Saturday, 08 September 2012 10:48

ሞት የገደለው ማንን ነው?

Written by  አለማየሁ ንጉሴ
Rate this item
(0 votes)

ጨረቃና ከዋክብትን፤ ሰማይና ምድርን፣ ሰውንና እንስሳውንም የማላይበት ጊዜ ይመጣል፡፡ የሚነፍሰውን ንፁህ አየርና የሚያማልል መስክ፤ ከአበባ ወደ አበባ የሚፈነጥዙትንም ቢራቢሮዎች ዳግመኛ አይቼ የማልደነቅበት ጊዜም ይመጣል፡፡ በዝንቦች የቀናት እድሜ ፌሽታ የምቀናበትም ወቅት… ያ ጊዜ ከሩቅ እንደሚሰማ አስፈሪ የዝናም ኮቴ ሲጮህ አይሰማኝም… ልጅ ሆኜ እናቴ እጅና እግሬን አስራ፣ በር በላዬ ላይ ዘግታ… አርጩሜ ቆርጣ ልትቀጣኝ ስትል እንደሚሰማኝ አይነት ፍርሃት ግን አሁን “የመጨረሻውን ጊዜዬን” ሳስብ አይሰማኝም፡፡ ቢሰማኝም ድምፁ እጅግ ሩቅ ከመሆኑ የተነሳ እንደ ትንኝ ትንፋሽ ፀጥ ያለ ይመስለኛል፡፡ ግን ፈፅሞ አልፈራሁም፡፡

የመኖር ጉጉቴን… የዘመን ምኞቴንና ጥልቁን የነፍሴን በህይወት የመኖር ናፍቆቴን ሊረሽን ቢመጣም ቅሉ አልፈራሁም፡፡ ለመፍራት፣ ለመንበቅበቅ፣ ለመርበትበት ከምክንያት በላይ የሆኑ ምክንያቶች ቢኖሩኝም አልፈራሁም፡፡

እኔ ብዬ ለመናገር እንኳን ድፍረት እንዳጣሁ ግን አልደብቅም፡፡ ይሄ አጣዳፊ ቀጠሮ እንዳለበት ሲሮጥ የሚመጣው “ፈፃሚው ጊዜ” ገድሎ የሚሄደው… በሬሳዬም ላይ ፎክሮ የሚራመደው ስጋዬን ብቻ እንዳልሆነ ይገባኛል፡፡ እንደ አድዋ ዘማች ወታደር “ዘራፍን” ስንቅ አርጐ፣ አንገቴን እንቅ አድርጐ፣ የእስትንፋሴን ያበጠች ፊኛ ለማስተንፈስ ሲሮጥ… የሚያጠፋው አይኔን ብቻ፤ ዝም የሚያሰኘው አንደበቴን ብቻ፤ አሳስሮ የሚያስቀምጠው እጅና እግሬን ብቻ… የሚያናጥበው እስትንፋሴን ብቻ፤ የሚከላው የፀጉሬንና የጥፍሬን እድገት ብቻ፤ አይደለም፡፡ እኔን ነው የሚገድል፡፡

በቃ እኔ የለሁም፡፡ አለም በኔ አይንና ጆሮ… በማስተዋሌም ካልተስተዋለች… የት አለች? አይኖቼን ከጥልቁ ህዋ ላይ ካላመላለስሁ… ለእጁም ስራ እጅ ካልነሳሁ… የታለሁ? እጆቼ ከእግሮቼ ጋር አብረው ለፍጡሩ ሁሉ ደግ ከመዋል ከቦዘኑ ምን ፈየዱልኝ? ታፍሶ በተሰጠኝ የጤና በረከት ተፍነክንኬ… ብን ብን ለምትለው ነፍሴ የታደላትን እፁብ ጥበብ አድንቄ… ከወገቤ እንዳደገደግሁ “አሜን!” ካላልሁማ ምን ተረፈኝ?

“ሞት” የሚንደረደርብኝ ይህን ሁሉ ለማጥፋት ነው፡፡ ከውስጤ ፈልቆ የሚወጣውን ምንጭ በጠፋ የሰው ልጅ ያለማስተዋል ባድማ ላይ ሳልረጭ ምን ሊሆን መጣ ሞት? ማን ሲያካልብ ሰደደው? እስክሞት ድረስ ለመኖር ብቻ ነበር እስካሁን የቆየሁት ማለት ነው? እኔኮ…

በአንድ በማላውቀው የሰው ልጅ ሞት ስቅስቅ ብዬ አለቅሳለሁ፡፡ ድንበር ለይቶ ላራቀው፣ እንጀራ ጐትቶ ለነጠለው… ተፈጥሮ አርቃ ላሰፈረችው፣ ለማየውም ለማላየውም ለዚያ የሰው ፍጥረት ህልፈት እንሰቀሰቃለሁ፡፡ ከጐኔም ከሩቄም በእንስቶች የሆድ ጐጆ ለወራት ተጠልሎ… ህይወትን ከኛ ጋር ሊጋራ ለሚመጣው አዲስ ጨቅላ… ለማየውም ለማላየውም እንደተደሰትሁ ነኝ፡፡ እንደሳቅሁ፡፡

እኔ የምሞተው…

አለምን አዝዬ ነው፡፡

እኔ የምኖረው…

አለምን ይዤ ነው፡፡

ማነው የህይወትን እያንዳንዱን ክዋኔ ከህልፈቴ በኋላ፣ “እንዲህ እንዲህ ሆነ፣” እያለ ደርዝ አስይዞ የሚነግረኝ? ከአይኔ ትቼያቸው የሄድኩት እኒያ ያማሩ መስኮች እንደምን ውለው እንዳደሩ የሚያስረዳኝ? ከጐረቤቶቼ እንስቶች የተወለዱት ትንንሽ የሰው ፍጥረቶች… ትልልቅ የዋህነታቸውን በሳቃቸው ውስጥ እንደያዙ በሜዳው ላይ ሲሯሯጡ እንደዋሉ… ከመሃከላቸው የትኛው አባራሪ የትኛው ተባራሪ፣ የትኛው ልጅ እንደወደቀ የትኛውስ እንዳለቀሰ፣ ማን ከሞት እንቅልፍ ቀስቅሶ ይነግረኛል…?

ጀርባዋን አሸት አሸት አድርጌ የማባብላት ጊደሬ ለቀኑ የምትሰጠኝ ወተቷ ስንት ጆግ ተቀዳ? - ነፋስ በማን አለብኝነት ሲነፍስ፣ የቀዬውን የገብስ ነዶ ሲያዘናፍል፣ የጐልማሶችን ባርኔጣ ሲነጥቅ… ደመናው ከሰማይ በታች እንዳረበበና ሳንፈልገው እንደከበበን… በመከርም እንደመጣብን… ‘ያዝልን! ያዝልን’ ብለን፣ ከደጀ ሰላሙ ውለን አድረን እንደገባን… የፀሎታችን ቃላቶች ክንፍ አብቅለው፣ በረው፣ ከእግዜሩ ዙፋን ስር አረፉ ወይስ በመላእክት እጆች ላይ ቀርተው ነጠፉ? በረሃብ ስጋት ስንዋልል… ልባችን ቅም እንዳለችስ ማን ቀስቅሶ ይነግረኛል?

…በውሃ ቀጠነ የሀገሬን ጐኗን የሚተገትግ፣ ያ የክፉ ሀገር ጐረቤትስ የሰበቀውን ጦር ሰበሰበ ወይስ አውገርግሮ ተከለባት? እኒያ የደረሱ ጐበዛዝት ጐረምሶች በአካኪ ዘራፍ ተጠምደው ዋሉ? የመንደራችን ቆንጆ ኮረዶችስ በማጀት ስራ… በበሶ ጭበጣ ቀልባቸውን አጡ? አልያስ ከዚህ ሁሉ የጦር ወሬና ድግስ… ሽርጉድ መሃል ዘንባባ ባፏ የነከሰች… የደመና ውርዴ የመሰለች እርግብ ሰማዩን አቋርጣ ስትበር የጠላትም የወዳጅም አይኖች ተንጋጠው አዩ? ”ይቅር ለግዚሀር” ነው የመለሳቸው? - ማን ነው ሚነግረኝ?

ሞት የገደለው እኔን ነው፡፡ ሞት የገደለው አለሜን ነው፡፡ አለሜም ህይወት ነበረች፡፡ እስትንፋስ፡፡ እስትንፋስም የህያውነት ሀሁ…፡፡

አሁንኮ…

የምወደውን ባለቅኔ ድምፅ እንዳልሰማ ነወ ያረገኝ ሞት፡፡ “ሞትም ይሙት - የታባቱ” ብዬ በአንደበቴ እንዳልወርደው… አየሩንም ሞልቶ የእረኞችን ልብ እስኪያሸፍት ድረስ እንዳይሰማ… እንዳይነሽጥ እኮ ነው ያደረገኝ፡፡…

አዛውንቱ… ከአጥራቸው ስር ከተጐለተው ትልቅ ቋጥኝ ላይ አረፍ እንዳሉ ያጫወቱኝን ወግ… ያስደመጡኝ የኑሮ ተረት… እናቴ በ”መሽቷል ግባ” አናጥባኝ… የጨዋታቸውን ጫፉን እንደያዝሁ፣ እንደጣመኝ፣ ነግቶ እስክፈጥመው እንደጓጓሁ… ማን ነው? ማን አለ መቃብሬን ምሶ ወጉን የሚቀጥልልኝ?

አይኑን እንደጨፈነ…

በመረዋ ልሳን ሲያንጐራጉር የሚውል የሚያመሽ ያ አዝማሪ፣ ይህ ተጉሮሮው የዋለ ሞገደኛ ድምፅ ከየት ነው የተለገሰው? ምስጢሩን ሳልገልጠው…

አይኔን እንደገለጥሁ…

በሰማይ ሰሌዳ ላይ የተዘሩት ክዋክብት የብርሃን ቅኔዎች… በብርሃን የተፃፉ ናቸው፡፡ ግዙፏ ድምቀት… ፀሀይ… የቅኔዎች ሁሉ ማሰሪያና መደምደሚያ አራት ነጥብ፡፡ ጨረቃ… ነገን ሊንቦገቦጉ… ነገን ሮጠውት ዛሬን ሊደርሱ ጓጉተው እሚከጅሉ… በጥበብ ሲቃ ጉሮሮአቸው የተያዘ “መጭ ተቀኚዎች”… ደብዛዛ ብርሃኖች… የጀምበር የሩቅ ተጐራባቾች፡፡

ኮከቦችን ወግ አስይዛችሁ አንብቧቸው እስቲ፡፡ በጌታ የተከወነ ደግነት፤ በእግዜር የተቀናጀ የእርስ በእርስ ትስስርና ምስጢር… በተንቀሳቃሹ ፍጥረት ያደረ ፍቅር… በግዑዝ ተፈጥሮ የተገለፀ ድንቅ ውበት… ከምድር ተንፀባርቆ በክዋክብት ፊደላት ከሰማይ ሰሌዳ ላይ በግጥም መልክ በአጭር በአጭሩ ተፅፎ፣ ሊጨረስ በማይችል መአት ስንኝ ተከትቦ፡፡

ተመልከቱ…

ለርህራሄና ለደግነት የተሰራው ሰው… በዘመኑ ሙሉ ገብሮት ያለፈውን የፈጣሪውን ዓላማ፡፡ በወግ በወጉ ሲነበብ፤ ትንታግ ፈጥሮ ሲደምቅ፡፡ ለማንም ለምንም በሚታይ ድምቀት፡፡ ምራቅ በሚያስውጥ የጥበብ ውበት፡፡

ተመልከቱ…

ለፍቅርና ለመረዳዳት የተፈጠረው ሰው… በዘመኑ ሙሉ ገብሮት ያለፈውን “የክፋት አላማ” በሰማይ ሰሌዳ ላይ ተዘበራርቆ ሲነበብ፡፡ እልም ስልም በሚል… አይንን በሚከስ ንባብ፡፡ እልፍ በደሎችን አይተው… መልሰው ያንፀባረቁ ከዋክብት ከትዝብታቸው ማየል የተነሳ፤ ከንዴታቸውም ግለት የተነሳ፤ ነደውና ተቃጥለው… አጥፊውን ሊቀጡ፣ በዳዩንም ሊያጠፉ ቁልቁል ሲሮጡ፡፡ ተወርዋሪ ኮከቦች ደረሱ፡፡ ግፈኞች በራቸው በጠንካራ መሸንጐሪያ ተዘግቶም ቢሆን… በጣራቸው ሽንቁር “የቅጣት መቀበያ” የፍርድ መሹለኪያ ቀዳዳ ግን አለ፡፡

ደግና የዋሆች ለሽልማታቸው ሳይበቁ፣ የየዘመኑ አጥፊና በዳዮች ለፍርድ ሳይቀርቡ… ምድርም መፍካቷን… መለምለሟን ሳላይ… ሞት የገደለው እኔን ነው፡፡ አለሙን ነው፡፡ ሁሉን፡፡

 

 

Read 1139 times Last modified on Saturday, 08 September 2012 11:03