Saturday, 24 July 2021 00:00

እናት ፓርቲ ለሰሜኑ ግጭት የሰላም ጥሪ አቀረበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

  በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል ከእለት ወደ እለት እየተባባሰ የመጣው ግጭት መፍትሔ አልባ ወደሚሆንበት ደረጃ ሊሻጋገር ይችላል የሚል ስጋት እንዳለው የገለፀው እናት ፓርቲ፤ በግጭቱ ቀጥተኛ ተሳታፊ ለሆኑና ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሠላም ጥሪ አቀረበ፡፡
“መላ ኢትዮጵያውያን አሁን በህዝባችን ላይ እየደረሰ ያለውን ዘውግ ተኮር፣እጅግ ፈታኝ የሆነ የእርስ በእርስ ግጭት እንዲሁም ግድያና መፈናቀል እንዴት መፍታት አቃተን?; ሲል የጠየቀው የፓርቲው መግለጫ፤ መላው ህዝብ  ከጦርነት ሥነልቦና ወጥቶ ስለ ሠላም እንዲያስብ ጥሪ አቅርቧል፡፡
እናት ፓርቲ በዚሁ ሰፋ ያለ መግለጫው፤ ለፌደራል መንግስት፣ ለትግራይና አማራ ክልል ህዝብ፣ ለመገናኛ ብዙኃንና ለአክቲቪስቶች ለአማራና ትግራይ ክልል ወጣቶች፣ ለሃይማኖት አባቶችና ለሃገር ሽማግሌዎች፣ በአሸባሪነት ለተፈረጀው የህወሓት ቡድን፣ ለአማራ ክልል መንግስት እንዲሁም ለአለማቀፍ ማህበረሰብ ባቀረበው የሰላም ጥሪ ሁሉም  የየራሱን ድርሻ እንዲወጣ ተማፅኗል፡፡
የፌደራሉ መንግስት የሰብአዊ መብቶችን ሁኔታ በጥብቅ እንዲያስከብር፣ ዜጎችን ያለ ምክንያት ማሠርና ማዋከብ እንዲያቆም አለም አቀፍ ጫናውን ብቃቱና ልምዱ ባላቸው ባለሙያዎች እየተመራ መቋቋም የሚያስችሉ የረጅምና የአጭር ጊዜ ስልቶች እንዲቀይስና ሌሎች ለሠላም ጠቃሚ የሆኑ እርምጃዎች እንዲወስድ ፓርቲው ጠይቋል፡፡
በክልሎች መካከል የሚነሱ የወሰን ግጭቶችን በዘላቂነት መፍትሔ እንዲያገኙ ለማስቻል ሁሉን አቀፍ ውይይት በማካሄድ ጎሳ ተኮር ፖለቲካውን በመሰረታዊ  መልኩ ለመለወጥ የሚያስችሉ የህገ መንግስት ማሻሻያ ለማድረግ መንግስት ከወዲሁ እንቅስቃሴ እንዲጀምር ጠይቋል፤ እናት ፓርቲ፡፡
ለትግራይና አማራ ህዝብ ባቀረበው ጥሪም፤ ሁለቱ ህዝቦች በታሪክ፣ በባህል በእምነትና ወግ ያላቸውን አንድነት አስጠብቀው እንዲያስቀጥሉና ጦርነቱ ለትውልድ ቁርሾ ሳያስቀምጥ ከወዲሁ የሚቀጭበትንና ሠላም ወርዶ ማህበራዊ መስተጋብር በሚመለስበት ጉዳይ ላይ እንዲሰሩ  ለሃገር ሽማግሌዎችና ለሃይማኖት አባቶች ፓርቲው ጥሪ አቅርቧል፡፡

Read 11210 times