Wednesday, 21 July 2021 00:00

10 በመቶ የአለም ህዝብ የረሃብ ሰለባ መሆኑ ተነገረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

     በ2020 በየደቂቃው ረሃብ 11 ሰዎችን፣ ኮሮና 7 ሰዎችን ገድሏል

           ባለፈው የፈረንጆች አመት 2020 በአለም ዙሪያ የሚገኙ 811 ሚሊዮን ሰዎች ወይም ከአጠቃላዩ የአለም ህዝብ 10 በመቶ የሚሆነው የረሃብ ሰለባ መሆኑን እንዲሁም 2.37 ቢሊዮን ሰዎች የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሰለባ መሆናቸውን ተመድ ከሰሞኑ ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል፡፡
የአለም የምግብ ፕሮግራምና የጤና ድርጅትን ጨምሮ አምስት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቋማት በጋራ ባወጡት በዚህ ሪፖርት፤ በመላው አለም የረሃብ ሰለቦች የሆኑ ሰዎች ቁጥር ባለፈው አመት ከነበረበት በ161 ሚሊዮን በመጨመር 811 ሚሊዮን መድረሱን የገለጹ ሲሆን ከአለማችን ህጻናት መካከል 22 በመቶ የሚሆኑት ወይም 149 ሚሊዮን ህጻናት የመቀንጨር ችግር ሰለቦች መሆናቸውንም አመልክቷል፡፡
በአፍሪካ የረሃብ አደጋ ሰለቦች ቁጥር ባለፈው አመት በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ በአመቱ በአህጉሪቱ 282 ሚሊዮን ሰዎች የረሃብ አደጋ ሰለቦች መሆናቸውንም ገልጧል፡፡
የኮሮና ወረርሽኝ፣ የምግብ እህሎች ምርት መቀነስ፣ የእርስ በእርስ ግጭቶችና የኢኮኖሚ ቀውሶች ለምግብ እጥረት ችግሩ መባበሳስ በምክንያትነት እንደሚጠቀሱ የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ለጋሽ አገራት ለድሃ አገራት የሚሰጡትን የምግብ ድጋፍ መቀነሳቸውም ችግሩ እንዲባባስ ማድረጉን ሪፖርቱ አብራርቷል፡፡
ኦክስፋም ኢንተርናሽናል የተባለው አለማቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት በበኩሉ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባወጣው ሪፖርት፣ በአመቱ በኮሮና ሳቢያ ከሞቱት ይልቅ በረሃብ ሰበብ ለሞት የተዳረጉት ሰዎች ቁጥር እንደሚበልጥ የገለጸ ሲሆን፣ ኮሮና በየደቂቃው 7 ሰዎችን ሲገድል ረሃብ ግን 11 ሰዎችን መግደሉን አመልክቷል፡፡

Read 2451 times