Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 01 September 2012 12:16

“ጠ/ሚኒስትሩ በቀደዱት ፈር እንጓዛለን”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አንደኛ ፅኑ፤ ሁለተኛ ታታሪና የማይደክሙ፤ ሶስተኛ የለውጥ አነሳሽ የነበሩ ታላቅ መሪ ናቸው፡፡ በአገራችን ለረጅም ግዜ ተንሰራፍቶ የቆየን ድህነት እና ስንፍና በስራ ትጋት እና በላቀ ታታሪነት ለመለወጥ የታገሉ መሪ ናቸው፡፡ ፓትሪያርክ አቡነ ጳውሎስም ለብዙ የለውጥ ምዕራፎች ምክንያት የነበሩ የኃይማኖት መሪ ናቸው፡፡ እናም በዚህ ሰሞን ሁላችንም ያጣነው እነዚህን  ሁለት የለውጥ ፊት አውራሪዎችን ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ታላላቅ ሰዎች የስራ እና የእድገት ጥረትን አስታጥቀውናል፡፡ የእነሱን አደራና ሃላፊነት ተሸክመን ወደፊት መገስገስ ይገባናል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊንና አቡነ ጳውሎስን በአንድ ሰሞን ማጣታችንን ሳስበው ግራ እጋባለሁ፡፡ ከእነሱ ማለፍ በኋላስ? ብዬ እጨነቃለሁ፡፡ ግን አንድ ነገር አለን፤ አሁን ያለችው ኢትዮጵያ ከእነዚህ ሁለት ታላቅ ባለራዕዮች የተረከብናት ናት፡፡ እነሱን በማጣታችን ግን ከጀመርነው የልማት አቅጣጫ ለአፍታ እንኳን መዘናጋት የለብንም፡፡  የየትኛውንም ትውልድ አገራዊ ሃላፊነትን በስፖርቱ ካለው የዱላ ቅብብል ውድድር ጋር በማመሳከር ልገልፅልህ እችላለለሁ፡፡ በቅርቡ በተካሄደው የለንደን ኦሎምፒክ ጃማይካውያኑ የአጭር ርቀት ሯጮች  እነ ዩስያን ቦልትና ዮሃን ብሌክ በ4 x 400 ሜትር ውድድር የወርቅ ሜዳልያ ሲወስዱ የዓለም ሪከርድ ሰብረው ነበር፡፡ እነዚህ ሯጮች በዚያ የኦሎምፒክ ውድድር ሲሰለፉ አንድ የጋራ አላማ ነበራቸው፡፡ ለጃማይካ የወርቅ ሜዳልያ በማስገኘት እና የዓለም ሪከርድን በመስበር ታሪክ መስራት፡፡ የኢትዮጵያን እድገት በዚህ የዱላ ቅብብል ሩጫ ልመስለው እፈልጋለሁ፡፡ ለኢትዮጵያ ለውጥ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በቅብብል ሩጫው የመጀመርያው ተነሺ ሆነዋል፡፡ አሁን ያለው ትውልድ በሁለተኛነት ዱላውን ተቀብሏል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጀመርያው ዙር ያለ የሌለ ሃይላቸውን ተጠቅመው ያቀበሉትን ዱላ፣ ይህ ትውልድ ደግሞ ያለ የሌለ ሃይሉንና አቅሙን ተጠቅሞ ዙሩን በማክረር ለቀጣዩ ትውልድ ማቀበል ይጠበቅበታል፡፡ ያ ተረካቢ ትውልድም የራሱን ዙር በተሻለ ፍጥነት ሸፍኖ፣ ለአራተኛው እና ለጨራሹ ትውልድ ማቀበል ይኖርበታል፡፡ አጨራረሱም ያማረ ሲሆን ሪከርድ ይሰበራል፡፡ ውድድር የምንገባው በጥሩ ሰዓት ለመጨረስ፣ ለማሸነፍ እና በድል ነፀብራቅ ለመድመቅ መሆን አለበት፡፡ በእድገት የዱላ ቅብብል  ስንወዳደር በመንቀራፈፍ ከመስመራችን ወጥተን ከውድድር ውጭ እንዳንሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ በከፍተኛ ሞራልና ቁርጠኝነት በገባንበት ውድድር ሁላችንም የምንችለውን ያህል ካደረግን፣ የምንሰብረው ሪከርድ አንድም ድህነትን ማጥፋት፤ ብሎም የህዳሴውን ግድብ መጨረስና ኢትዮጵያን መካከከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ማድረስ ይሆናል፡፡

አንድ ሆላንዶች የሚጠቅሱትን አባባል ልንገርህ፡- ጎበዝ ሰው ሁሌም ጣቱን የሚቀስረው በራሱ ላይ ነው ይላሉ፡፡ ሰነፎች ግን ላለባቸው ችግርና ድክመት ጣታቸውን የሚቀስሩት በሌላው ላይ ነው፡፡ ስለዚህም እኛ ኢትዮጵያውያን ለድህነታችን፤ ለኋላቀርነታችንና ለድክመታችን ሌላው ላይ ጣታችንን መቀሰር የለብንም፡፡ ችግር ካለብን ድክመት ከተሰማን ሌላውን ምክንያት ማድረግ የለብንም፤ ጉብዝናችንን የምናሳየው ከስህተቶቻችን ራሳችን ተምረን፤ ለድክመቶቻችን ራሳችንን ተጠያቂ አድርገን፣ ለተሻለ ለውጥ ስንሰራ ብቻ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለስፖርቱ በነበራቸው ትኩረትና አድናቆት ሁሌም እማረክ ነበር፡፡  ከቤጂንግ ስንመለስ እንዲህ ብለው ጠየቁኝ “ለምንድነው በስፖርቱ ብዙ ወጣቶች የማይመጡት? ችግሩ ምንድነው?” በስፖርቱ ብዙ ጀግኖችን ለማፍራት ለወጣቶች ማሰልጠኛ የሚሆን አካዳሚ ቢኖር ብዬ እኔም ሌሎችም ሃሳብ አቀረብን፡፡ ይህንን ምክራችንን ሙሉ ለሙሉ ተቀብለው አስቸኳይ ትእዛዝ ሰጡ፡፡ ይህ ውሳኔያቸውም ቦሌ አካባቢ በሚገኘው ትልቅ ሜዳ ላይ በ300 ሚሊዮን ብር፣ ምናልባትም ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ እና የመጨረሻ ስራዎች ሲከናወኑለት እስከ 600 ሚሊዮን ብር ይፈጃል ተብሎ የሚገመት የስፖርት አካዳሚ መገንባቱ እውን ሆነ፡፡ ይሄው የስፖርት አካዳሚ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አስቸኳይ ትእዛዝ ሲገነባ ቆይቶ፣ በሚቀጥለው አመት ታዳጊዎችን በመቀበል ስራ ሊጀምር ነው፡፡ የስፖርት አካዳሚው ከፍተኛ ደረጃ ያለው ከመሆኑም በላይ በጥራቱ በእንግሊዝ፤ በፈረንሳይና በጣሊያን እንኳን ያላየሁት ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እኛ አትሌቶች ከተሳተፍነባቸው ሁሉም ኦሎምፒኮች ወደ አገራችን ስንመለስ አንዴም ሳይቀሩብን በክብር ተቀብለው አመስግነውናል፡፡ ይሄው ትኩረታቸው ለሁላችንም ትልቅ መነሳሳት ፈጥሮብናል፡፡ በየኦሎምፒኩ ከእኔ ጋር የነበራቸውን አንዳንድ ንግግሮችንም አልረሳቸውም፡፡ በሲድኒ ኦሎምፒክ ከፖል ቴርጋት ጋር ያደረግሁትን ትንቅንቅ አስመልክቶ በሰጡኝ አስተያየት፣ አስቀድመህ መውጣትና ማሸነፍ እየቻልክ እስከመጨረሻው ተናንቀህ ለምን አስጨነቅኸን ብለውኝ ነበር፡፡ እኔም በውድድሩ ያለኝን ሁሉ ጉልበት አሟጥጬ በእልህ ማሸነፌን ገለፅኩላቸው፡፡ ከአቴንስ ስመለስ ደግሞ “ምነው ወርቁን ጥለህ መጣህ?” ነበር ያሉኝ፡፡ ቤጂንግ ላይ ጠብቁኝ ነበር ምላሼ፡፡ ከአቴንስ ስንመለስ እኔና ደራርቱ ከእሳቸው ዘንድ ልዩ ተሸላሚዎች ነበርን፡፡ በወቅቱ በኮከብ ቅርፅ የተሰራ የክብር ሜዳልያ የሸለሙን ክቡር መለስ ዜናዊ፤ ለኢትዮጵያ አትሌቶች በሰራችሁት የፈር ቀዳጅነት ሚና ትመሰገናላችሁ ብለው ነበር፡፡ከእንግዲህ ቃል የምገባው በስፖርቱ፣ በኢንቨስትመንቱ እና በሁሉም መስክ የያዝኩትን ለመቀጠል ነው፡፡ እኔም ብሆን እንደ ለውጥ ፊት አውራሪዎቻችን ማለፌ አይቀርም፡፡ ግን ማለፍ የምፈልገው ህያው ተግባራትን ሰርቼ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የውዴታ ግዴታዬ ነው፡፡ ሰዎች ይወለዳሉ፤ ይሰራሉ፤ ያልፋሉ፡፡ ህያው ተግባር የሰሩ ግን እድለኞች ናቸው፡፡ የዚህን አርዓያነት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በተግባር አሳይተውናል፡፡ እኛም እሳቸው በቀደዱት ፈር እንጓዛለን፡፡ ይህን ስል ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ከልቤ የማስተላልፈው መልእክት አለ፡፡ ለአገራችን ጥሩ እና ህያው ተግባር እንስራ፤ ቢያንስ ጥሩ ነገር ማድረግ ባንችል እንኳን መጥፎ ከመስራት እንቆጠብ፡፡

(አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ)

 

 

Read 2720 times Last modified on Saturday, 01 September 2012 12:20