጥና ዕድገት ብዙ ነገሮችን በጋራ ሲሰሩ የነበሩት አቡነ ሰላማና አፄ ቴዎድሮስ ህልፈታቸው በተመሳሳይ ጊዜ መሆኑም ያስደምማል፡፡

“ጳጳሱ አቡነ ሰላማ፣ እዚያው እግዞት እንዳሉ በ1860 ዓ.ም ጥቅምት 15 ቀን ሞቱ” የሚለው የተክለጻዲቅ መኩሪያ መጽሐፍ፤ አፄ ቴዎድሮስም በዚያው ዘመን መቅደላ ላይ ማረፋቸውን ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ለ1ሺህ 500 ዓመታት ያህል ከግብጽ ፓትርያርክ እየተሾመ ሲመጣላት ቆይቶ፣ በ1951 ዓ.ም የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሊቀ ጳጳስ በአገር ውስጥ መሾም በመቻሉ የወቅቱ ንጉስ አፄ ኃይለሥላሴ ምስጋናውን ይወስዳሉ፡፡ ንጉሱና ሁለተኛው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ አቡነ ቴዎፍሎስ በደርግ መንግሥት በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወታቸውን እንዲያጡ መደረጋቸውም አስገራሚ መመሳሰል ይፈጥራል፡፡

ንጉሱንና ፓትርያርኩን ጨምሮ ለብዙ ዜጐች ሕይወትና ንብረት መጥፋት ምክንያት የነበረው የደርግ መንግሥት፤ ታሪኩ የተቋጨው በሽሽትና በስደት ነበር፡፡ ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ በ1989 ባሳተሙት “እየሄድኩ አልሄድም” የተሰኘ የግጥም መድበል ውስጥ “የመሪዎች ስደት” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ግጥም አገርና ሕዝብን ጥለው ስለሚሸሹ መሪዎች ሕሊናን የሚሞግት ስንኞች አቅርበዋል፡፡

ግጥሙ የሚጀምረው በዩጋንዳዊያን የድርሰት ሥራ ውስጥ ስለምትገኝ አንዲት ሴት በመግለፅ ነው፡፡ ሴትየዋ “እግዜር የት ቆሞ ነው የፈጠረን እኛ?” የሚል  ጥያቄ ስታነሳ ሌላው “የሩቁን የጥንቱን ከምትመረምሪ፣ ጠይቂ ያሁኑኑ ብለሽ፤ የት ነው ያለው?” ይላታል፡፡ ሦስተኛው አካል ለጠያቂዎቹ “ሰማይ ቤት ነው ያለው” የሚል መልስ ይሰጣቸዋል፡፡ ይህንን በልቦለድ ላይ ተመስርቶ የቀረበ ግጥም አገራዊ ለማድረግ የሞከሩት ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ፤ ግጥማቸውን የሚያጠናቅቁት በሚከተሉት ጠያቂ ስንኞች ነው፡፡

ከምድር ተሽቀንጥሮ ሰማይ ከነጐደ

በጅቡቲ በኩል እንግሊዝ ከሄደ

በናይሮቢ በኩል ሐራሬ ከሄደ

ከሕዝብ ፍላጐት እየበረገገ

ለሕዝብ ነኝ ብሎ ከሕዝብ ካልሆነ

ብቻውን ለመጓዝ ከተደናበረ

ምኑንስ እረኛ ምኑን መሪ ሆነ?

አፄ ኃይለሥላሴና ሊቀ ጳጳስ ቴዎፍሎስ ሕይወታቸውን በግፍ እንዲያጡ በመደረግ፤ ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያምና ፓትሪያርክ መርቆርዮስ አገር ጥሎ በመውጣት ተመሳሳይ ታሪክ እንደተጋሩት ሁሉ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊና ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጳውሎስ እንደ አፄ ቴዎድሮስና አባ ሰላማ በተቀራራቢ ጊዜ በሞት በመለየታቸው ይመሳሰላሉ፡፡ ንግሥት ዘውዲቱና ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማቴዎስም በተቀራራቢ ጊዜ መሞታቸው ይታወቃል፡፡ የዚህ አንደምታው ምን ይሆን? አንድም፣ አንድም፣ አንድም…እየተባለ አንደምታ በብዙ ትርጉምና ምሳሌ ሊገለጽ ስለሚችል ያወያይ ይሆናል፡፡ ባለራዕይነትና የዱላ ቅብብሉን እንደ አንድ ትርጉም ብናይ ግን የችግሮች መነሻ መሆኑን ያመለክተናል፡፡

ቴዎድሮስ፣ ምኒልክ፣ ጣይቱ፣ ዘውዲቱ፣

ኃይሌና ተፈሪ፣ ነጋሶ፣ መንግሥቱ፣

በሥጋ፣ በመንፈስ፣ ባጥንት፣ በጉልጥምቱ፣

እየተቃረኑ፣ እየተቻቻሉ፣ እየተረታቱ፣

አብረው ይኖራሉ - አስረው እየፈቱ፣

ሞቱ እየኖሩ፣ ኖረው እየሞቱ፡፡

ይህ ግጥም “አልን፣ ተባልን፣ አስባልን” በሚል ርዕስ አብርሃም ረታ ዓለሙ በ1998 ዓ.ም ባሳተመው መጽሐፍ ውስጥ ይገኛል፡፡ መሪዎችና ታሪካቸው መቼም እንደማይሞት፤ ያንዳቸው ዘመን ሥራና ተግባር ወደ ቀጣዩ እንደሚሸጋገር የሚገልጹ ሀሳቦችን ይዟል፡፡ የአፄ ቴዎድሮስ አገርን አንድ የማድረግ ራዕይ አፄ ዮሐንስና አፄ ምኒልክ ደክመውለት እውን ሆኗል፡፡ የአፄ ምኒልክ ምኞትና ጅማሬዎች በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን ተሳክተዋል፡፡ ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያም ለ17 ዓመታት ኢትዮጵያን ያስተዳደሩት ከአፄ ምኒልክ ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ መንግሥታት ከልለው ባቆዩትና ባለሙት ቤት መንግሥት ውስጥ ተቀምጠው ነበር፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ህልፈትን ተከትሎ መሪያችንን፣ መንግሥታችንን ሕዝብና አገራችንን አክብረው በሀዘን ሥነ ሥርዓቱ ለመካፈል ከተለያዩ አገራት የመጡ እንግዶችን ያስተናገደው መስቀል አደባባይ (በደርግ ዘመን የተጨመሩ ሥራዎች ቢኖሩም) በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን የተሰራ አደባባይ ነው፡፡ በኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያም ዘመን በቤተመንግስት ግቢ ውስጥ የተሰሩት ሁለት ሕንፃዎች የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጽሕፈት ቤት ሆነው ከማገልገላቸውም በላይ በህልፈታቸው ማግስት ለቅሷቸውን የሚደርሱ ኢትዮጵያዊያንና የውጭ አገር እንግዶችን አስተናግደዋል፡፡

ያለፈው ዘመን መልካም ተግባርና ውጤት ለቀጣዩ እንዲህ ዓይነት ጠቀሜታ ማስገኘት መቻሉ ቢታይም በየዘመናቱ ግን የመንግሥት ወይም የመሪዎች ራዕይ በሕዝቡ ተቀባይነት እያጣ በተቃራኒው ለሕዝብ ፍላጐት መንግሥታቱ ደንታ ቢስ እየሆኑ አገርን የመምራቱ ዱላ ቅብብል በሥርዓት መፈፀም ሳይቻለው ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት አገርና ሕዝብ በጣም ብዙ ተጐድተዋል፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ህልፈት ማግስት ጀምሮ አቶ መለስ ባለራዕይና የሥራ  ሰው ስለመሆናቸው ከተለያዩ አካላት ምስክርነት እየተሰጠላቸው ይገኛል፡፡ ለራዕዮቻቸው ፈር መያዝ ዘመኑ፣ ትውልዱ፣ የሥራ አጋሮቻቸው፣ ሕዝብና ዓለም አቀፋዊ እውነታ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳደረጉላቸው የምንረዳው የቀድሞውን ታሪክ መለስ ብለን ስንመለከት ነው፡፡

የአፄ ቴዎድሮስ ባለራዕይ መሆን ማንም አሌ ብሎ የማያስተባብለው ሐቅ ነው፡፡ ራዕያቸውን የሚረዳ የሥራ ባልደረባ፣ አጋርና ሕዝብ ግን በብዛት ማግኘት አልቻሉም ነበር፡፡ ለለውጥና ዕድገት ሥራ በመጀመሪያ አብረዋቸው የቆሙት አቡነ ሰላማን ጨምሮ ለአፄ ቴዎድሮስ ጉድጓድ የሚቆፍር በመብዛቱ የተነሳ የንጉሡ ራዕይ በአጭር እንዲቀጭ ምክንያት ሆኗል፡፡

ይህንን ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የአገዛዝ ዘመን ጋር በንጽጽር ብንመለከተው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጳውሎስ የአገሪቱ ሰላምና ዕድገት አስተማማኝ መሠረት እንዲኖረው በአሜሪካ ከሚገኘው “ስደተኛው ሲኖዶስ” ጋር እርቅ ለመፍጠር በመትጋት ላይ ነበሩ፡፡ በልጅነታቸው አፄ ቴዎድሮስ ዘንድ የነበሩት አፄ ምኒልክ ንግስናቸው በሰላማዊ የዱላ ቅብብል የተገኘ ነው ባይባልም ከአፄ ቴዎድሮስ ጋር የሚመሳሰለውን ራዕያቸውን እውን ለማድረግ ብዙ ውጣ ውረዶች ማሳለፋቸውን መረጃዎች ያመለክቱናል፡፡የማስፈፀም ስልጣን የነበራቸው የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የተለያየ ፍላጐትና ዓላማ ያለው ሕዝብና የውጭ አገር መንግሥታት ደባና ተንኮል የነገሥታቱ ራዕይ እውን እንዳይሆን እንቅፋት መሆኑ የአፄ ኃይለሥላሴ መንግሥትም የሚጋራው ነው፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በፊት በአባይ ወንዝ ላይ የልማት ሥራ መስራት እንደሚቻል አምነው የመጀመሪያውን የአባይ ድልድይ ያስገነቡት ንጉሡ፤ ደርግ መጥቶ ሥራና ታሪካቸውን ለማጥፋት ብዙ የደከመው ለታሪክ ሽሚያና የዱላ ቅብብሉን በአቋራጭ ለመውሰድ ከመጓጓት በመነሳት ይመስለኛል፡፡ ደርግ በአቋራጭ ያገኘውን ስልጣን ከያዘ በኋላ ንጉሡንና ፓትርያርኩን ጨምሮ የብዙ ዜጐችን ሕይወት እንደዘበት ሲቀጥፍ ያላሰበው ነገር ቢኖር የነገ የእኛ ዕጣ ፈንታስ ምን ይሆናል? የሚለውን ነበር፡፡

በስደትና በእስር የተጠናቀቀውን የደርግ አገዛዝ የተካው የኢህአዴግ መንግሥት ከ21 ዓመት የስልጣን ዘመን በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ህልፈት ተከትሎ ለአገሪቱ አዲስ ሊባል የሚችል ታሪክ ማስመዝገብ ችሏል፡፡ ገዢው ፓርቲ “ምንም የፖሊሲ ለውጥ ሳይኖር በሰላማዊ የስልጣን ሽግግር የታላቁ መሪያችን ራዕዮች እውን ይሆናሉ” ብሏል - በአደባባይ፡፡ ይህ በራሱ፤ ለአገርና ለሕዝብ ለሚጨነቅ ሁሉ፤ ትልቅ ተስፋና መረጋጋት የሚያጐናፅፍ ነው፡፡ አቡነ ጳውሎስ ከ”ስደተኛው ሲኖዶስ” ጋር እርቅ በመፍጠር የአገር ዕድገትና ሰላም ዘላቂ እንዲሆኑ እንደጣሩት ሁሉ አሁንም የጠቅላይ ሚኒስትር ራዕዮች እውን እንዲሆኑ ብቻ ሳይሆን ሁሉም የሚመኘውና የሚጓጓለት ታላቅ አገርና ሕዝብ እንድንሆን ተመሳሳይ ጥረቶች በየዘርፉ መታየት ይኖርባቸዋል፡፡

 

 

 

Read 3090 times Last modified on Saturday, 08 September 2012 12:29