Print this page
Saturday, 14 August 2021 13:57

ክፋት በዛብን

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

   "በተፈጠረው ችግር ከቀያቸው ተፈናቅለው ነፍሳቸውን ለማትረፍ የመጡ ሰዎች አሉ ተብሎ የቤት ኪራይ በእጥፍ መጨመር ምን አይነት ክፋት ነው! ሰው ችግር ውስጥ መግባቱን እያዩ በሌላው ሰቆቃና ስቃይ ለማትረፍ የሚፈልጉ ምን አይነት ፍጡራን ናቸው!--"
             


            እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ… ይሄ የሸመታው ምናምን ነገር ምን ብናደርግ ይሻለናል! ግራ ገባን እኮ! አሁን ሸመታ ደርሰን ስንመለስ… “እነኚህ ስግብግቦች ኪሎ አስር ብር የነበረውን ቲማቲም፣ አስራ አንድ ብር ያስገቡብን!!” ብለን ለአንዲት ብርና ለብር ከሀምሳ ጭማሪ ‘መነጫነጭም’ ሊናፍቀን ነው፡፡ ልክ ነዋ…ሲጨንቅ እኮ መጣ ብላ ሄድ የምትል ‘ንጭንጭ’ ትናፍቃለች...ትልቀኛው አንጀት ውስጥ ገብታ አትቀረቀርማ!  በቃ ‘ሽው፣ ሽው!’ ነው፡፡ ዘንድሮ ልጄ ገበያ ደርሰን ስንመለስ በንጭንጭ ብቻ የምንገላገለው አልሆነም፡፡ ከትናንት ወዲያ ሀምሳ ብር የገዛችሁት እቃ ዛሬ ሰማንያ ብር ሲሆንባችሁ ‘ንጭንጭ’ ብሎ  ነገር የለም። ለንጭንጭም ቢሆን እኮ መጀመሪያ አእምሮ በሚገባ ማሰብ መቻል አለበት፡፡
እናማ....አሁን ገበያ ደርሰን ልክ ደጃፋችንን ተራምደን ስንገባ መጀመሪያ የሚታየን ነገር በቅርብ ያለ ሶፋም ይሁን ምናምን ላይ በደረታችን መወርወር ነው። እያንዳንዷ ተጨማሪ ብር አንድ፣ አንድ ዱላ ነቻ! ወገባችን በወይራ ሽመል ሲቀነደብ የዋለ ይመስላላ!
ክፋት በዛብን!
“አንተ! ምን ሆነህ ነው እንደሱ የተዘረጋጋኸው?”
“ኑሮ፣ ኑሮ ነው የዘረጋጋኝ፡፡”
“ጀመረህ እንግዲህ...ገበያ ሄደህ ምንም ነገር ሳትገዛ ባዶ እጅህን ተመለስክ እንዴ!“
“እሱ ባዶ እጅ ነው!“ (ይቺ ደግሞ…ለራሴ ወገቤ ሲቆመጥ ውሏል፣ ጭራሽ ትጨምርልኛለች እንዴ!)
“ምኑን ነው የምትለኝ?”
“እዛ ሶፋው ስር ያለው ምንድነው! ዓይን የለሽም እንዴ!” (“ማንን ታሸንፋለህ ቢሉት ሚስቴን አለ፣; የተባለው እኮ ዝም ብሎ አይደለም!) ፌስታሏን በሁለት ጣቷ ብድግ አድርጋ አየት ታደርጋታለች፡፡
“አፈር በበላሁ!”
ሴትየዋ ጤና የላትም እንዴ! ታዲያ አፈር መብላት ካማራት ራሷን ትቻል እንጂ እኔ ወገቤን ተቆርጬ ከሸመትኩት ጋር ማያያዝ ምን ማለት ነው! እኔ ሩብ ፌስታል ለማይሞላ እቃ የገፈገፍኩት ሁለት መቶ ሠላሳ ብር የነርቭ ስርአቴን አዛብቶት እያለ… እሷ ተጋድማ ውላ….ብቻ ይቅር! አሀ…የሆዴን ካወቀች የመልስ ምቱን አልችለውማ!
ስሙኝማ…ክፋታችን እኮ ልክ አጣ! የስግብግብነታችን ቀይ መሰመር ምኑ’ጋ እንደሆነ መገመት እንኳን አስቸጋሪ ሆነብን!
በተፈጠረው ችግር ከቀያቸው ተፈናቅለው ነፍሳቸውን ለማትረፍ የመጡ ሰዎች አሉ ተብሎ የቤት ኪራይ በእጥፍ መጨመር ምን አይነት ክፋት ነው! ሰው ችግር ውስጥ መግባቱን እያዩ በሌላው ሰቆቃና ስቃይ ለማትረፍ የሚፈልጉ ምን አይነት ፍጡራን ናቸው!
የፍልሰታ ጾም ዋዜማ ሐሙስ ዕለት ምን ቢሆን ጥሩ ነው… በብዙ አካባቢዎች ዘይት ድራሹ ጠፋ! ብዙዎች ደብቀውት ነበር ማለት ነው፡፡ እንደውም አሁንማ ከተማችን ውስጥ ሦስትና አምስት ሊትር ዘይት አንጠልጥለው እየዞሩ ‘ዘይት ፈላጊ’ የሚሉ ሰዎች ተፈጥረዋል፡፡ ስግብግብነት ገና ጉድ ያሳየናል!
የምር ግርም ይላል… እንደዚህ የሚያደርጉት የንግድ ሰዎች እነሱ ቤተሰብ የሌላቸው ይመስል፣ ወንድም እህት፣ ዘመድ አዝማድ የሌላቸው ይመስል፣ ሚስት ባል የሌላቸው ይመስል፣ ልጆች የሌላቸው ይመስል! እየተደረገ ያለው እኮ ‘የገበያ ስትራቴጂ’ ሳይሆን ሊገልጸው የሚችለው አንድ ቃል ብቻ ነው... ጭካኔ! እስቲ ወደ ሸመታ…
“ጤና ይስጥልኝ…”
የጎንዮሽ ያየኛል፡፡ በሆዱ… አለ አይደል… “ይሄኔ ከገቢዎች ሊሰልለኝ የመጣ ይሆናል!” ብሎ እንዳያስብ ያው ያፈጠጡት የ‘ማልኒዩትሪሽን’ ምልክቶች ከተጠርጣሪነት ‘ያድኑኛል!’ በቃ ልክ እንደሌለሁ ሁሉ (‘እንዳልተፈጠርኩ ሁሉ’ ማለትም ይቻላል…) እቃ እያነሳ ያነሳበት እዛው ቦታ መልሶ ያስቀምጣል፡፡ ለ“ጤና ይስጥልኙ” ምላሽ መሆኑ ነው፡፡ እኛም አይገደን፣ እንደዛም እያደረጉን ነገም፣ ከነገ ወዲያም “ጤና ይስጥልኝ…” ማለቱን አንተውም…‘ቢቆጥርልን’ ብለን!
“ዘይት  ፈልጌ ነበር…”
“ዘይት አልቋል፡፡”
ውይ ትእቢት! ውይ ትእቢት! “ባይበላስ ቢቀር!” የሚያሰኝ አይነት ትእቢት አለ አይደል! ፊት ለፊታችሁ እኮ የዘይት ጠርሙሱ መለስተኛ ግንብ መስሎ ተደርድሯል!
“እዛ ጋ የተደረደረው ዘይት አይደለም እንዴ!” (እኔ የምለው እዛው ፍጥጥ ብሎ እየታየ “አልቋል” ብሎ ነገር ምን አይነት ቅሽምና ነው! ስሙኝማ…. ልታታሉልን መሞከራችሁ ካልቀረ ምናለ ትንሽ ‘ክሬቲቭ’ ብትሆኑ! 
“እሱ ለደንበኞች የተቀመጠ ነው፡፡”
“ምናለ  ብትሸጥልኝ!”
“ነገርኩህ እኮ፣ እሱ የደንበኛ ነው፡፡ ደግሞም ተከፍሎበታል፡፡“
“እባክህ የእኔ ወንድም ተባበረኝ። ቤተሰቤ ተቸግሮብኝ ነው፡፡” አሰብ ያደርጋል፡፡
“ለአንተ ስል ስምንት መቶ ብር ውሰደው!”
“ስምንት መቶ ብር! ለአምስት ሊትር ዘይት!”
“የደንበኞቼን ነው እኮ አንስቼ የምሰጥህ። ስላሳዘንከኝ ነው እንጂ ለማንም አልሸጥም ነበር፡፡” ስላሳዘንከኝ! በቃሪያ ጥፊ ቢያጮላችሁ እንኳን ህመሙ የዚህን ያህል አይሰማችሁም፡፡ ‘ስላሳዘንከኝ!’ 
“አሺ አምስት መቶ ሀምሳ ብር ልክፈል፡፡” ግስላ ይሆንባችኋል፡፡
“እንደውም አልሸጥም፡፡ አሁን ሥራችንን እንሥራበት ውጣልን!”
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ነገሬ ብላችሁልኛል…አንድ ሰው ብቻ እያለም ‘እኛ’ እያሉ የሚያወሩ ባለሱቆች ብዙ ናቸው፡፡ እኔ የምለው… ፊውዳሊዝም በየት በኩል ሰርስሮ ነው ሱቆች ውስጥ የገባብን! ቂ…ቂ…ቂ…
የምር ግን… ይህን ያህል ክፉዎች ነበርን እንዴ! የትርፍና የኪሳራ ጉዳይ ሳይሆን...አለ አይደል... በቃ ቅልጥ ያለ ክፋት! በሰው ችግር መደሰት!
በመሥሪያ ቤት ቢሆን ያስቸገሩን ትልቅዬም፣ ትንሽዬም አለቆችን በሆዳችንም ቢሆን “ሁልሽም የመዋቅር ጊዜ ታገኛታለሽ!” ምናምን ማለት እንችላለን። …ነጋዴዎችን ግን “የመዋቅር ጊዜ ታገኛታለሽ!” አንላቸው ነገር! “ገቢዎች ልክ ያገባልኛል!” አንል ነገር  ሲገቡ አናይ! ግን፣ ለምን ይዋሻል እንረግማቸዋለን! (እስካሁን ግን ገና ጉዳያችን ለውሳኔ አልቀረበም መሰለኝ!)
ምንም ጥፋት ሳትፈጽሙ ወይንም አጉል ባህሪይ ሳታሳዩ ዝም ብሎ ስለደበራችሁት ብቻ አላሳልፍም ብሎ የሚከለክል የጥበቃ ሠራተኛ በቃ ‘ክፉ’ ነው፡፡
“እባክህ በጣም አስቸኳይ ጉዳይ ነው ያለብኝ! ዛሬን ካለፈኝ ህይወቴ ይበላሻል፡፡”
“ሰውዬ፣ ሥራችንን እንሥራበት ዘወር በልልን!” (እዚህም ፊውዳሊዝም ሹልክ ብሎ ገብቷል ማለት ነው!)
በተለይ ደግሞ ምን መሰላችሁ… “ችግር ገጥሞኝ ነው፤” “እባክህ የእኔ ጌታ፣” “እባክሽ የእኔ እመቤት” ካላችሁማ ክፋቱ ይብስባቸዋል፡፡
እናም...ክፋት በጣም በዝቷል፡፡
“ስሚ እንትና የሆነችውን ሰማሽ?”
“አልሰማሁም፣ ምን ሆነች?”
“ከሥራ ተቀነሰች አሉ፡፡”
“ጎሽ፣ ዋጋዋን ሰጡልኝ!”
“መሀላችሁ ችግር አለ እንዴ!”
“ምን አገናኝቶን?”
“ታዲያ ምን አደረገችሽ? ለምንድነው ዋጋዋን ሰጡልኝ ያልሽው?”
“በቃ አልወዳትም፡፡ ሳያት ደሜ ነው የሚፈላው!”
ከፋት በዛብን!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1623 times