Wednesday, 28 July 2021 00:00

የትንበያ ሚስጥርና ፈተና - ከትንቢተ ዮናስ ትረካ።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

• በስሜት ህሊናው ለተጋረደበት አገርና እልህ ለተጠናወተው ፖለቲካ፣ ጥሩ ምክር የያዘ ድንቅ ትረካ ነው - ከመከራ የሚያድን የቅንነት ምክር (በሃይማኖታዊ ሳይሆን በዓለማዊ ትርጉሙ)።
               ዮሃንስ ሰ


              “የጌታ ቃል፣ ወደ አሚቴ ልጅ ወደ ዮናስ፣ እንዲህ አለ። ተነስ፣ ወደ ነነዌ፣ ወደ ታላቋ ከተማ ሂድ። በእርሷ ላይም ስበክ። ክፋታቸው፣ በእኔ ፊት ገንኗልና። ዮናስም ተነሳ፤…” በማለት ይጀምራል - የትንቢተ ዮናስ ትረካ። ቶሎ ወደ ነነዌ ለመሄድ የተነሳ ቢመስልም፤ ችኮላው ለኩብለላ ነው።
በነገራችን ላይ፣ “የአሚቴ ልጅ ዮናስ”… የሚለው ሐረግ፣ በጥሬው፣ “የእውነት (የእምነት) ልጅ እርግብ”… የሚል ትርጉም ያዘለ ነው። ላይ ላዩን በችኮላ ካየነው፣ የዮናስ ትንቢት፣ እንደ ስሙ አይደለም። እርግብ ማለት ነዋ - ዮናስ ማለት። በግዕዝም፣ በአረብኛም፣ ትርጉሙ ያው ነው። የሌስላው መዝገበ ቃላትም፣ ´ዋኖስ´ ከሚለው የአማርኛ ቃል ጋር ያዛምደዋል። የዮናስ ትንቢት ግን፣ ከእርግብ የሚጠበቅ ሰናይ ትንቢት አይመስልም። የመዓት ምፅአትን የሚናገር ነውና።
ከባህር፣ ከምድርና ከሰማይ መኮብለል - ወዴት ለመውረድ?
“ዮናስም ተነሳ። ከጌታ ፊት ወደ ተርሲስ ለመሸሽ፣ ወደ ጃፋ ወረደ። ከተርሲስ የመጣ መርከብም አገኘ። አብሯቸው ወደ ተርሲስ ሊሄድ፣ ዋጋ ከፍሎ ተሳፋረ - ከጌታ ፊት ኮብልሎ።”
በስተምስራቅ ወዳለችው ታላቅ ከተማ እንዲያቀና ነበር፣ ተነስ የተባለ። እሱ ግን፣ ተነስቶ፣ በስተምዕራብ “ወረደ”። በዚህ አያበቃም። ገና፣ እየወረደ ይሄዳል። ባህር ለመሻገር እንደተሳፈረ፣ ወዲያውኑ ችግር ተፈጠረ።
“ጌታ፣ በባህሩ ላይ ታላቅ ነፋስን አመጣ። በባሕርም ላይ ታላቅ ማዕበል ሆነ። መርከቢቱም ልትሰበር ቀረበች። መርከበኞቹም ፈሩ። እያንዳንዱም ወደየአምላኩ ጮኸ። ከመርከቧ ውስጥ፣ የእቃ ጭነታቸውን ለማቅለል ወደ ባሕር ጣሉት። ዮናስ ግን፣ ወደ መርከቧ ውስጠኛ ስፍራ፣ ጥግ ድረስ ወርዷል። በጥልቅ እንቅልፍም ተኝቷል።”
ለመሸሽ ወደ ምዕራብ ወረደ። አሁን ደግሞ፣ ወደ ስር ወርዶ ተሸሸገ? ወይስ የመጣው ይምጣ ለማለት ነው? ወይስ ማምለጫ እንደሌለው አውቆና ተስፋ ቆርጦ? በዚያ ቀውጢ ሰዓት እንቅልፍ?
የመርከቧ አለቃ፣ በዮናስ እንቅልፍ ግራ ተጋብቷል። መርከበኞች፣ በድንገተኛው ማዕበል ፈርተውና ተጨንቀው፣ ለምሕላና ለፀሎት ይጮሃሉ። እሱ፣ ለጥ ብሏል።
“ምነው ተኝተሃል? እንዳንጠፋ፣ ጌታ ያስበን እንደሆነ፣ ወደ አምላክህ ተጣራ አለው” - የመርከቡ አለቃ።
ዮናስ፣ ወደ አምላኩ አልተጣራም። የመሸሽና የመሸሸግ ሃሳቡ፣ የትም አንደማያደርሰው ጠፍቶት አይደለም። ከእውነት ጋር ተጣልቶ፣ ከእውኑ ዓለም ሸሽቶ ወዴትም ማምለጥ አይቻልም። መድረሻና መደበቂያ ቦታ እንደማይኖረው ዮናስ ገብቶታል። ቢሆንም፤ ሃሳቡን አልቀየረም። ልቡ ከኩብለላ አልተመለሰም።
“ኩብለላ ወይም ሞት!” - የእልህ መፈክር።
መርከበኞቹ፣ ማዕበሉ እጅግ ሲያስጨንቃቸው፣… “ይህ ክፉ ነገር፣ በማን ምክንያት እንዳገኘን እናወቅ ዘንድ፤ ኑ፣ እጣ እንጣጣል ተባባሉ። ዕጣም ተጣጣሉ። ዕጣውም በዮናስ ላይ ወደቀ።”
ዮናስ፣ በዚህ አልተገረመም። ጥፋቱን ያውቃል። እንዲያም ሆኖ፣ “የማዕበሉ ሰበብ እኔ ነኝ” ብሎ፣ እውነተኛውን ታሪክ አልነገራቸውም። ጥፋቱን አልተናዘዘም። በእርግጥ፣ ውሸትም አልተናገረም። ዝም አለ።
መርከበኞቹ በጥያቄ ሲያጣድፉት ግን፤ ነገራቸው። ሳይደናገጥ በእርጋታ፣ “ባህሩንና የብሱን የፈጠረ፣ የሰማይ አምላክን እፈራለሁ (አመልካለሁ)” በማለት፣ የኩብለላ ታሪኩን ጨምሮ አወጋቸው።
ከባህር፣ ከምድርና ከሰማይ ሸሽተህ ወዴት ትኮበልላለህ? ምን የሚሉት ጉድ ነው የሰራኸው?
መርከበኞቹ እጅግ ስለፈሩ፤ ባህሩም ክፉኛ ይናወጥ ስለነበር፤ “ባህሩ እንዲረጋልን ምን እናድርግብህ?” አሉት።
ልቡን ከከንቱ ኩብለላ ከመለሰ፣ ማዕበሉ እንደሚቆም፣ ዮናስ አሳምሮ ያውቃል። የተሳሳተ ሃሳቡን ቀይሮ ካስተካከለ፣ የጥፋት ምፅአትን ማስቀረት እንደሚችል እርግጠኛ ነው። ግን አላደረገውም። እና ምን ተሻለ? ዮናስ፣ ክፉ አይደለም። አብረን እንጥፋ አላለም። ሌላ መፍትሔ ነገራቸው።
“ይህ ታላቅ ማዕበል በኔ ምክንያት እንዳገኛችሁ አውቃለሁ። አንስታችሁ ወደ ባህር ጣሉኝ። ባህሩም ፀጥ ይልላችኋል” ብሎ መከራቸው።
ኩብለላውን ከመተው ሞትን ይመርጣል? አንስታችሁ ወደ ባህር ወርውሩኝ! መርከበኞቹ፣ እሺ አላሉትም። ነፍስ ማጥፋትን እንደዘበት ቆጥረት፣ እንዴት እሺ ብለው ይቀበሉት? ይልቅ፣ ከባህሩ ወደ የብስ ለመጠጋት፣ እንደገና በርትተው ቀዘፉ፤ ታገሉ። ግን አልሆነላቸውም። ማዕበሉ ይባስኑ እየከፋ ነው። በመጨረሻም፣ “ይቅር በለን” እያሉ፣ ዮናስን ወደ ባህር ወረወሩት፤ ማዕበሉ ጠፋ፤ ባህሩ ፀጥ አለ።
የመከራ መዓት፣ ካወቁበት “ቀሪ” ይሆናል። ይሄ፣ ለዮናስ፣ ማር እና እሬት ነው።  
ዮናስ፣ ቁልቁል እየወረደ እየሰመጠ ነው። ለኩብለላ፣ መርከብ ሊሳፈር ወደ ጃፋ ወረደ። ከዚያ፣ ወደ መርከቧ ውስጠኛ ክፍል ወረደ። ከዚያ፣ ወደ ባህር፣ ቁልቁል ሰጠመ። ከዚያም፣ ግዙፍ አሳ ዋጠው። የአሳ ነባሪ ሆድ ውስጥ ተቀበረ። ሶስት ቀንና ሌሊት፣ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ቆየ።
ከዚያስ፣ ሃሳቡን ቀየረ? ልቡ፣ ከኩብለላ ተመለሰ? “መሸነፍ” አልፈለገም። ግን ደግሞ፣ ጨለማ ውስጥ ተቀብሮ መቅረትም አልፈለገም። ደግነቱ፣ እንዴት መውጣት እንደሚችል ያውቃል። ለጊዜውም ቢሆን ልቡን መለስ ለማድረግ፣ ለጊዜውም ቢሆን ከእውነታ ጋር ለመታረቅ ወሰነ። ጨለማው የአሳ ነባሪ ሆድ ውስጥ ሆኖ፣ ዮናስ እንዲህ አለ።
“በመከራዬ ሳለሁ ወደ አምላኬ ወደ ጌታ ጮኽሁ። እሱም ሰማኝ፤…
በሲኦል ሆድ ውስጥ ሆኜ ጮኽሁ፤ ቃሌንም አዳመጥህ፤
ወደ ጥልቁ ወደ ባህሩ ጣልኸኝ…
ማዕበልህና ሞገድህ ሁሉ በላዬ ፈሰሱ…
አንተ ግን፣ አቤቱ አምላኬ፣ ሕይወቴን ከጉድጓድ አወጣህ።”… አለ ዮናስ።
የአሳ ሆድ ውስጥ ተቀብሮ፣ “ተጣራሁ፤ ሰማኝ” ይላል - ምንም ሳይጠራጠር። “ወደ ጥልቁ ባህር ጣልኸኝ። ህይወቴን ከጉድጓድ አወጣኽ”… ብሎ የሚናገረውም፣ ገና ከመቃብር ሳይወጣ ነው። ከመቃብር እንደሚወጣ እርግጠኛ ነው። ከመተማመኑ የተነሳም፣ ገና ከወዲሁ ማመስገን ጀምሯል። ከክፋት መንገድ ጋር ተጣብቆ ሙጭጭ ማለት እንደማያዋጣ በመግለጽም፣ ምክር ይለግሳል።
“ከንቱነትንና ሐሰትን የሚጠብቁ፣ ምህረታቸውን ትተዋል።
እኔ ግን፣ በምስጋና ቃል መስዋዕት አቀርባለሁ።
ስዕለቴንም እከፍላሉ። ማዳን በጌታ ዘንድ ነውና።” አለ ዮናስ።
ሁለት ወዶ አይቻል ነገር!
ከእውነት ጋር ተጣልቶ መሸሽና፣ በሃሰት መንገድ መጓዝ፣ ወደ ከንቱ ጥፋት እንደሚያወርድ ዮናስ ይነግረናል። ይሄ፣ “አይቀሬ እውነት” እንደሆነ አስቀድሞ ያውቃልና።
ግን ደግሞ፣ ወደ እውነትና ወደ ቀና መንገድ ከተመለሰ፣ የመዓት ውርጅብኝ ሁሉ፣ “ቀሪ” እንደሚሆን፣ ዮናስ እርግጠኛ ነው። “ይቅር” ይባላል። በዚህ ተማምኖ፤ ገና ከተቀበረበት ጨለማ ሳይመጣ፣ “ሕይወቴን ከጉድጓድ አወጣህ” በማለት፣ ምስጋና ያቀርባል።
ደግሞም አልተሳሳተም። ተቀብሮ አልቀረም። መከራው ቀሪ ሆነለት። ከአሳው ሆድ ወጣ። መሬት ላይ አረፈ። ብርሃንም አየ። የሰላም አየር ተነፈሰ። ከመከራ መዓት ተርፎ፣ ሕይወትን አጣጣመ - ጣፋጭ ጣዕም። ግን፣ መራራነቱ በርትቶ ታየም። ለምን? “ከመዓት መትረፍ” የሚሉት ነገር፣ ትንቢትን የሚያከሽፍ ነገር ነዋ። ይሄ፣ በፍፁም አልጣመውም። በጭራሽ፣ አይዋጥለትም። ይጎመዝዛል። ነገሩ እንዲህ ነው።
ከእውነት ሸሽቶ መኮብለል፣ ወደ ክፉ ጨለማ ያወርዳል። ይሄ “አይቀሬ እውነት” ነው።
ነገር ግን፣ እዚያው ሙጭጭ ብሎ ካልቀረ፣ ተጸጽቶ በንስሐ፣ ልቦናውን ወደ እውነት ከመለሰ፣ ጨለማውና መከራው “ቀሪ” ይሆናል። ወደ ህይወትና ወደ ብርሃን ይወጣል። ይሄም “አይቀሬ እውነት” ነው።
የነነዌም ጉዳይ፣ ከዚህ ውጭ እንደማይሆን አስቀድሞ አውቋል - ዮናስ።
በክፋት መንገድ ከቀጠሉ፣ ክፉ ጥፋት ይወርድባቸዋል። ያኔ፣ “እኔም ብያለሁኮ። እኔም ትንቢት ተናግሬ ነበር” ሊላቸው ይችላል - ዮናስ።
መንገዳቸውን ካስተካከሉ ግን፣ ከመዓት ያመልጣሉ፤ በደህና ተርፋሉ። ሊወርድባቸው የነበረ መዓት፣ “ቀሪ” ይሆናል። ያኔ፤ የዮናስ ትንቢት ቀልጦ ይቀራል? ያኔ፣ “ከንቱ ሟርተኛ” ብለው ይሳለቁበታል? ይሄ ነገር፣ ውስጥ ውስጡን ቢያንገበግበውም፣ ዮናስ እንደገና የመኮብለል ፍላጎት የለውም። ወደ ጨለማ ወርዶ መከራውን አይቷል። ትረካው ይቀጥላል።
“ስበክባት” እና “ስበክላት” - የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች።
“የጌታም ቃል ዳግመኛ ወደ ዮናስ እንዲህ አለ። ተነስ፤ ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ። የምነግርህን ስብከት ስበክላት አለው። ዮናስም ተነሳ። እንደ ጌታ ቃል፣ ወደ ነነዌ ሄደ።”
“ሰበክላት”?
“በነነዌ ላይ ስበክ “ የሚለው የመጀመሪያው ትዕዛዝ፣ “ለነነዌ ስበክላት” በሚል ሌላ ትዕዛዝ ተቀየረ? የተቀየረ ቢመስልም፣ ልዩነት የለውም። ዮናስ መች ጠፋው? “ስበክባት” ማለት፣ ያው፣ “ስበክላት” እንደማለት ነው። የሁለቱም አባባሎች አላማ ተመሳሳይ ነው። የስብከቱ ትርጉም፣ የትንቢቱ ፋይዳ፣ የነነዌ ሰዎች በንስሐ እንዲድኑ አይደል? ስበክባት እና ስበክላት… ተዛማጅ አባባሎች ናቸው።
እንደ ወቀሳና እንደ ምክር ነው - ዝምድናቸው። የቅንነት እንጥፍጣፊ ካላጣን በቀር፣… ወቀሳ ውስጥ ምክር አለ። ምክር ውስጥ ወቀሳ አለ። የተጣመመውን ለማቃናት፣ የጨለመውን ለማብራት፣ መዓት እንዲቀር፣ ወደ ሲሳይ እንዲቀየር ነው - የወቀሳና የምክር አላማ። “ውቀሰው” ማለት፣ ላይ ላዩን ሲያዩት ጥላቻ ይመስላል። ግን ምከረው እንደማለት ነው።
ስበክባት ወይም “በነነዌ ላይ ስበክ” ማለትም፣ ከቁጣ የመጣ እርግማን ይመስላል እንጂ፣ ከተቆርቋሪ መንፈስ የሚወጣ የነፍስ አድን ጥሪ ነው። ስበክላት እንደማለት ነው፣ ትርጉሙ። “እንዳንጠፋ” ወይም “እንድንድን” ብሎ የመናገር ያህል ነው ተመሳሳይነታቸው።
በአጭሩ፣ የትንበያው ቁምነገር፣ “ትንበያው እንዲከሽፍ” ነው። ይሄ ነው ለዮናስ ያልተዋጠለት። ትንቢቱ፣ በእውን መድረስ አለበት። ካልሆነ ግን፣ ከትንቢት መኮብለል ይሻላል።
የተተነበየው መዓት፣ “ትንቢት ብቻ” ሆኖ ሲቀር፣ ከንቱ ልፋት ይሆናል። “ከንቱ ሟርተኛ” የሚል ስድብም ያመጣል። ውርደት ነው። እናም፣ ከውርደት ለማምለጥ ኮበለለ። ተደበቀ። ግን ሸሽቶ ተሸሽጎ ማምለጥ አልቻለም። ወደ ነነዌ መሄድ፣ ግድ ሆኗል።
ምናልባት፣ ትንቢቱን ንቀው ካጣጣሉት፣ ስብከቱን ካቃለሉት፣ በክፉ መንገዳቸው ከቀጠሉና ካላስተካከሉ፤ ትንቢቱ በእውን ይፈጸም ይሆናል። “ከንቱ ማርተኛ” እንዳልሆነ ያዩታል። “እኔም ብያችሁ ነበር” ይላቸዋል - ትንቢቱ በእውን ከደረሰ። ትንቢቱ ከከሸፈ ግን፣…. ውሸታም መባል፣…. አቤት ውርደቱ! ያንገሸግሻል፤ ይጎመዝዛል።
“የግብር ይውጣ” ትንቢት? ወይስ ቅንነትን የሚያስተምር ትረካ?
የሆነ ሆኖ፣ ዮናስ ወደ ነነዌ አቀና። በዘመኗ፣ የምድራችን አቻ የለሽ ከተማ ተብሎላታል - ነነዌ። በትረካው ደግሞ፣ የከተማዋ ትልቅነት እጅጉን ገናና ሆኗል።
“ነነዌም፣ የሶስት ቀን መንገድ ያህል፣ እጅግ ትልቅ ከተማ ነበረች” ይላል - ትረካው።
በትንሹ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ፣ ሶስት አራት እጥፍ ትበልጣለች ማለት ነው። ለስንት ቀን ያህል እየሰበከ ከተማዋን ማዳረስ ይችላል? በጣም ሰፊ ናት። ዮናስ ለዚህ አልተጨነቀም።
“የአንድ ቀን መንገድ ያህል፣ ወደ ከተማይቱ ውስጥ መግባት ጀመረ። ጮኾም፣ በሶስት ቀን ውስጥ ነነዌ ትገለበጣለች አለ።”
በቃ። የዮናስ ትንቢት ይህችው ናት። እንዲያደምጡትና እንዲገባቸው፣ እንዲያምኑትና እንዲፀፀቱ፣ በንሥሃም ከክፋት ወደ ሰናይ መንገድ እንዲመለሱ የፈለገ አይመስልም። ማብራሪያ የለ፤ ማሳመኛ የለ፤ የምክር ውትወታ የለ… ወቀሳና ውግዘት ለመናገር እንኳ አልሞከረም።
በሦስት ቀን ውስጥ፣ ነነዌ ትገለበጣለች አለ። በቃ። ለግብር ይውጣ አይመስልም?
አስገራሚው ነገር፤ ብዙ የነነዌ ሰዎች፣ የዮናስን ትንቢት አመኑ። ለጾም ለምሕላ ተነሱ። ትልቅ ትንሽ የለም። ሁሉም፣ የዘወትር ልብሳቸውን አውልቀው፣ ማቅ (ጆንያ ዘባተሎ) ለበሱ።
ንጉሡም ወሬ ሲሰማ፣ አላመነታም። “ከዙፋኑ ተነስቶ፤ መጎናጸፊያውን አወለቀ። ማቅ ለበሰ። አመድ ላይ ተቀመጠ። አዋጅም አስነገረ” ይላል ትረካው።
ይሄ ለዮናስ አስደሳች አይደለም። ጾም፣ ምሕላ፣ ንሥሃ፣… በዚህ በዚህ፣ የመዓት ትንበያው ቀልጦ ሊቀር ይችላል። ሕፃን አዋቂው ሁሉ እየፆመ? ንጉሡ ከዙፋኑ ወርዶ፣ ጆንያ ለብሶ፣ አፈር ላይ እየተቀመጠ? ምን ይሄ ብቻ?
እንስሳቱም እንዲጾሙ እንዲጸልዩ ታወጀ። አዋጁ እንዲህ ይላል - “ሰዎችና እንስሳት፣ ላሞችና በጎች አንዳችን አይቅመሱ፤ አይሰማሩም። ውኃንም አይጠጡ።”
ምን ይህ ብቻ። ምሕላም ታክሎበታል።
“ሰዎችና እንስሳት፣ በማቅ ይከደኑ። ወደ ጌታ በብርቱ ይጩኹ” ተብሎ ታወጀ።
እንዲሁም ፣”ሰዎች ሁሉ፣ ከክፉ መንገዳቸውና በእጃቸው ካለው ግፍ ይመለሱ። እኛ እንዳንጠፋ፣ ጌታም ተመልሶ ይጸጸት እንደሆነ፣ ከጽኑ ቁጣውም ይመለስ እንደሆነ ማን ያውቃል?” በሚል አዋጅ፣ ታላቂቱ ከተማ፣ ጾምና ጸሎት፣ ምሕላና ጽሞና ውስጥ ገባች።
“ጌታም፣ የነነዌ ሰዎች ከክፉ መንገዳቸው እንደተመለሱ፣ ስራቸውን አየ። ጌታም ሊያደርግባቸው በተናገረው ክፉ ነገር ተጸጽቶ አላደረገውም” ይላል ትረካው።
“ይህም፣ ዮናስን ከቶ ደስ አላሰኘውም። እሱም ተቆጣ።”
ዮናስ የፈራው ነገር ደረሰ። ነገሩ ለወሬ አይመችም። የነነዌ ንሥሃ፣ እንከን የሚወጣለት አይደለም። “ጾምና ፆሎቱ፣ ምሕላና ጥሞናው ከልክ አለፈ፤ በጣም አበዙት” ካልተባለ በቀር፣ የተዋጣለት ንሥሃ ነው - ከክፋት መንገድ ወደ ቀና መንገድ የሚመልስ። የትንበያው አላማስ ይሄው አይደል? መዓቱን በንሥሃ ለማክሸፍ።
ዮናስ ግን በጭራሽ አልተደሰተም። ወይ መደሰት? ተቆጣ። ብስጭቱን የሚገልጸው ግን በፀሎት ነው።
“ወደ ጌታም ጸለየ። አቤቱ፣ እለምንሃለሁ። በአገሬ ሳለሁ የተናገርሁት ይህ አልነበረምን? አንተ፣ ቸርና ይቅር ባይ፣ ታጋሽም፣ ምህረትህም የበዛ፣ ከክፉው ነገርም የምትጸጸት አምላክ እንደሆንህ አውቄ ነበር። ስለዚህ ወደ ተርሌስ ለመኮብለል ፈጥኜ ነበር” አለ ዮናስ።
የክፋት መንገድ፣…. ካልተቃና በቀር፣ የጥፋት መዓትን እንደሚያመጣ፣ መቀመቅ እንደሚያወርድ፣ ምድርን በሶስት ቀን እንደሚገለብጥ ያውቃል። አይቀሬ እውነት ነው።
በንስሃ ወደ መልካም መንገድ መመለስ ደግሞ፣ መዓትን ያስቀራል፤ ያድናል። እራሱ ዮናስኮ፣ ከጨለማው የሞት ሆድ ውስጥ ወጥቷል። ከተማዋም ከመዓት እንደምትድን ቀድሞ ገምቷል። የትንቢቱ አላማ ትንቢቱን ለማክሸፍ እንደሆነ ከመነሻው ገብቶታል። ትንቢቱ ሲከሽፍ ደግሞ ከንቱ ሟርተኛ ያስብላል። ለዚህ ነበር ለሽሽት የተጣደፈው። አሁን፣ ጉዱን ውርደቱን በተግባር አየው።
“አሁንም፣ አቤቱ፣ ከሕይወት ሞት ይሻለኛልና እባክህ፣ ነፍሴን ከእኔ ውሰድ አለው” ዮናስ። በፀሎት መልክ የቀረበ ቁጣ ነው። “ጌታም፣ በውኑ ትቆጣ ዘንድ ይገባሃልን? አለ”።
ዮናስ መልስ አልሰጠም። ግን ንዴቱ አልበረደም። ለተግሳፅ ልቡን አልሰጠም። በእልህ ተይዟል። “በሶስት ቀን ትገለበጣች” ብሎ ከሻፊ ትንቢት ተናግሮ፣ በከንቱ ተዋርዶ ሊቀር? ባዶ እጁን ወደ አገሩ ሊመለስ? አያደርገውም።
ዮናስ፣ ከከተማይቱ ወጣ። ከተማይቱ የሚያገኛትን እስኪያይ ድረስ፣ በስተምስራቅ በኩል፣ ዳስ  ሰርቶ፣ ከጥላው ስር ተቀመጠ። ከተማዋ ስትገለበጥ ለማየት? ባትገለበጥ እንኳ፣ ክፉኛ በመሬት መንቀጥቀጥ ስትፈርስ ለማየት? ቢያንስ ቢያንስ ከተማዋ ስትንገጫገጭ ስትርድ፣ እሱ ከማዶ ሆኖ ለማየት? እስከዚያው ግን፣ ፀሐይ እንዲመታው አልፈለገም። ዳስ ሰርቷል።
ደግነቱ፣ ጥላ የምትጨምርለት ተክል፣ ከጭንቀቱ ልታድነው በቅላ ለመለመች። ዮናስ ተደሰተ። በማግስቱ ግን፣ ተክሏ በትል ተበልታ ደረቀች። ዮናስ ፀሐይ መታውና ተናደደ።
“ከሕይወት ሞት ይሻለኛል” አለ።
“…ትቆጣ ዘንድ ይገባሃልን?” አለው ጌታ።
“እስከሞት ድረስ እቆጣ ዘንድ ይገባኛል” ብሎ መለሰ።
“እንድትበቅል ላልደክምባት ላላሳደግሃት”… ተክል?
የነነዌ ሰዎች እንደ የአቅማቸው እድሜ ልክ ለደከሙበት ቤት ንብረትስ? ዮናስ፣ ፀሐይ ስለመታው ተናዷል። ግን “ቀኛቸውንና ግራቸውን የማይለዩ ከመቶ ሃያ ሺህ የሚበልጡ” የነነዌ ሰዎችስ፣ በመቅሰፍት ይሙቱ?
ይህንን እውነታ እንድናገናዝብ፣ እልህም ሆነ ሌላ ስሜት ህሊናችንን እንዳይጋርድብንል፣ መቼም ቢሆን በማንኛውም ሰበብ እንዳንስት፣ ሁሌም ከእውነትና ከቅንነት መንገድ እንዳንወጣ ትምህርት የሚሰጠን አስደናቂው ትረካ፣ በዚህ መልክ ነው የሚፈጸመው። አእምሮ ያለው ያስተውል ነው ነገሩ። እውነትም፣ በቅጡ ላስተዋለው፣ የዮናስ ትንቢት፣ እንደስሙ ለቀና ነው። ትንበያው ሰርቷል፤ ተሳክቷል። ትንበያው የከሸፈው ለምን ሆነና!


Read 10160 times