Saturday, 31 July 2021 00:00

የ7 አመቷ ብራዚላዊት ለናሳ ባበረከተችው ግኝት በአለም ትንሽዋ አስትሮኖመር ተባለች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ብራዚላዊቷ የ7 አመት ታዳጊ ኒኮል ኦሊቬራ በቅርቡ ከባልደረቦቿ ጋር በጥምረት ባደረገችው ምርምር 7 አዳዲስ አስቴሮይዶችን ማግኘቷንና በዚህም በአለማችን የአስትሮኖሚ ወይም ስነከዋክብት ምርምር ታሪክ በለጋ ዕድሜዋ በሙያው አዲስ ግኝት ያበረከተች ቀዳሚዋ አስትሮኖመር ተብላ መሸለሟን ቴክታይምስ ድረገጽ አስነብቧል፡፡
ኦሊቬራ በአሜሪካው የጠፈር ምርምር ማዕከል ናሳ እና ኢንተርናሽናል አስትሮኖሚካል ሰርች ኮላቦሬሽን በተባለው አለማቀፍ ተቋም በተከናወነው አስቴሮይድ ሃንት ሲቲዝን ሳይንስ የተሰኘ የምርምር ፕሮግራም ተሳታፊ በመሆን 7 አዳዲስ አስቴሮይዶችን ማግኘቷን የጠቆመው ዘገባው፣ በዚህ ውጤታማ ስራዋም የአለማችን ትንሽዋ አስትሮኖመር የሚል ዕውቅና ከተቋማቱ ልታገኝ መብቃቷን ገልጧል፡፤
ታዳጊዋ ለጠፈርና ለስነከዋክብት ልዩ ፍቅርና ፍላጎት ያድርባት የጀመረው ገና የሁለት አመት ህጻን ሳለች እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ ዕድሜዋ ከፍ እያለ ሲመጣ ወደሙያው የበለጠ መሳቧንና በራሷ ጥረት ከፍተኛ ዕውቀት ለማካበት መቻሏን እንዲሁም በስድስት አመት ዕድሜዋ አላጎኣስ የተባለው የብራዚል የአስትሮኖሚ ጥናት ማዕከል አባል ሆና የበለጠ ዕውቀት መገብየቷንና በከፍተኛ ውጤት ማለፏን ተከትሎም በትምህርት ቤቶች እየተጋበዘች ትምህርት መስጠት እንደጀመረች ገልጧል፡፡
የብራዚል የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር ባለፈው ወር ባካሄደው የመጀመሪያው አለማቀፍ የአስትሮኖሚና ኤሮኖቲክስ ሴሚናርም ብራዚላዊቷን በመጋበዝ ትምህርታዊ ማብራሪያ እንድትሰጥ ማድረጉን የጠቆመው ዘገባው፣ በቅርቡም አስቴሮይድ ሃንት ሲቲዝን ሳይንስ ፕሮግራም ተሳታፊ በመሆን 7 አዳዲስ አስቴሮይዶችን ማግኘቷንና በዚህም በእድሜ ለጋዋ የአለማችን አስትሮኖመር ለመባል መብቃቷን አመልክቷል፡፡
ታዳጊዋ ኦሊቬራ የኮሮና ወረርሽኝን ተከትሎ የራሷን የዩቲዩብ ቻናል በመክፈት በስነከዋክብት ዙሪያ ከሙያ አጋሮቿ ጋር ገለጻ መስጠት መጀመሯንም ዘገባው አስነብቧል፡፡


Read 979 times