Monday, 26 July 2021 19:35

ግማሽ ሚሊዮን ዶላር የተገመቱት የጆ ባይደን ልጅ ስዕሎች እያወዛገቡ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ልጅ ሃንተር ባይደን በቅርቡ በዋይት ሃውስ በኩል ለጨረታ ሊያቀርባቸው ያቀዳቸው ሁለት ስዕሎች ጉዳይ ብዙዎችን እያወዛገበ እንደሚገኝ ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
ሃንተር ባይደን የሳላቸው ሁለት ስዕሎች በዋይት ሃውስ ለጨረታ ሊቀርቡ መሆኑንና እያንዳንዳቸው እስከ ግማሽ ሚሊዮን ዶላር ይሸጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆመው ዘገባው፣ ስዕሎቹ በሃንተር የፕሬዚዳንት ልጅነት ሰበብ በማይገባቸው ከፍተኛ ዋጋ እንዲሸጡ የተኬደበት መንገድ አግባብ አይደለም በሚል በብዙዎች ትችት እየቀረበባቸው እንደሚገኝ አመልክቷል፡፡
ስዕሎቹ ሙያዊ አካሄድን በተከተለ መልኩ በአርቲስቶችና ልምድ ባላቸው አጫራች ኩባንያዎች አማካይነት ለጨረታ መቅረብ ሲገባቸው ሰውዬው የፕሬዚዳንቱ ልጅ በመሆኑ ብቻ ስዕሎቹ በነጩ ቤተመንግስት አሻሻጭነት ለጨረታ መቅረባቸውና የተጋነነ ዋጋ እንዲያወጡ መደረጋቸው አግባብ አይደለም በሚል ብዙዎች ተቃውሞ ማሰማታቸውን ገልጧል፡፡
ዋይት ሃውስ የፕሬዚዳንቱ ልጅ ጉዳይ በአባቱና በአሜሪካ አስተዳደር ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳይፈጥር ለማድረግ ማቀዱን እንዳስታወቀ የተነገረ ሲሆን፣ ሃንተር ባይደን  በዩክሬንና ቻይና ያደረጋቸው የንግድ ስምምነቶች ከአባቱ ጋር በተያያዘ የጥቅም ግጭት ሲያስነሱ መቆየታቸውን በማስታወስ የስዕሎቹ ሽያጭም መሰል ጥያቄን ሊያጭር እንደሚችል አስነብቧል፡፡
የ51 አመቱ ሃንተር ባይደን በአንድ የኒው ዮርክ ጋለሪ አማካይነት ለጨረታ የሚያቀርባቸው ስዕሎች እስከ ግማሽ ሚሊዮን ዶላር ይሸጣሉ መባላቸው ብዙዎችን ማስገረሙን የጠቆመው ዘገባው፣ ከዚህ ቀደም ይህ ነው የሚባል የስነጥበብ ታሪክም ሆነ ችሎታ የሌለው ጀማሪ ሰዓሊ ለሰራቸው እዚህ ግባ የማይባሉ ስራዎች ዋጋው እጅግ መጋነኑን የሚናገሩ መኖራቸውንም ገልጧል፡፡


Read 1325 times