Sunday, 25 July 2021 00:00

ኳታር ኤርዌይስ የአመቱ የአለማችን ምርጥ አየር መንገድ ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ሊቨርፑል ከዩኔስኮ የአለም ቅርሶች መዝገብ ተሰረዘች

            ኤርላይን ሬቲንግስ የተባለው አለማቀፍ ተቋም የ2021 የፈረንጆች አመት የአለማችን ምርጥ 20 አየር መንገዶችን ዝርዝር ከሰሞኑ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ የአለማችን አቪየሽን ኢንዱስትሪ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ክፉኛ በተደቆሰበት የፈተና ጊዜ ስኬታማ ሆኖ የዘለቀው ኳታር ኤርዌይስ በአንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
ተቀማጭነቱ በአውስትራሊያ የሆነው ኤርላይን ሬቲንግስ በዘንድሮው ዝርዝሩ በሁለተኛነት ደረጃ ላይ ያስቀመጠው አየር መንገድ አምና በአንደኛ ደረጃ ላይ የነበረው ኤር ኒውዚላንድ ሲሆን፣ ሲንጋፖር ኤርላይንስ፣ ኳንታስ ኤሜሬትስ እና ካቲ ፓሲፊክ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
በ2021 የፈረንጆች አመት የአለማችን ምርጥ 20 አየር መንገዶች ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት ቀሪዎቹ አየር መንገዶች ደግሞ ቨርጂን ጋላክቲክ፣ ዩናይትድ ኤርላይንስ፣ ኢቫ ኤር፣ ብሪቲሽ ኤርዌይስ፣ ሉፍታንዛ፣ ኤኤንኤ፣ ፊናኤር፣ ጃፓን ኤርላይንስ፣ ኬኤልኤም፣ ሃዋያን ኤርላይንስ፣ አላስካ ኤርላይንስ፣ ቨርጂን አውስትራሊያ፣ ዴክታ ኤርላይንስ እና ኢትሃድ ኤርዌይስ ናቸው፡፡
ተቋሙ የአመቱን ምርጥ አየር መንገዶች ለመምረጥ ከሚጠቀምባቸው መስፈርቶች መካከል ትርፋማነት፣ ከ7 ኮከብ በላይ የደህንነት ደረጃ መያዝ፣ ለመንገደኞች ምቾት ፈጠራ የታከለበት አመራር መስጠት እንደሚገኝበትም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ አለማቀፍ ዜና ደግሞ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም ዩኔስኮ የእንግሊዟን ከተማ ሊቨርፑል ከአለም ቅርሶች መዝገብ መሰረዙንና ይህም የከተማዋን ከንቲባና ነዋሪዎችን ክፉኛ ማስቆጣቱን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ተቋሙ እ.ኤ.አ በ2004 በአለም ቅርስነት የመዘገባትን ሊቨርፑል ከዝርዝሩ ለማውጣት የወሰነው፣ የከተማዋን ጥንታዊነትና ውበት የሚቀንሱ የእግር ኳስ ስቴዲየምን ጨምሮ በርካታ አዳዲስ ህንጻዎች መገንባታቸውን ማረጋገጡን ተከትሎ እንደሆነም ዘገባው ገልጧል፡፡

Read 1029 times