Wednesday, 18 August 2021 00:00

የኳታሩ ሃማድ የአመቱ የአለማችን ምርጥ አውሮፕላን ማረፊያ ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የአፍሪካ የአየር መንገዶች ተጓዦች ቁጥር በ66 በመቶ ቀንሷል


            የኳታሩ ሃማድ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ የ2021 የፈረንጆች አመት የአለማችን ምርጥ አውሮፕላን ማረፊያ ተብሎ መሸለሙን አረብ ኒውስ ዘግቧል፡፡
በአለም ዙሪያ የሚገኙ የአውሮፕላን ጣቢያዎችን በተለያዩ መስፈርቶች እየገመገመ ደረጃ የሚሰጠው ስካይትራክስ የተባለው ተቋም፣ ከሰሞኑም የአመቱን ምርጦች ዝርዝር ይፋ ያደረገ ሲሆን ባለፈው አመት በ3ኛ ደረጃ ላይ የነበረውና በኳታር መዲና ዶሃ የሚገኘው ሃማድ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ዘንድሮ በአንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
በዘንድሮው የአለማችን ምርጥ የአውሮፕላን ማረፊያዎች ዝርዝር ውስጥ የሁለተኛነትን ደረጃ የያዘው የጃፓኑ ቶክዮ ሃኔዳ አውሮፕላን ማረፊያ ሲሆን፣ ሲንጋፖር ቻንጊ አውሮፕላን ማረፊያ ሶስተኛ ደረጃን ለመያዝ ችሏል፡፡
ከአራተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ የያዙትም እንደ ቅደም ተከተላቸው ኢንቼኦን አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፣ ናሪታ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፣ ሙኒክ አውሮፕላን ማረፊያ፣ ዙሪክ አውሮፕላን ማረፊያ፣ የለንደኑ ሄትሮው አውሮፕላን ማረፊያ፣ ካንሳኢ አውሮፕላን ማረፊያ እና ሆንግ ኮንግ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በአመቱ ከፍተኛ የደረጃ መሻሻል ያሳየው የአውሮፕላን ማረፊያ ኢስታንቡል ኤርፖርት መሆኑንና ባለፈው አመት ከነበረበት 102ኛ ደረጃ ዘንድሮ ወደ 17ኛ ደረጃ ከፍ ማለቱንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
በተያያዘ ዜና ደግሞ፣ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ አለማቀፉ የአየር ትራንስፖርት መንገደኞች ቁጥር በ70 አመታት ውስጥ ከፍተኛውን ቅናሽ ባሳየበት የፈረንጆች አመት 2020፣ የአፍሪካ አየር መንገዶች ያጓጓዟቸው መንገደኞች ቁጥር በ2019 ከነበረው  በ66 በመቶ ያህል ቅናሽ ማሳየቱን ዘ ኢስት አፍሪካን ድረገጽ ከሰሞኑ ባወጣው ዘገባ አስነብቧል፡፡
የአፍሪካ የአየር መንገዶች በ2019 ያጓጓዟቸው መንገደኞች ቁጥር 95 ሚሊዮን ያህል እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ በ2020 የፈረንጆች አመት ግን ይህ ቁጥር በ65.7 በመቶ ያህል በመቀነስ ወደ 34.3 ሚሊዮን ዝቅ ማለቱን አመልክቷል፡፡
የአፍሪካ አየር መንገዶች በአመቱ በድምሩ 10.21 ቢሊዮን ዶላር ያህል ገቢ ማጣታቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ አለማቀፉ የአየር መንገደኞች ገቢም በ69 በመቶ ያህል ቅናሽ ማሳየቱንም አመልክቷል፡፡
የኮሮና ወረርሽኝ በአለማቀፍ ጉዞዎች ላይ የፈጠረው ቀውስ እጅግ ከፍተኛ እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ የአለማቀፍ የአየር መንገደኞች ቁጥር በአንጻሩ በ2019 ከነበረበት 4.5 ቢሊዮን በ60.2 በመቶ ያህል በመቀነስ ወደ 1.8 ቢሊዮን ዝቅ ማለቱንም አክሎ ገልጧል፡፡


Read 7783 times