Monday, 02 August 2021 20:35

"ጥፋ ያለው ከተማ ነጋሪት ቢጎሰም አይሰማ"

Written by 
Rate this item
(2 votes)

   የአንድ  ሰፈር  ሰዎች ወደ ጦርነት ሊሄዱ ለረጅም ጊዜ በዝግጅት ላይ ከርመዋል። በዝግጅቱ ወቅትም የማይፎክሩት ፉከራ፣ የማያቅራሩት ቀረርቶ፣ የማይደነፉት ድንፋታ አልነበረም። ገና ሳይዘመት ይዘፈናል፣ አታሞ ይደለቃል፣ ዳንኪራ ይረገጣል። ዘማቾቹም ለህፃን ለአረጋውያኑ ጀግንነታቸውን እያስረዱ ከድል በኋላ ምን አይነት ሹመት እንደሚሾሙ ሳይቀር ይተነብያሉ። በተለይም አለቃቸው ጠላትን እንዴት ድባቅ እንደሚመታና የተማረኩትንም እጅ-እግራቸውን ጠፍሮ አስሮ መንደር ለመንደር እያዞረ እንደ ላንቲካ እንደሚሳያቸው፣ከዚያም እስከ አንገታቸው ድረስ ከነህይወታቸው መሬት ቀብሮ ከብት እንደሚያስነዳባቸው ዲስኩር ያደርጋል። አንድ ነገሩ ያላማራቸው አዛውንት፤
“ተው ልጆቼ፣ ሲሆን እርቁ ነበር እሚበጀን፤ እምቢ ብላችሁ ጦር ውስጥ ከገባችሁ ደግሞ ፉከራውና አስረሽ ምቺው ቢቀርባችሁ? ለእሱ ስትመለሱ ያደርሳችኋል” ቢሉ፤ ሰሚ ጆሮ አጡ።
ፉከራው ይቀጥላል። ዘፈኑ ይቀልጣል። በመካያው ለዚያ አለቃ ፈረስ ተዘጋጀለትና ሌሎቹ ጋሻ ጃግሬዎች በእግራቸው፣ እሱ በፈረስ ዘመቱ። ብዙ ጊዜ አለፈ። የጦርነቱን ወሬ ግን አየሁም ሰማሁም የሚል ወሬ-ነጋሪ ጠፋ። መንደሩ ተጨነቀ። አሸነፉም ተሸነፉም የሚል ወሬ በሀሜት መልክም እንኳ ሳይሰማ ይከርማል…
 በመጨረሻም ከሩቅ አንድ ሰው በፈረስ ሲመጣ ይታያል። አቧራው ይጨሳል። የመንደሩ ሰውም፤ “መጡ-መጡ” እያለ ለመቀበል ይወጣል።
ቀድሞ የደረሰው ያ የዘመቻው መሪ ነበር። ከፈረሱ ወርዶ ሰዉን #እንዴት ከረማችሁ;  ካለ በኋላ፣ እኒያ ተዉ ይሉ የነበሩ አዛውንት፤
 “እንደው ልጄ አገር ያስባል አትሉም እንዴ? አንድ መልዕክተኛ አጥታችሁ ነው ሳትልኩብን የቀራችሁት? ለመሆኑ ጦርነቱ እንዴት ነበር?” ብለው ይጠይቁታል።
ያም የዘመቻው መሪ፤ “አይ፤ እንደፈራነው አይደለም። እኔ በደህና በሰላም ተመልሻለሁ!!” ብሎ መለሰ።
*   *   *
አምባገነን መሪዎች ከራሳቸው በዕብሪት የተሞላ ፍላጎት ውጪ፤ እንኳን ለሚገዙት ህዝብ ለገዛ ግብረ-አበሮቻቸውም ቁብ የላቸውም። ለማንም አያዝኑም። ሰብአዊነት አልፈጠረባቸውም። ዋናው የእነሱ ደህንነት ነው።  ዋናው የእነሱ ሥልጣን ነው። ዋናው የእነሱ ሰላም ነው። ዋናው የእነሱ ቅዠት እውን መሆን ነው። ሌላው ሁሉ ትርፍ ነው፡፡ ለዚያ ደግሞ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ ይደነፋሉ፡፡ ያስፈራራሉ፡፡ ህዝብ ለዘመቻ ይቀሰቅሳሉ፡፡ ጦርነት ያውጃሉ፡፡ አስገድደው ያዘምታሉ። ህዝባቸውን ያለ ርህራሄ ለሞት ይገብራሉ። የሺዎች ህይወት እየተቀጠፈና፣ የሺዎች ኑሮ እየተፈታ እነሱ ፍላጎታቸውን ማርካት እንጂ እልቂቱ ደንታቸው አይደለም።
በታሪክ የሚታወቀው የሮማ ንጉሥ ኔሮ /ሉሺየስ ዶሚቲየስ አሄኖባርበስ/ የሥልጣኑ ጣዕምና ግዛት ሲያሰክረው እናቱንም፣ ሚስቱንም፣ ጓደኞቹንም ገድሎ በገዛ ፍላጎቱ ብቻ እየተመራ ሮማ ስትቃጠል፣ እሱ ይደንስ የነበረና በመጨረሻም አመፅ በአመፅ ላይ እየተደራረበ ሲመጣበት፣ ራሱን ለመግደል የበቃ አምባገነን ንጉስ ነበር።
እንዳለመታደል ሆኖ በአህጉራችንም ሆነ በአገራችን ሥልጣንና ጥቅም ያሰከራቸው አምባገነኖችን አላጣንም፤ ከጥንት እስከ  ዛሬ።
የሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በመሰንዘር የጦርነቱን ክብሪት የጫረው አምባገነኑ የህውኃት ቡድን፣ ወደዚህ እኩይ ድርጊቱ የገባው #ከሁለት አሰርት ዓመታት በላይ እንደ ርስት ከያዝኩት የመንግስት ሥልጣን ለምን ተገፋሁኝ; በሚል ቁጭትና እብሪት ነው ቢባል ኩሸት አይሆንም፡፡ ድንገት ከእጁ ያመለጠውን ሥልጣን መልሶ ለማግኘትም ብቸኛው አማራጭ ነፍጥ ነው ብሎ ያሰላው ህወኃት፤ ለሦስት ዓመታት ያህል ራሱን ለጦርነት ሲያዘጋጅ ከረመ - ለትግራይ ህዝብ "ዙሪያህን ተከበሃል" የሚል በፍርሃትና በስጋት የሚቀፈድድ  ሃሰተኛ ፕሮፓጋንዳ በመስበክ፡፡  
የመከላከያ ሰራዊት የህግ ማስከበር ተልዕኮውን ለመወጣት ወደ ትግራይ ሲዘምት ቡድኑ ምን እንደተሰማው በእርግጠኝነት ለማወቅ ያዳግታል፡፡ ነገር ግን እንደ ማንኛውም አምባገነን፣ በመቶ ሺዎች በሚቆጠሩ የትግራይ ወጣቶች መስዋዕትነት ህልሙን ለማሳካት ተፈጥሞ እንደነበር በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡
ከላይ በታሪኩ እንደተጠቀሰው፣ በጦርነቱ ዋዜማ ያልተፎከረ ፉከራ፣ ያልተደነፋ ድንፋታ፣ ያልተደለቀ አታሞ አልነበረም፡፡ ጦርነት ግን ድንፋታና ፉከራ አይደለም፡፡ ህይወት ያስገብራል፡፡ እልቂትና ፍጅት ያስከትላል፡፡ ጥፋትና ውድመት ያመጣል፡፡
የመከላከያ ሰራዊቱ የመቀሌ ከተማን በአጭር ጊዜ ውስጥ ተቆጣጠረ፡፡ ሂደቱ አልጋ በአልጋ ግን አልነበረም፡፡ ይሆናል ተብሎም አይጠበቅም፡፡ መስዋዕትነትን ያስከፍላል፡፡ በጦርነቱ ብዙ ሺህ የትግራይ ወጣቶች አልቀዋል፡፡ ከቡድኑ አመራሮች መካከልም አብዛኞቹ ሲገደሉ፣ ከፊሎቹ በቁጥጥር ስር ውለው ወህኒ ወርደዋል፡፡  
ከሞት የተረፉት በጣት የሚቆጠሩ የህውኃት አመራሮች መቀሌ ሲገቡ ምን አሉ? እንደ ዘመቻ መሪው፤ “አይ! እንደፈራነው አይደለም። በደህና በሰላም ተመልሰናል!” ነው ያሉት፤ ግብረ አበሮቻቸው በሙሉ ቢገደሉባቸውም፡፡ ከዚም የውሸት ድል አከሉበት፡፡ የፌደራል መንግስቱ በራሱ ጊዜ የተናጥል የተኩስ አቁም አውጆ ሠራዊቱን ከመቀሌ ቢያስወጣም፣ እነሱ ግን “አሸንፈን ነው ያስወጣናቸው” ሲሉ በዕብሪት ተሞልተው ደነፉ፡፡
ደጋግመው ያስተጋቡትን ውሸት እውነት ነው ብለው አመኑና፣ መቀሌን በተቆጣጠሩ ማግስት፣ ሌላ ዙር የጦርነት አዋጅ አወጁ፡፡ በአማራም በአፋርም በኤርትራም በኩል ጥቃት እንደሚሰነዝሩ ምለው ተገዘቱ፡፡ "ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ሲኦል መግባት ካለብንም እንገባለን" ብለው ተፈጠሙ፡፡ እንደተለመደው ብዙ ብዙ ድንፋታዎች፣ ብዙ ብዙ  ዛቻዎች ተሰሙ፡፡
ይኸኔ ነው የትግራይ ህዝብ ሰቆቃና መከራ እንደ አዲስ የጀመረው።
ወጣቶችና አዛውንት ለሌላ ዙር ጦርነት በውድም በግድም እየተመለመሉ ይዘምቱ ጀመር፡፡ ቡድኑ ዕድሜያቸው ያልደረሰ ህፃናትን ለጦርነት በመጠቀም ዓለምን ጉድ አሰኘ፡፡ በሁለት ሳምንታት ውስጥ  በአፋርና በአማራ በኩል በተደረጉ ጦርነቶች ብዙ ሺ የትግራይ ታዳጊዎችና አዛውንቶች ማለቃቸው ተሰምቷል፡፡ አሁንም ግን የህወኃት ቡድን በጦርነቱ ቀጥሎበታል፡፡ በየጦርነት አውድማው ድል እንደቀናው እየደሰኮረም ነው፡፡
በዚህ መሃል ከ1.2 ሚሊዮን በላይ የትግራይ ህዝብ ለረሃብ አደጋ መጋለጡ እየተነገረ ነው፡፡ በትግራይ ስልክ የለም፡፡ መብራት የለም፡፡ የባንክ አገልግሎት የለም፡፡ ትራንስፖርት የለም፡፡ ሥራ የለም፡፡ ደሞዝም የለም፡፡ በጀትም የለም፡፡ እንዲያም ሆኖ የህወኃት ቡድን አሁንም ድል ማድረጉን እየደሰኮረ ነው፡፡
አምባገነኖች መቼም ይሁን የትም ሽንፈትን አምነው ተቀብለው አያውቁም። አልፈው ተርፈውም ለህዝባቸውም ዋሽተውና ጦሱ ተርፎት፣ ህዝቡ ጭምር በነሱ ቅኝት እንዲዘፍን ያስገድዱታል፡፡ “ጥፋ ያለው ከተማ ነጋሪት ቢጎሰም አይሰማ” ማለት ይኸው ነው። ከዚህ ይሰውረን!

Read 9995 times