Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 08 September 2012 12:20

“ከሀገሩ የወጣ ሀገሩ እስኪመለስ…”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

“ፈረንጅ ሃገር ሳትሄድ ገና እዚሁ ሳለህ፤

የገባኸውን ቃል ለምን ታፈርሳለህ”

“ኑሮ በባዕድ ሀገር” የተሰኘው - በብርሃኑ ሠርፁ የተፃፈው መጽሐፍ ስለስደትና ስለ ስደት ምክንያቶች የሚከተለውን ይላል፡፡ ቁንጨብ ቀንጨብ አድርገን እንየው:-“የጽሑፉ ዓላማ በሕጋዊውም ሆነ በሕገ ወጥ መንገድ ከሀገራቸው ወጥተው፤ በአብዛኛው በዩናይትድ ኪንግደም፤ በልምድ እንግሊዝ ተብላ በምትታወቀው ሃገር፤ በአሜሪካና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በዓረብ ሀገሮች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ኑሮ ምን እንደሚመስል ያየሁትን፤ ያጋጠመኝንና በስሚ ስሚ የሰማሁትን ጭምር፤ ከሁሉም ጋር፤ በተለይም የአብዛኛውን ኢትዮጵያውያን የባዕድ ሀገር ኑሮ በደንብ ከማያውቀውና፤ “ፈረንጅ ሀገር ስሄድ ቀይ ምንጣፍ ተነጥፎ ይጠብቀኛል፤ አስፋልቱም ወርቅ የተነጠፈበት ነው፤” ብሎ ከሀገሩ በተገኘው ዘዴ ለመውጣት ከአኮበኮበው ኢትዮጵያዊ ጋር ለመካፈልና፤ በየባዕድ ሀገሩ ያለውም ኢትዮጵያዊ፤ ምንም እንኳን ሀገር ቤት ገብቶ ሲዘባነንና ሲዝናና ሲታይ የደላው መስሎ ቢታይም፤ ዕውነተኛው ሕይወቱ ግን ምን እንደሚመስል በመጠኑም ቢሆን ለማሳየት ነው፡፡ ያቀረብኩላችሁ ገጠመኞች በአብዛኛው የእንግሊዝ ሀገር ልምዴን ያካተቱ ሲሆኑ በመጠኑ ደግሞ በአሜሪካና በአረብ ሃገሮች የሚገኙ ወገኖቻችንንም ኑሮ ዳበስ የሚያደርጉ ናቸው” ይላል ደራሲው፡፡

ውጭ ሀገር ወይም ፈረንጅ አገር (በዱሮ ስሙ) ምን ማለት ነው? የሚለውን በቀላሉ ሲገልፀው፤ “የሌላ ሰው ሀገር፤ በሀገራችን አጠራር “ፈረንጅ አገር”፤ “ባሕር ማዶ” ወይም “ውጭ ሀገር” እየተባለ ይጠራል፡፡ ታዲያ እያንዳንዱን ቃል ብንመለከተው፤ ባሕር ማዶ የሚለው ባሕር ማቋረጥን ስለሚያካትት ኬንያ፤ ጅቡቲ፤ ጋና ወይም ናይጄሪያ የሄደው ባሕር ስላላቋረጠ ውጭ አልሄደም ማለት ነው? በተለምዶ ደግሞ ፈረንጅ የምንለው ቆዳው የነጣውን ስለሆነ ቻይናው ዘንድ ወይም ህንዱ ሃገር የሄደውስ ምን ሊባል ነው ተብሎ ነው መሰለኝ፤ አሁን አሁን በተለይ የተሄደበት ሀገር ስም በግልጽ ካልተጠቀሰ በስተቀር በአብዛኛው የምንጠቀመው፤ “ውጭ ሀገር” የሚለውን ቃል ነው፡፡ በእርግጥ ብዙዎቻችን ትንሽም ጉራ ብጤ ስላለብን፤ የቤተሰቡ አባል ወደ አሜሪካ ወይም ወደ አውሮፓ የሄደ እንደሆን ነው እንጂ በአፍ ሙሉ “ልጄ፤ ወንድሜ፤ እህቴ አሜሪካ፤ ካናዳ፤ ፈረንሳይ፤ እንግሊዝ ሄዷል/ሄዳለች፤” እየተባለ የሀገሩ ስም ተጠቅሶ የሚወራው፤ በየዓረቡ ሀገር የተበተኑትን ቤተሰቦቻችንን ስናነሳ በደፈናው “ውጭ ሄዷል፤ ውጭ ሄዳለች” ብለን ነው የምናወራው፤ ምክንያቱም ሕይወታቸውንም፤ አኗኗራቸውንም፤ ሥራቸውንም ጠንቅቀን ስለምናውቅ እያፈርንበት መሰለኝ፡፡” ሰው ሁሉ አምስቱን ዓመት ሙሉ ቤተሰቦቿን “ያቺ ልጅ ደህና ናት? ወሬዋን ትሰማላችሁ? ለመሆኑ የት አገር ነው ያለችው?” እያለ ሲያደርቃቸው ለነበረው ሰው ሁሉ “ደህና ናት፤ ውጭ ነው ያለችው፤” ሲሉ የነበሩት የቤተሰቦቿ አባላት ሁሉ ገና “ያቺ ልጅ ደህና ናት?” ተብለው ሲጠየቁ ገና እንግሊዝ ከገባች ወር ሳይሞላት ተሽቀዳድመው “ደህና ናት፤ እሷኮ እንግሊዝ አገር ነው ያለችው፤” ማለት ጀምረው ነበር፡፡ ዓረብ ሀገር በነበረችበት ሃገር ስም ሳይጠቀስ ኖሮ አውሮፓ ስትገባ ነበር ያለችበትን ሀገር መግለጽ የጀመሩት፡፡

…ምናልባት እንዲህ እንዳሁኑ ዘመን ወደ ሦስተኛው ዓለምና ወደየአረቡ ሀገር ኢትዮጵያውያን ሴቶቹ ለግርድናና ለዝሙት ሥራ፤ ወንዱ ደግሞ ለጉልበት ሥራ መሰደድ አልጀመረ ስለነበርና የሚሄደው እዚያው ፈረንጅ ሀገር ለትምህርት ብቻ ስለሆነ ሊሆን ይችላል የፈረንጅ አገር ይባል የነበረው፡፡ እንዲያውም የቀድሞው የክብር ዘበኛ ባንድ ዝነኛ ድምጻዊት የነበረችው ብዙነሽ በቀለ

“ፈረንጅ ሃገር ሳትሄድ ገና እዚሁ ሳለህ፤

የገባኸውን ቃል ለምን ታፈርሳለህ” እየለች የምታንጐራጉረው ዘፈን ነበራት፡፡

ዱሮ ዱሮ ልጆች በነበርንበት ዘመን ሰዎች ለትምህርት ወደ ውጭ ሀገር ይላኩ ነበር፡፡ ከዚያም ሲመለሱ፤ እንዲህ እንዳሁኑ ዘመን በድንች አላላጥም፤ በአበባ አቀማመጥም፤ በመፀዳጃ ቤት መጠጣም ዲግሪ አገኘሁ የማይባልበትና ምሁር ተብዬ የበዛበት ዘመን ስላልነበረ፤ በተወሰኑና ለሀገር ይጠቅማሉ ተብለው በመንግሥት ደረጃ በተመረጡ ሙያዎች ፈረንጅ ሃገር ሄደው ተምረው የሚመለሱ ሁሉ ደህና የሥራ ቦታና ኃላፊነት እንደሚሰጣቸው እናይና እንሰማ ነበር፡፡ በተለይ በንጉሡ የአገዛዝ ዘመን፤

…“ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በዛሬው ዕለት ለትምህርት ወደ ውጭ የሚላኩ ተማሪዎችን በቤተ መንግሥት ተቀብለው አሰናብተዋል፤” ወይም “ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በዛሬው ዕለት ከውጭ ሀገር ትምህርታቸውን አጠናቀው የተመለሱ ተማሪዎችን ተቀብለው፤ በተማሩት ሙያ ያስተማረቻቸውን ሀገራቸውን በቅን እንዲያገለግሉ መሪ ቃል ሰጥተዋል” የሚል ነበር፡፡ እንዲህ እንደጐርፍ መፍለስ ስላልነበረና የሚሄዱትና የሚመለሱት ሰዎችም በጣት የሚቆጠሩ ብርቅዬዎችና በመንግሥት ለትምህርት የሚላኩ በመሆናቸው፤ ንጉሡ እንኳን ጊዜ ኖሯቸው ተማሪ ይቀበሉ፤ ይሰናበቱና ሀገራቸውን እንዲያገለግሉም አደራ ይሉ ነበር፡፡

በንጉሡ ዘመን ንጉሡን ሳይሰናበቱ መሄድና መመለስ የተጀመረው (American Field Service)   የሚባል  አሜሪካኖች በወቅቱ ከባላንጣቸው ከሶቭየት ሕብረት ጋር ዓለምን እኔ እገዛ እያሉ በሚፎካከሩበት ዘመን ያስተዋወቁት ፕሮግራም ሲጀመር ነበር፡፡ ጐበዝ ናቸው የሚባሉ ተማሪዎች አስራ አንደኛን ክፍል ካጠናቀቁ በኋላ ለአንድ ዓመት ወደ አሜሪካ ተልከው ሲማሩ ይቆዩና ሲመለሱ፤ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና፤ በልምድ ማትሪክ የሚባለውን ፈተና፤ ሳይፈተኑ በቀጥታ ዩኒቨርሲቲ መግባት ይፈቀድላቸው ነበር፡፡

…ሁሉም ባይሆኑም፤ አንዳንዶቹ በጣም ያበዙት ነበር፡፡ በቀልድ መልክ ሳይሆን የምራቸውን ንግግራቸውን ለውጠው “በጨለማ ስሄድ ቀኝ እግሬን እንቅፋት መታኝ፤” ለማለት “ከቸለማ ስሄድ ከኝ እግሬን እንክፋት መታኝ፤” ይሉ ነበር፡፡ አንዳንዶቹማ ከልጅነት እስከ ዕውቀት የኖሩበትን እርምጃቸውን ሁሉ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለውጠው ሲራመዱ እንደ ኳስ እንጣጥ እንጣጥ ይሉ ነበር፡፡

…ከፍተኛ የኢትዮጵያውያን ፍልሰት ወደ ባዕድ ሀገር የተጀመረው ደርግ ሥልጣን ላይ ከወጣበት ዘመን ጀምሮ ነው፡፡ ደርጉ ሥልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ የቀድሞ ባለሥልጣናትን፤ ልጆቻቸውን ከዚያም በፖለቲካ ምክንያት የተቃወሙትን ሁሉ ወንዱ፤ ሴቱ፤ ወጣቱ፤ ሽማግሌው ሳይቀረው ሲያስር፤ ሲገርፍ፤ ሲገድል፤ ለነፍሱ የሳሳው ሁሉ፤ “ከመሞት መሰንበት” ብሎ ሽሽት ጀመረና ፍልሰት ተማረ፡፡

…አንድ ጊዜ ተሰባስበን የባሕሩ ቀኜን ዜማዎች ስናዳምጥ፤

“አባት የሞተ እንደሁ ባገር ይለቀሳል፤

እናትም ብትሞት ባገር ይለቀሳል፤

እህትም ብትሞት ባገር ይለቀሳል፤

ወንድም የሞተ እንደሁ ባገር ይለቀሳል፤

ሀገር የሞተ እንደሁ ወዴት ይደረሳል?”የሚለውን ግጥም የሰማ አንድ አሿፊ ወንድሜ “ተው እባክህ ይሄ ዱሮ ቀርቷል፤ በዘመናዊውም ጊዜ ጐረቤት ሃገርም ቢሆን ተሄ

ዶ ይለቀሳል፤” ያለውን ሳስታውስ፤ ራሳችን ከደላንና ከተመቸን ሀገር የሚለውን ስሜት እያጣን እየሄድን ይመስለኛል፡፡

ታዲያ አልፎ አልፎ ተገናኝተን ያን ጊዜ የተናገረውን ሳነሳበት፤ “ይሄውልህ ጐረቤት ሃገር ሆኜ ከማልቀስ ተገላግዬ ራቅ ብዬ ተቀምጬ ለሞተችው ሀገሬ እያለቀስኩላት ነው፤” ይላል፡፡

አብዛኛው ወጥቶ የአውሮፓንና የአሜሪካኑን ኑሮ ድሎት የለመደ ስለሆነ ተመልሶ መጥቶ፤ ሌላ ሌላው ቢቀር ጥሩ የመኖሪያ ቤት፤ የማይቋረጥ የውሃና የኤሌክትሪክ አገልግሎት እያገኘ መኖር ስለሚፈልግና፤ ዳጐስ ያለ ገንዘብ ይዞ ተገብቶ የራስ የውሃ አቅርቦትና አነስተኛ የኤሌክትሪክ ጄኔሬተር ከሌለ በስተቀር፤ እንደዚህ ዓይነቶቹ አገልግሎቶች፤ ከተሟላላቸው ከበርቴዎች በቀር በስመ ኢትዮጵያዊ ሁሉም በመብትነት የሚያገኛቸው ስላልሆኑ፤ የሚያሳድደው መንግሥት ቢወድቅም፤ ተመልሼ ሄጄስ እንዴት ሆኜ ልኖር ነው እያለ ወደ ድሎቱ አደላና እንደወጣ ቀረ፡፡

…አሉ የሚባሉት የመንግሥት ሆስፒታሎች በመድሃኒት እጥረት ተወጥረው፤ የሕሙማኑ ቤተሰቦች በግላቸው መድሃኒት በከፍተኛ ዋጋ ከግል የመድሃኒት መሸጫዎች ገዝተው እንዲያቀርቡ እንደሚጠየቁ ሲሰማ ወሬው አስበርግጐት ይሸሻል፡፡

…ሌላው ደግሞ ያችኑ በባዕድ ሀገር፤ ሌት ተቀን ያለ ዕረፍት ሁለትና ሦስት ሥራ ሠርቶ፤ ያጠራቀማትን ገንዘብ ይዞ ወደ ሃገር ቤት ገብቶ እሷኑ እየመነዘረ እስከ ዕለተ ሞቱ አብቃቅቶ ለመኖር ይወስንና፤ በአንድ በኩል አንዱ ዶላር በአስራ ስድስት የኢትዮጵያ ብር፤ አንዱ ፓውንድ ደግሞ በሃያ አምስት የኢትዮጵያ ብር እንደሚመነዘር ሰምቶ፤ ያጠራቀመውን የውጭ ሀገር ገንዘብ በኢትዮጵያ ብር ምንዛሪ ሲያሰላው፤ የትዬለሌ ነው ብሎ ደስ ይለውና፤ እንዴት ሀገሩ ገብቶ፤ በወር ምን ያህል እያጠፋ ያለ ችግር እንደሚኖር ዕቅድ አውጥቶ ወደ ሀገሩ ለመመለስ ይወስናል፡፡ ግን ያ የዛሬ ስንት ዓመት በስሙኒ ሰባት እንቁላል፤ በስልሳ ሳንቲም አንድ ኪሎ ስኳር፤ በአርባ ብር አንድ ኩንታል ሰርገኛ ጤፍ በሃያ ብር በግ፤ በሁለት ብር ዶሮ፤ በአምስት ብር ኪሎ ቅቤ፤ በሁለት ብር ሊትር ዘይት ሲገዛና የዶሮ ዋጋ ከሳንቲሞች ዘልሎ አንድ ብር በመግባቱ፤

“ጋሼ ማረኝ ማረኝ፤ ጋሼ ማረኝ ማረኝ፤

ዶሮ ብር አወጣች እኔ ስጋ አማረኝ፡፡”

ተብሎ በተዘፈነበት ዘመን ሀገሩን ጥሎ የወጣ ሰው፤ ሂሳቡን የሚያሰላም “ያኔ እኔ ከሀገር ቤት ስወጣ፤ ዋጋው ይሄ ስለሆነ፤ አሁን ግፋ ቢል እጥፍ ቢሆን ነው፤” ብሎ ነው፡፡

ሆኖም ሒሳቡን ሲያሰላው፤ ያ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ሀገሬ ላይ  አንደላቆ ያኖረኛል ብሎ ያሰበው ገንዘብ ቅቡጭ ብሎ ከሦስትና ከአምስት ዓመታት በላይ እንደማያኖረው ሲያውቅ፤ ያለበት ሃገር ኑሮ የተሻለ ሆኖ ስለሚያገኘው ሀገሩ ለመመለስ እንደጓጓ ይቀራል፡፡

ብዙው ስደተኛ ደግሞ በሄደበት ሃገር ተደላድሎ ንብረት አፍርቶ ልጆች ወልዶ፤ ልጆቹ ጭራሽ ፈረንጆች ሆነው ለሀገራቸው ቋንቋና ባሕል እንግዳ ሆነው ሲያያቸው “ከአሁን ወዲያ ገብቼስ ምን አደርጋለሁ? እዚሁ የልጆቼን ዕድገት እያየሁ ድሬና ኩዬ ሞቴን ልጠብቅ እንጂ፤ ሀገር ቤትስ ሄጄ ከአሁን ወዲያ ምን አደርጋለሁ! ብሎ ተስፋ ቆርጦ እንደወጣ ይቀራል፡፡ ታዲያ ልቢቱ ሁልጊዜ ሃገር ቤት ናት፡፡

ታዲያ ብዙው እንዲሁ እንዳለ ነው ዕቅዱና አፈጻጸሙ ሳይገናኙ የሚሞተው” ይላል፡፡

(“ምኞቴ እንደጉድፍ ወድቃ፣ ተስፋዬ እንደጉም መንጥቃ

የወንድሜን ልጆች እንኳ ለርስታቸው ሳላበቃ፤

የእኔ ነገር በቃ  በቃ” (ፀ ገ መ “የከርሞ ሰው”) እንዳለው ነው!)

…እናም ዕድሜው ከገፋ በኋላ ከሃገሩ ወጥቶ በሰው ሀገር ተበትኖ የሚኖረው የዘመኑ ትውልድም እንደዚሁ አንድ ቀን ሀገሬ እገባለሁ እንዳለ ነው ኖሮ የሚያልፈው፡፡ ልጆቹ ግን ወደ ወላጆቻቸው ሃገር የሚሄዱት እንደ ሀገር ጐብኚ ማለትም ያባታቸውን ወይም የእናታቸውን ሃገር ለማየት እንጂ እዚያው ተደላድለው ለመኖር አይደለም፡፡ ምክንያቱም ያ የወላጆቻቸው ሃገር እንጂ የእነሱ ሆኖ አይሰማቸውም አይታያቸውምም፡፡

…ያደግንበት አካባቢና ሁኔታ፤ እንኳንስ ሌላ ቀርቶ መጥፎ ብለን የምናስበውን ነገር እንኳን እንድናስታውስ የሚያደርግ ልዩ መስህብና ኃይል በውስጣችን ጥሎ የሚያልፍ ይመስለኛል፡፡ ታዲያ ያ መስህብ ለዚያው በውስጡ ላለፈ ግለሰብና ቡድን እንጂ፤ በዚያ ውስጥ ላለፈ ግለሰብ ምንም መስሎ ካለመታየቱም በላይ አንዳንድ ጊዜ እንዲያውም “አሁን ይሄ ምን ጥሩ ነገር ሆኖ ነው ትዝታ ጥሎበት የሄደው?” የሚያሰኝ ነው፡፡

አባቶቻችንን፤ እኛ ልጆቻቸው “አሁን መገራረፍና የጫካ ፍራፍሬ መልቀም ምን ጥሩ ነገር ሆኖ ነው እንደዚህ በትዝታ የሚያወሩት?” ብለን ታዝበን እንዳላለፍናቸው ሁሉ፤ እኛም የአባትነት ወግ ደርሶን ለልጆቻችን በልጅነት ዘመናችን ስላሳለፍነው “ፓስቴ መብላት፤ ብይ መጫወት፤ ቡሄ መጨፈር፤ ለእንቁጣጣሽ ለዘመድ አዝማድ አበባ ሰጥተን ገንዘብ መሰብሰብ” ትዝታ እያነሳን “የልጅ ለዛ ዱሮ ቀረ” እያልን ስናወራቸው፤ እነሱም በተራቸው “አሁን ይሄ ምን ደስ የሚል ነገር ሆነና ነው ትዝ የሚላችሁ?” ይሉናል፡፡ ግን የአሁኑ ዘመን ልጆች ከኛ ዘመን ልጆች የሚለዩት፤ እኛ የሚሰማንን በግልጽ አውጥተን መናገር እንፈራ ስለነበር ወላጆቻችንን ስለሚያወሩልን የልጅነት ታሪካቸው ታዝበን ዝም ስንል፤ የእኛ ልጆች ግን በግልጽ የመናገር ነጻነቱን የተጐናፀፉ ስለሆኑ የኛን ዘመን አሁን እነሱ ካሉበት ዘመን ላይ ቆመው እየተመለከቱ “እንዴት ፓስቴ ትበሉ ነበር? እንዴት እንደዚህ ዓይነት ጨዋታ ትጫወቱ ነበር?” ብለው፤ ትዝታችንን ያጣጥሉብናል፡፡

የጣና አዳራሽን ያየ ወንድሜ “አይ!! እኔ መርካቶ ስልህ አንተ ስትገባ ሌላው ሲወጣ፤ ወይም አንተ ስትወጣ ሌላው ሲገባ እየተላተምክና እየተገፋፋህ፤ አንዳንዴም ምነው ሰውዬ ዓይን የለህም እንዴ? እየተባባልክ፤ ገበያተኛ በተሸከመው ዕቃ እየጐሸመህና ዓይንህን እየጠነቆለህ የሚገበያይበትን ገበያ አልኩህ እንጂ፤ ይሄ “መውጫ ብቻ”፣ “መግቢያ ብቻ” የሚለውማ እዚያ እፈረንጁ ሀገር የሰለቸኝ ነው!!” ብሎ እምቢ ብሎኝ ጣና ገበያን ሳይጐበኝ ተመልሷል፡፡

…ጉልበተኞች በሚገዙት ሀገር እኮ መፈታት ነው እንጂ ከባዱ ነገር፤ መታሰርማ ማንኛውም የመንደር ሹም ሁሉ ሊፈጽምብን የሚችለው ነው፡፡

ታዲያ መቼም የደርግ ዘመን እስረኛ ሁሉ የሚያስታውሰው ነገር ነው፤ በየጊዜው የእስረኛ ቆጠራ ይካሄዳል፡፡ ፎርም ይቀርብና ስም፤ ዕድሜ፤ የታሰርክበት ቀን፤ የታሰርክበት ምክንያት፤ ያሰረህ ባለሥልጣን፤ የሚለው ሲመጣ ይሄ ወጣት ሁልጊዜ የሚለው “የታሰርኩበት ምክንያት የትራፊክ መንገድ ዘግቼ ሲሆን፤ ያሰሩኝ ሰውዬ ግን ማንና ምን እንደሆኑ አላውቅም” ነበር፡፡

እንግዲህ በአንድ ትውልድ ብቻ፤ ደርግ ሥልጣን ላይ ሲወጣ የንጉሡ ባለሟሎችና ደጋፊዎች የነበሩና ደርግን እንቃወማለን ብለው የተነሱ የተለያዩ ሕቡዕ ድርጅቶች አባላትና ደጋፊዎቻቸው፤ እንዲሁም የደርግ ደጋፊዎችና አጫፋሪዎች የነበሩና በኋላ ከደርግ ጋር የተኮራረፉ፤ አሁን ያለው መንግሥት ሥልጣን ላይ ሲወጣ ደግሞ የደርግ ደጋፊዎች የነበሩና አንዳንድ የደርግ ተቃዋሚ ቢሆኑም ካለው መንግሥት ጋር ግን የማይስማሙ ድርጅቶች አባላት፤ ደጋፊዎችና አጫፋሪዎች የነበሩ የፖለቲካ ድርጅት አባላትና ደጋፊዎች ስደት ስለጀመሩ፤ ባለፉት አርባ ዓመታት ውስጥ በተከሰተው የፖለቲካ ውጣ ውረድ ምክንያት የደስተኛው ቁጥር እየናረ ሄደ፡፡

ከፖለቲካው ምክንያት ሌላ ኢትዮጵያውያንን ከሀገራቸው እንዲሰደዱ ያደረጋቸው ትልቁ ምክንያት ደግሞ የኢኮኖሚ ችግርና፤ ቀደም ሲል ሕዝቡ በኑሮው ውስጥ የነበረው መስፈርት (ቫልዩ)፤ ሁሉ ተለውጦ የሁሉም ነገር መለኪያ ገንዘብ መሆኑ ነው፡፡ ቀደም ሲል አንድን ሰው በትምህርቱ፤ በዕድሜው፣ በፀባዩ፤ ለሀገርና ለህብረተሰቡ ከሚያበረክተው አገልግሎት አንጻርና በቁም ነገሩ እናከብር የነበረው  ሁሉ ተለወጠና፤ በአለንበት ዘመን የሰው መክበሪያው፤ መወደጃውና መደነቂያው መሥፈርት፤ ገንዘቡ ብቻ ሆነ፡፡ ስለዚህ ይሄንን፤ በሕብረተሰቡ ውስጥ አንቱ የሚያሰኝና የሚያስከብር ቁልፍ ነገር ለማግኘት፤ ሞራል የሚባለው ነገር ሁሉ ቀረና፤ በፈለገው ዘዴ ገንዘብን ለማግኘት መሮጥ ሆነ፡፡

ሁሉም ከሀገሩ ወጥቶ ምንዛሪው ጠቀም ያለ ገንዘብ ወደሚያገኝበት ሀገር ተሰድዶ ራሱንም አሻሽሎ ሌሎች ቤተሰቦቹንም ደጉሞ መኖርን መረጠ፡፡

ዐረብ አገር የሚሄዱት እህቶቻችን ሁለት አስከፊ ነገሮች፤ ማለትም በአንድ በኩል የራሳቸውና የቤተሰቦቻቸው በችጋር መቆላትና አዝጋሚ ሞት መሞት፤ በሌላ በኩል ደግሞ ወይም እነሱ ራሳቸውን አዋርደውና ሸጠው የቤተሰቦቻቸውንና የራሳቸውን ሕይወት ማቆየት፡፡

በእነዚህ ሁለት አጣብቂኞች ውስጥ ነው ያሉት፡፡

ብቻ ምን አለፋችሁ ነገሩ ሁሉ “የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጭው” ሆነና “ብትፈልግ ስረቅ፤ ብትፈልግ ግደል፤ ብትፈልግ አጭበርብር፤ ብቻ ገንዘብ ይዘህ ተገኝ፤” ሆነ መፈክሩ፡፡

ታዲያ፤ ከፖለቲካው ምክንያት በተጨማሪ ይህንን “ገንዘብ ይዞ መገኘት” የሚለውን መስፈርት ለማሟላት ብለን ነው መሰለኝ ሁላችንም ሀገራችንን እየለቀቅን መፍለስ የጀመርነው፡፡ ግን ምን እናድርግ አንድን ሰው ባለበት ሕብረተሰብ ውስጥ ለየት የሚያደርገው፤ የሚያስከብረውና ለኃላፊነትም የሚያበቃው ያለው ገንዘብ መጠን እንጂ ሌላው ማንነቱ መሆኑ እየቀረ ከመጣ ዓመታት አለፉ፡፡

…ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፤ካለው መንግሥት ጋር ምንም ዓይነት የፖለቲካ ቅራኔ የሌላቸው በኢኮኖሚውም ቢሆን ከአብዛኛው ኢትዮጵያዊ በተሻለ ሁኔታ ላይ የሚገኙና ምንም ዓይነት የሶሽያል ችግርም ያላጋጠማቸው ስደተኞች መታየት የጀመሩበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡

…አንዳንዶች ደግሞ ካለው መንግሥት ጋር እጅና ጓንት ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተው፤ ወይ የግል ጥቅማቸው ሲነካ ያለበለዚያም ደግሞ ያለውን መንግሥት ሁኔታ ሲመለከቱት ብል የበላው እንጨት መሆኑን ሲረዱ፤ አብረው ላለመውደቅ ሲሉ ቀደም ብለው ጥለውት በመሄድ ራሳቸውን ከእስራትና ከሕዝብ ፍርድ ለማዳን የሚሰደዱ ናቸው፡፡

…አንዳንድ በየኢትዮጵያ ኤምባሲዎች የተሰገሰጉ ጥቅም አሳዳጆችና ሆዳሞች ደግሞ፤ ባሉበት ሀገር በሥራቸው ላይ እስካሉ ድረስ ያለው መንግሥት ደጋፊ መስለው የሚታዩና ያለው መንግሥት ጊዜው ዘንበል ብሎበት ቢወድቅ ባሉበት ሀገር የፖለቲካ ጥገኝነት ጠይቀው የሚቀሩ ናቸው፡፡

ወደ አዲስ አበባ ላለመሄድ አንዴ የጤና አንዴ የቤተሰብ ችግር እየደረደሩ የአዲስ አበባ ጉዞን የሚሸሹ ናቸው፡፡ እንግዲህ እነዚህ ናቸው በቦሌ ወጥተው ስደተኛነት የሚጠይቁ ጥቂት ዜጐች፡፡

ሀገርን ትቶ መውጣት እንደ ሎተሪ ማሸነፍም ይሁን እንደ ስደት ተቆጥሮ፤ በተለያዩ ዘዴዎች ከሀገሩ ከወጣ በኋላስ ስደተኛው እንዴት ነው በሄደበት ሀገር ተቀባይነትን የሚያገኘው? መኖር ከጀመረስ በኋላ እንዴት ይሆን አብዛኛው የሚኖረው የሚለው ጥያቄ ሲመጣ፤ በስደት ላይ የሚገኘው የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ሕይወት፤ ለአብዛኛው ስደተኛ ምንም እንኳን ከነበረበት ሁኔታ ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ቢሆንም፤ በስደተኝነት እንዲቀበለው ለሄደበት ሀገር ኢሚግሬሽን መሥሪያ ቤት ተቀባይነትን ማግኘት ሲል የሚያቀርበውን ምክንያት፤ ሀገር ቤት ሲሄድ ደግሞ መስሎ ለመታየት ሲል የሚያደርገውንና በስደት በሚኖርበት ሃገር ያለበትን ሁኔታ ሲያዩትና ሲሰሙት ግን፤ አንዳንዴ አስቂኝ፤ አንዳንዴ አሳፋሪ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ አሳዛኝ ነው፡፡

 

 

Read 2163 times Last modified on Saturday, 08 September 2012 12:26