Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 08 September 2012 11:57

“ደጋግሞ መተኮስ ቆዳ ማበላሸት ነው!” አለ አሉ የነብር አዳኝ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

በምፀታቸው ረቂቅነት የሚታወቁት ፀሀፌ-ተውኔት መንግሥቱ ለማ ስለ አካላዊ እንቅስቃሴ በድራማ ውስጥ ሲያስተምሩ፤ ድራማ ሲሠራማንኛውም የሰውነታችን ክፍል ሊንቀሳቀስ ይገባዋል ለማለት የሚከተለውን ተረት ይጠቅሱ ነበር፡፡ እነሆ፡-

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ለምድር ለሰማይ የከበዱ ዲታ፣ በጣም የሚፈሩ የሚከበሩ ትልቅ ሰው ነበሩ፡፡ እኒህ ሰው ከባለቤታቸው ጋርሲኖሩ አንድ ወንድ ልጅ አፍርተዋል፡፡ ዕድሜ ልኩን ለእሳቸው ሲያገለግል የኖረ ብርቄ የሚባል አገልጋይ ደግሞ አላቸው፡፡ በየጊዜው ግብር ያገባሉ፡፡ ድል ያለ ድግስ ይደግሳሉ፡፡ የከተማውን ታላላቅ ሰዎች ይጠራሉ፡፡ በዚህ የግብር ድግስ ላይ ብርቄ የጌታውንእጅ ባስታጠበ ቁጥር እንዲህ ይላል፡-

“ጌታዬ፤ እርሶ ከሞቱ እኔ በዚህ ዓለም ላይ ምንም ነገር አይቀረኝም፡፡ ስለዚህ እመንናለሁ!”

ጌትዬውም፤

“ተው ብርቄ አታረገውም፡፡ ዝም ብለህ ቃል አትግባ፡፡ መመነን ትልቅ ቁርጠኝነት ይጠይቃል” ይሉታል፡፡

ብርቄም፤

“የለም ጌታዬ! እርሶ ሞተው?፤ ዓለም ለምኔ ነው?! እመንናለሁ” ይላል፤ ፍርጥም ብሎ፡፡

ጌትዬው “አንድ ኩታና አንድ ብርሌ ጠጅ ይገባሃል!” ይሉና ይሸልሙታል፡፡ ይህ የብርቄ መሀላ፣ ግብር በበሉ ቁጥር ይቀጥላል፡፡ ይህንን

የማያውቅ ሰው የለም፡፡ በተለይ ሁሌም እድግሱ ላይ እየመጣ የሚጫወት አንድ አዝማሪ አሳምሮ ያውቀዋል፡፡ ግጥም እየደረደረ

ውዳሴውን ያሰማበታል፡፡

ጊዜ አለፈ፡፡ ጌትየው አረጁና ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡

ሚስትየው፤ ቆይተው ቆይተው በአገር ሽማግሌ ተመክረው፤ ሌላ ሀብታም፣ አንቱ የተባሉ ጌታ ሰው አግብተው ይኖሩ ጀመር፡፡ ብርቄም

ለአዲሱ ጌታ አገልጋይ ሆኖ፤ እንደተለመደው

“ጌታዬ እርሶ ከሞቱማ እመንናለሁ” እያለ ሽልማቱን እየተሸለመ ሎሌነቱን ቀጠለ፡፡

እኒህኛውም ጌታ ግብር ያበላሉ፡፡ ያ ነባር አዝማሪም ግብዣው ላይ ግጥም እየደረደረ ጨዋታውን ቀጥሏል፡፡

አንድ ቀን ታዲያ፤ እንዲህ ሲል ማንጎራጎር ይጀምራል፡-

“ትላንትና ማታ ጌታዬን አግኝቼ” አለና፤ ትኩረት ለማግኘት ዝም አለ፡፡ ጥቂት ተጋባዦች ብቻ ናቸው የሰሙት፡፡ ደገመው፡- “ትላንትና

ማታ ጌታዬን አግኝቼ” አለ፡፡ ግማሹ ህዝብ ሰማው፡፡ ስለሞቱት ጌታ እየዘፈነ መሆኑን አውቋል ሰዉ፡፡ ሶስተኛ ሲደግመው፤ ሰው ሁሉ

ፀጥ  ብሎ ያዳምጠው ጀመር፡፡ ይሄኔ ጮክ ብሎ ማንጎራጎሩን ቀጠለ፡፡ ግጥሙን በደረደረ ቁጥር ወደ ብርቄ ዞሮ ትኩር ብሎ እያየው

ነው፡፡

“ትላንትና ማታ ጌታዬን አግኝቼ

‘ሚስቴ ደህና ናት ወይ?

ልጄስ አደገ ወይ?

ብርቄስ መነነ ወይ?’

ብለው ቢጠይቁኝ፤

“ሚስትዎት ደህና ናቸው

ልጅዎትም አድጓል

ብርቄም አልመነነም!!፤

ብዬ ብነግራቸው፤”

‘አዬ ጉድ!

አ…ዬ ጉድ!

አዬ ጉድ’ ያሉበት፣ ረገፈ ጣታቸው!!!”

***

ቃል ስንገባ በስሜታዊነት አይሁን! ቃል ስንገባ በአድር-ባይነት አይሁን! ቃል ስንገባ ለይስሙላ አይሁን! ቃል ስንገባ በእርግጥ አደርገዋለሁ ወይ? ብለን ከልባችን ጠይቀን፣ በአዎንታዊነት እራሳችንን አሳምነን፣ በቁርጠኝነታችን ተማምነን እንጂ እንደው በሞቅ ሞቅና በሰሞነኛ መንገኝነት ተገፋፍተን እንዳይሆን እንጠንቀቅ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ቃል የምንገባበትን ጉዳይ ጠንቅቀን እንወቅ፡፡ ለምሳሌ፤ የምንለው ዓላማ ጠላ መጥመቅ ቢሆን ብለን እናስብና ጋኑ በደንብ ታጥቦ ታጥኗል ወይ? ጠላው በቂ ብቅልና ጌሾ አለው ወይ? አስተማማኝ ቦታ ተቀምጧል ወይ? ጠላው ምን ደረጃ ላይ ነው ያለው? ገና ለጋ ነው? በስሏል? መኮምጠጥ ጀምሯል? እንዲጠጣ ብቻ ነው ወይስ እንዲያሰክር ነው የሚፈለገው? ጠማቂው ባለሙያ ነው ወይ? ስንት ሰው ነው እንዲጋበዝ የተፈለገው? ጐረቤት ይጠራል ወይ? ከመጠጣት ያለፈ ምን ጥቅም አለው? ጠላ ጠምቀን እፎይ ብለን መቀመጥ ነው ወይስ ምግብም ማብሰል አለብን? ድግሳችንን አገርም ጎረቤትም ሁሉ ነው ወይ የሚበላው? ፀጉረ-ልውጥ ድንኳን ሰባሪ ቢመጣብንስ? በቂ አጋፋሪ፣ በቂ ጠባቂ፣ በቂ ተቆጣጣሪ አለን ወይ? በአጠቃላይ፤ ምንም ደሀ ብንሆን የድግስ ትንሽ የለውም ይባላልና መጠንቀቅ አለብን!! ብክነትን መቆጣጠር ይገባናል!! ድግሱን ለግሉ የሚበላን በንሥር ዐይን ማስተዋልና መጠበቅ አለብን!!

እንደዱሮ ተማሪዎች በ”ነት” (“ism”) እንናገርና “ዛሬ ሀገራችን

ሰብአዊነት (Humanism)፣ ባህላዊነት (Culturalism)፣ ምሁራዊነት (Intellectualism)፣ ዕድገታዊነት (Developmentalism) እና አንድነታዊነት (Nationalism)

እንደሚያሻት፤ ቢያንስ ያለፉት ሣምንታት ያሳዩናል፡፡ (ሱዛን ራይስ ከሁሉም በላይ ሰብዓዊ ግንኙነት ወሳኝ መሆኑን /አሜሪካውያን እንዴት እንደሚያውቁን መገንዘባችን ሳይረሳ/ አሳይታናለች፡፡)

“እኔ ነኝ ያለ…” እያልን መዝፈናችን የድፍረታችን ዘርፍ መሆኑ አንደተጠበቀ ሆኖ፤ የተግባር አርአያ ነው ብለን የምናስበው ሰው ግን በልባችን ሊኖር ይገባል፡፡ ወደድንም ጠላንም፤ ለልማት መነሳሳቱ መልካም መሆኑን እንደምናይ ሁሉ ለውጥ ዛሬም በአንድ ጀንበር እንደማይመጣ ልብ እንበል! ለደቂቃም ቢሆን አንዘናጋ!! የአንድ ሰሞን የሥራ ሰዓት ማክበር ሳይሆን የሥራ ባህል በዘላቂነት እንዲኖር ማድረግ ነው ቁምነገሩ! ሥር-ነቀል ለውጥ ማምጣት ብዙ ፖለቲካዊ ገፅታዎች አሉት፡- የተቃዋሚ መሪዎች ሁሉ ወደ ውጪ መፍለሳቸው፤ አክራሬ ትላንት የሆኑ በጡረታም፣ በውጪ ሹመትም፣ ከእንቅስቃሴው ዕምብርት መራቃቸው፣ ለውጥ የማይዘልቃቸው ሰዎች (ተቸካዮች) በዚህም ሆነ በዚያ ምክንያት መገለል፣ አዳዲስ ተተኪዎችን ማዘጋጀት፣ በየመዋቅሩ ላይ ሁነኛና የሚታዩ ለውጦችን ማካሄድ…እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡

ለመሪያችን መታሰቢያ ማስቀመጥ መልካም ተግባር ይሁን እንጂ አስተሳሰባችንን መንደራዊ (Local) እንዳናደርግ ዓለማቀፋዊውን አድማስ አብረን እናስተውል፡፡ ታሪካዊነቱን እናሰላስል!

እንደ ሰሜን ኮርያው ኪም ኢል ሱንግ ዳር - ድንበር የሌለው ውዳሴ፣ ሐውልቶች፣ የአዳዲስ ብር ኖት ምስሎች፣ የመንገዶች ስያሜ ወዘተ. እንዳይበዛ አግባብ ያለው መታሰቢያ መሆን እንዳለበት እናስብ!

ስለራዕይ ካሰብን ፖለቲካዊ ቅርብ - አዳሪነትን (Political Myopiaን) መዋጋት አለብን!

Chi Si ferma e perduto ይላል ጥሊያን፡፡ “መንገድ ጀምሮ የቆመ ቀለጠ” እንደማለት ነው! በአማርኛ አተራረት “ያረፈ የሊጥ ሌባ!” እንደማለትም ሊታሰብ ይችላል!

ትልቁን ስዕል እናስብ (The bigger picture)፡፡ የጣሊያኑ ንጉሥ ቪክቶር ኢማኑኤል ሦስተኛው፤ ሒትለርን የጀርመኑ እግረኛ ጦር በየቦት ጫማው ስንት ከምሱር ምሥማር አለው?” ብለው፤ ለማብራራት፣ “የጣሊያን እግረኛ ወታደር፤ ተረከዙ ላይ 22 ሚሥማር፣ ሶሉ ላይ በጠቅላላው 52 ሚሥማሮች አሉት፣” አሉት፡፡ ሒትለርም፣ “ጫማውን ትተው ዋናውን ሰውዬ ለምን አያዩም?”  ብሏቸዋል አሉ፡፡

ትልቁን ነገር እንይ፡፡ ዝርዝር ኪስ ይቀዳል ይላል የአራዳ ልጅ!

አገራችን ከድህነት ለመውጣት ገና ብዙ መንገድ፣ ገና ብዙ ትግል አለባት፡፡ የሰው መተካካት ጉዳይ ትልቅ ሥራ ነው፡፡ ሀገራዊም ሆኑ ዓለም አቀፋዊ ክፍተቶችን ለመሙላት ብርቱ ብርቱ ሰዎች ይፈለጋሉ፡፡ የተቋም መዋቅር ብቻ ሳይሆን መዋቅሩ ላይ የሚቀመጡትን ሰዎች በቅጡ መምረጥ ያስፈልጋል፡፡ ከግለሰበኝነትም (Selfish individualism) ሆነ፣ ከአምልኮ-ሰብ (personality cult) የራቀ አካሄድ ይጠበቅብናል፡፡ በተጨባጭ ጎዳናውን መጥረግ እንጂ በግምትና በአቦ-ሰጡኝ ከመሄድ መጠንቀቅ አለብን፡፡ ከወገንተኝነት ርቀን የበዛሄ-ተሳትፎን እምናለመልምበት ዕድል አሁን ያለ ይመስላል፡፡ ይህን ዕድል ማጣት ምን እንደሚመስል በ1966፣  በ1983፣ በ1997 አይተናል፡፡ ቆም ብለን ማሰቢያ ጊዜ አለን!

ደጋግመን መፈክር ስላሰገርንና፣ ደጋግመን በቃል ቃል ስለገባን ግባችንን በተግባር እንመታለን ማለት አይደለም፡፡ የምንጓዘው ዓላማችንን አንጥረንና አነጣጥረን መሆን አለበት፡፡ ተግባሩን እንጂ ተደጋጋሚ ወሬውን እንተው፡፡ በአንድ አስተማማኝ ጥይት የነብሩን ግንባር ለመምታት የሚችለው የነብር አዳኝ፤ “ደጋግሞ መተኮስ ቆዳ ማበላሸት ነው!” አለ የሚባለው ለዚህ ነው!

 

 

Read 4703 times Last modified on Saturday, 08 September 2012 12:11

Latest from