Print this page
Sunday, 08 August 2021 00:00

በግብጽ ከ43 አመታት በኋላ የዳቦ ዋጋ ጭማሪ ሊደረግ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

     የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ፣ የአገሪቱ መንግስት እ.ኤ.አ ከ1977 አንስቶ ሲያደርገው የነበረውን የዳቦ ዋጋ ድጎማ ለማንሳት ማሰቡን ከሰሞኑ በይፋ ማስታወቃቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ መንግስት በየአመቱ ለዳቦ የሚያደርገውን 44.8 ቢሊዮን ፓውንድ ያህል ድጎማ ማንሳቱ በዳቦ ዋጋ ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪና ተቃውሞን ያስከትላል የሚል ስጋት መፍጠሩን የጠቆመው ዘገባው፤ በአሁኑ ወቅት 60 ሚሊዮን ያህል ግብጻውያን መንግስት በሚያደርግላቸው የዋጋ ድጎማ አንድ ዳቦ በ0.05 የግብጽ ፓውንድ ሂሳብ እየገዙ እንደሚገኙና አንድ ሰው በየዕለቱ አምስት ዳቦዎችን መግዛት እንደሚፈቀድለት አክሎ ገልጧል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ባለፈው ማክሰኞ አንድ የምግብ ፋብሪካን ሲመርቁ ባደረጉት ንግግር፤በአገሪቱ 20 ዳቦዎች በአንድ ሲጋራ መግዣ ዋጋ እየተሸጡ መገኘታቸው እጅግ አስገራሚ መሆኑን ጠቁመው፤ከአራት አስርት አመታት በላይ የዘለቀውን የዳቦ ዋጋ ድጎማ ማንሳት እጅግ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ማስታወቃቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
የዳቦ ዋጋ ጉዳይ በአገሪቱ ለተቃውሞ መነሾ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ ሲሆኑ ፕሬዚዳንቱ ግን #የዋጋ ጭማሪ እናደርጋለን ስንል ያን ያህል የከፋ ጭማሪ እናደርጋለን ማለታችን አይደለም; ሲሉ አበክረው ለህዝባቸው ቃል ቢገቡም፣ ግብጻውያን በዚያው ዕለት ብቻ በትዊተር ላይ ከ4 ሺህ በላይ የተቃውሞ መልዕክቶችን ማስተላለፋቸው ተጠቁሟል፡፡
በአገሪቱ ለመጨረሻ ጊዜ የዳቦ ዋጋ ጭማሪ የተደረገው ከ43 አመታት በፊት በፕሬዚዳንት አንዋር ሳዳት ዘመን እንደነበር ያመለከተው ዘገባው፤ጭማሪው በወቅቱ በአገሪቱ ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣና ተቃውሞ ቀስቅሶ እንደነበር አስታውሷል፡፡


Read 10641 times
Administrator

Latest from Administrator