Sunday, 25 July 2021 00:00

ኢሠመጉ በአስቸኳይ ሊሻሻሉ ይገባል ያላቸውን የመብት ጥሰቶች አቀረበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 በሃገሪቱ ዘርፈ ብዙ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች እየተፈፀሙ መሆኑን አረጋግጫለሁ ያለው የኢትዮጵያ ሠብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሠመጉ)፤ መንግስት አፋጣኝ እልባቶችን እንዲያበጅ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በጋዜጠኞች፣ በማህበረሰባዊ አንቂዎችና ግለሰቦች ላይ የሚፈፀሙ እስራቶች ህግን የተከተሉ መሆናቸውን መንግስት እንዲያረጋግጥ ያሳሰበው ኢሠመጉ፤ ታሳሪዎች ያሉበት አድራሻን ለቤተሰቦቻቸው ግልፅ እንዲያደርግ ጠይቋል፡፡
በህግ ተፈልገው እስራት እየተፈፀመባቸው ያሉ ግለሰቦች ያሉበት ቦታ አለመታወቁንና የታሳሪ ቤተሰቦች መጨነቃቸውን ያስታወቀው ኢሰመጉ፤ የክትትል ባለሙያዎችም የታሳሪዎችን አድራሻ አግኝተው የሰብአዊ አያያዝ ሁኔታቸውን መከታተል እንደተሳናቸው አመልክቷል። መንግስት በህገ መንግስቱ የተጣለበትን በህግ ጥላ ስር ያሉ ግለሰቦችን ደህንነት የማረጋገጥና በህጉ የተቀመጡ የእስረኞች አያያዝ ቅድመ ሁኔታዎች መሟላታቸውን ማረጋገጥ ይገባዋል ብሏል፤ ኢሠመጉ ለአዲስ አድማስ ባደረሰው መግለጫው፡፡
በጋዜጠኞች፣ ማህበረሰብ አንቂዎችና ግለሰቦች ላይ ከሚፈፀመው አስሮ የመሰወር ድርጊት ባለፈ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች አሁንም መቀጠላቸውንና ለዚህም መንግስት ዘላቂ መፍትሔዎችን እንዲያበጅ ተቋሙ  አሳስቧል፡፡
እየተፈፀሙ ካሉ ጥቃቶች መካከልም በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን ጃርቴ ወረዳ ውስጥ የአማራ ብሔር ተወላጆች በሸኔ ታጣቂዎች "በአካባቢው መኖር አትችሉም ለቃችሁ ውጡ" በሚል በዞኑ ባሉ አምስት ቀበሌዎች የእርሻ ስራቸው ሙሉ ለሙሉ እንዲወድም መደረጉን፣ ነዋሪዎቹ ለህይወታቸው ጭምር ዋስትና ማጣታቸውን ኢሰመጉ በመግለጫው አትቷል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በዞኑ ሰንቦ ጨፌ በተባለ አካባቢ ቀደም ባለው ሳምንት በርካቶች በሸኔ ታጣቂዎች እንደተገደሉና የተረፉት በሻምቡ በኩል አድርገው ወደ ተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች ለመሄድ ሲሞክሩ ተከልክለው ችግር ላይ እንደሚገኙ መረጃ ደርሶናል ብሏል-ኢሰመጉ በመግለጫው፡፡
በተጨማሪም፣ በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን አሙ ወረዳ ስር ከሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ በ11/11/2013 ዓ.ም ሌሊት ላይ በቁጥር ከ250 እስከ 300 የሚደርሱ በህግ ቁጥጥር ስር የነበሩ እስረኞች ከፖሊስ ማቆያ ጣቢያው በመውጣት የመሳሪያ ግምጃ ቤት በመግባት መሳሪያና ጥይት በመዝረፍ፣ ከሌሊቱ 6 ሰዓት እስከ  9 ሰዓት ድረስ ማንነት ለይተው በህዝብ ላይ ሲተኩሱ ማደራቸውን፣ በዚህም ከ30 ሺህ በላይ ዜጎች ከአካባቢው መፈናቀላቸውን፣ ተፈናቃዮቹ አሁንም የደህንነት ስጋት እንዳለባቸው ኢሠመጉ አመልክቷል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ሰዎች "ሸኔን ተባብራችኋል፤ ልጆቻችሁ ሸኔን ተቀላቅለዋል" እየተባሉ ፍ/ቤት ሳይቀርቡ ለበርካታ ጊዜያት በጠባብና በተጨናነቀ ክፍል ውስጥ እንደሚታሰሩና ለበሽታ እየተዳረጉ መሆኑን ተቋሙ በሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ መተከል ዞን ቡለንና ድባጤ ወረዳ አሁንም ከፍተኛ የሆነ የፀጥታ ችግር እንዳለ እንዲሁም ክልሉ ከአማራ ክልል በሚዋሰኑባቸው የቻግኒ ወረዳ አካባቢዎች በርካታ ከብቶች በህገ ወጥ ታጣቂዎች መዘረፋቸውን ኢሠመጉ አመልክቷል፡፡
በሌላ በኩል፤ በሐምሌ 4 ቀን 2013 በደቡብ ጎንደር ወረታ ከተማ ፎገራ ወረዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሶስት የትግራይ ተወላጆች በአካባቢው ሰዎች ተደብድበው መገደላቸውንና ከፍርድ ወጪ የሚፈፀሙ ወንጀሎች አሳሳቢ መሆናቸውን  በሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
በተጨማሪም፣ በትግራይ ክልል እድሜያቸው ለአካለ መጠን ያልደረሱ ታዳጊዎችና ህፃናት የጦር መሳሪያ አንግበው በጦርነት ውስጥ እየተሳተፉ ስለመሆኑ ኢሠመጉ መረጃዎች እንደደረሱትና ጉዳዩ አሳሳቢ መሆኑን አስታውቋል፡፡ እነዚህን ሁሉ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች መንግስት በተለያየ አግባብ እንዲያስቆም ኢሰመጉ በመግለጫው አበክሮ ጥሪ አቅርቧል፡፡ ለሰብአዊ መብት መከበር መረጋገጥ መንግስት ሃላፊነቱን እንዲወጣም መክሯል፡፡

Read 10460 times