Wednesday, 04 August 2021 00:00

ስንቱን ነገር እንራብ?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 መልካም አስተዳደር ተርበን፤ ሰከን ማለትን ተርበን፤ እልህ ተርበን፣ ሀቅ መስማት ተርበን፣ እውነት መናገርን ተርበን ፖለቲካዊ መተባበርን ተርበን፣ በወንድማማችነት መፎካከርን አቅምና አቅል አጥተን፣ በችኩል ጅብ ቀንድ ላይ እኛ ፖለቲከኞች በፀያፍ ቃላት እየተሰዳደብን፣ እየተጠቋቆርን ከመቃወም የጠላትነት ፖለቲካ ጣጣ ተጠልፈን ቅንነትንና ደግነትን ተርበን እንዴት እንቀጥላለን? ምናልባት “ቆንጆዎቹ ትውልዶች” ሲፈጠሩ ከአይነተ ብዙ ረሀብ ይታደጉን ይሆን? የ1960ዎቹና ይህ ትውልድም ቆሻሻ አስተሳሰብ፣ አነጋገርና አተገባበር የተጠናወተው በመሆኑ “አስቀያሚ” ብያቸዋለሁ። ሚሊዮኖች እንዲሞቱ እቅድ እያወጡ እንስሳዊ ጭካኔ ጠባይ የተጠናወታቸውን ስናስብ “አስቀያሚዎች” ማለት ያንስባቸዋል።
ኢቲቪ “አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች” በሚል ለአስተያየት የሚቀርቡ ሰዎች፤ ለገዢው ፓርቲ ታማኝነታቸውን ለማሳየት የሚሰጡት ምስክርነትና አስተያየት ለህጋዊ፣ ህሊናዊና  ሀገራዊ እንድምታ ደንታ ስለሌላቸው ውሸት ብቻ እየመሰከሩና እየተናገሩ እስከ መቼ ይዘለቁ ይሆን  ኢትዮጵያ የአፍሪካ ምሳሌ ናት  እንላለን። የአፍሪካ እናትም፣ እህትም አርአያም ናት። ኢትዮጵያዊያን የራሳችን ባህላዊ እሴትና ዘመናዊ አስተሳሰብ ያውም ያልተዳቀለ አለን። የጠቅላይ ሚኒስትሩን (የ2010 ዓ.ም) “የመደመር” አገር በቀል ፍልስፍናን ማሰብ ይቻላል። ካለን ከባህላችን አንዱ ይሉኝታ ነው። ሰው ምን ይለኛል? ማለት ጥሩ የኢትዮጵያዊነት ባህል ነው! የአለም ዘር ሁሉ ምንጭ (ድንቅነሽ) መገኛ ነን። በተጨማሪም ቅኝ አልተገዛንም፣ የታላቅ ሃይማኖቶች ተቀባይና አክባሪ ሀገር ኢትዮጵያችን፣ የራሳችን ሀገር በቀል እምነትና እውነት (waaqeffannaa) ያለን ኩሩ ሕዝቦች ሆነን፣ እንዴትስ ብዙ ነገር እንራባለን?
ጥሩ ይሉኝታ ማለት ህዝብ ምን ያለናል? ሀገር ምን ይለናል? ህሊናዬ ምን ይለኛል? ቀጣይ ትውልድስ እንዴት ይመዝነኛል? ታሪክስ ምን ፍርድ ይሰጠኛል? ብሎ በጥልቀት በማሰብ፣ የማያስፈልግ ምስክርነት ከመስጠት፤ የማያስፈልግ ዘፈን ከመዝፈን፣ ያልተገባ ፍራቻን በማስወገድ ወቅታዊና ተጨባጭ ሀገራዊ እውነታን በእውቀትና በእምነት መመስከር መቻል ማለት ነው። እንደ አበው አባባልም፤ የማይሆን ተናግሮ ትዝብት ውስጥ ከመውደቅ “ዝምታ ወርቅ ነው” የሚለውን ማሰብ ይመረጣል። እስቲ ወደ ፊት ራቅ አድርጌ ላስብና ዛሬ የምሰጠው (የምንሰጠው) አስተያየት፣ ከዛሬ 30 እና 50 ዓመታት በኋላ ልቻችን፣ የልጅ ልጆቻችን ምን ይሉናል? እንባል ይታያችሁ በ1889 ዓ.ም በንጉስ ምኒልክ ዘመነ አገዛዝ የጀመረን ረሃብ፣  በኃይለ ስላሴም መጠኑን ጨምሮ፣ በደርግም ብሶበት አይተነው፣ በማናውቀው ሁኔታ በ1977 ዓ.ም አንድ ሚሊዮን ሰዎች በረሃብ ሲያልቁ፤ ደርግና ትህነግ (ሕወሓት) በረሃብተኛ ህዝብ ስም እህልና ብር እየለመኑ፤ የየፓርቲዎቻቸውን የፖለቲካ ሥራና ጉባኤ በውስኪ እየተራጩ ያከብሩ ነበር።
በኢህአዴግ ዘመንም የረሃብ ችግር ወደ “ችጋርነት” (ፕ/ር መስፍን በግልጽ የሚጠቀሙበት ቋንቋ ነው) ከፍ ብሎ 7 ሚሊዮኖች ባይሞቱም፣ በሚሊዮኖች ተርበን፤ በሚሊዮኖች የውሸት ቁጥር ላይ ተከራክረን፣ ከትናንት እስከ ዛሬ ሚሊዮን ረሃብተኞችንና ይህን መሰል አሳፋሪና አሳዛኝ ታሪክ ተሸክመን እየገሰገስን እናገኛለን። የኔ ጥያቄ “ይህ እስከ መቼ ይቀጥላል ነው?” በዚህ ዘመን ከ6 ሚሊዮን ረሀብተኛ ወገኖቻችን መካከል በአርሲ ዝዋይ ዱግዳ ወረዳ በ2001 እና በ2002 ዓ.ም  የምርት ዘመን፣  በዝናብ እጦት ሰብል ሙሉ በሙሉ መጥፋቱን ተከትሎ  በከፍተኛ ረሃብ የተጎዳ ሕዝብ መሆኑን እንደ ማስረጃ መጥቀስ ይቻላል። ኃላፊነት መወጣትን፣ መብትና  ግዴታንም… ተርበን እስከ መቼ እንዘልቅ ይሆን?
በንጉሱ ዘመን (በ1960ዎቹ) ሬዲዮና ቴሌቪዥን ብርቅ ቢሆንም፣ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ጥሩ የመስማትና የማየት ዕድል ከነበራቸው ወጣቶች አንዱ በዘመኑ የመነቃነቅ ሳንሱር መቀስ (ሃሳብን መቆጣጠር፣ ህሊናን ማስቆጣት፣ መጨቆን) ጨካኝ አመራርና አሰራር ቢኖርም ከንጉሱ ዘመን ጋዜጠኞች ነት  የሚጠቀሰው የአርሲ ሁሩታው፣ ጋዜጠኛ አሳምነው ገ/ወልድ፤ የሀሳብ ልጓሙን ተጋፍጦ፣ በቋንቋ ጥበብ የመቀሷን ሳንሱር ሸልቅቆ፤  የአገዛዙን ብልሹነት በጀግንነት ያጋልጡ ከነበሩት አንዱ እንደነበረ ትዝ ይለኛል። እና ወይ ነዶ! ወይ የዛን ጊዜ ጋዜጠኞች! ለህዝብ፣ ለህግ፣ ለሀገርና ለህሊና የነበራቸው ተቆርቋሪነት ከፍተኛ እንደነበር መመስከር ያስፈልጋል። በቀጣይ ወደ ስልጣን የመጣው ወታደራዊው ሆነ ጽንፈኛው ብሔረተኛው ህወሓት፣ ከንጉሱ በባሰ “ሃሳብ” ገዳይ፣ አሳዳጅና አሳሪ ሆኖ።
ጋዜጠኞች ህዝብን፣ ህግን፣ ሕገ-መንግስትን፣ ሀገርን፣ ህሊናንና ሙያዊ ግዴታን እችላ ብለው የገዥዎችን ፍላጎት ብቻ ተሸክመው ኖረው ኖረው  የኢትዮጵያን ምድር መልቀቃቸውን በየብስ፣ በባህር ወይም በአየር  ሲያረጋግጡ ብቻ “ እነ ኢቲቪም ሆኑ ሬዲዮ ጣቢያዎች እንዲሁም የመንግስታው ጋዜጦች ሙያዊ ነፃነት እንዳልነበራቸው ሲመሰክሩ ታዝቤለሁ። ጥቂቶች ግን ብቻቸውን ቢሆኑም ስርዓቱንና ግፉን በመዳፈር ተደንቀዋል (ተመስገን ደሣለኝ፣ ውብሸት ታዬ፣ ፕ/ር መረራ ጉዲና)” ከብዙዎቹ ለአብነት ይጠቀሳሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ በፓርቲ ታማኝነት ወይም በኮታ ወደ ሙያው ስለሚገቡ ለሙያው ደንታ ባይኖራቸውም አይፈረድባቸውም። ይባስ ብሎም “ልማታዊ ጋዜጠኛ የሚባል ካባም ስለሚደረብላቸው ችግርን መንቀስና ማሳየት አይደፍሩም።
እንድፈር  ቢሉም  አቅሙናብቃቱና  አይኖራቸውም። ስለዚህ ጋዜጠኞቻችን ሙያችሁን፣ ህዝባችሁን፣ ሀገራችሁን፣ ታሪካችሁ መፍራትና ማክበርን ጨክናችሁ መጀመር አለባችሁ። ገዥዎች ይቀያየራሉ፤ ታሪክ ግን ይቀጥላል።
(ከወንድሙ ኢብሳ “የእውነት ምርኩዝ” የተቀነጨበ)

Read 1195 times