Print this page
Monday, 19 July 2021 00:00

የጋና ቀዳማዊት እመቤት በአበል የተከፈላቸውን 151 ሺህ ዶላር ሊመልሱ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የጋና ፓርላማ ባለፈው ሳምንት ለአገሪቱ ቀዳማዊት እመቤቶች የወሰነው የደመወዝ ጭማሪ የአገሪቱን ዜጎች ማስቆጣቱንና ትችት ማስከተሉን ተከትሎ፣ የአገሪቱ ቀዳማዊት እመቤት ርብቃ አኩፎ አዶ ባለቤታቸው ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ አንስቶ ለአራት አመታት ያህል በአበል መልክ የተከፈላቸውን 151 ሺህ 618 ዶላር ሙሉ ለሙሉ እንደሚመልሱ ማስታወቃቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የጋናው ፕሬዚዳንት አኩፎ አዶ መንበረ ስልጣኑን ሲቆናጠጡ አብረዋቸው ወደ ቤተመንግስት የገቡት ርብቃ፣ ፓርላማው ለእሳቸውና ለምክትል ፕሬዚዳንቱ ባለቤት የደመወዝ ጭማሬ ማድረጉ አግባብ አይደለም የሚሉ ወቀሳዎች መበራከታቸውን ተከትሎ በሰጡት መግለጫ፣ አበል ክፈሉኝ ብዬ አይደለም ሲከፍሉኝ የኖሩት፣ የወሰድኩትን ገንዘብ አንድም ሳላስቀር ለሚመለከተው የመንግስት አካል እመልሳለሁ ማለታቸውን ነው ዘገባው ያስነበበው፡፡
ቀዳማዊት እመቤቷ አበሉን እንደሚመልሱ ከመናገራቸው ባለፈ ፓርላማው በቅርቡ ያጸደቀላቸውን አዲስ ደመወዝ እንደማይቀበሉት ማስታወቃቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ፓርላማው ለእሳቸውም ሆነ ለአገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ባለቤት የወሰነላቸው ወርሃዊ ደመወዝ 3 ሺህ 500 ዶላር እንደሚደርስና ይህም ከአገሪቱ ሚኒስትሮች ደመወዝ ጋር እኩል መሆኑንም አመልክቷል፡፡
በተያያዘ ዜና ደግሞ፤ ናይጀሪያ ከቅኝ አገዛዝ ነጻ ከወጣች በኋላ በነበሩት 61 አመታት በሙስና ሰበብ በድምሩ 582 ቢሊዮን ዶላር ያህል ማጣቷን ዋይአይኤጂኤ የተባለ አንድ የአገሪቱ ተቋም ከሰሞኑ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡
ተቋሙ ይፋ ባደረገው መረጃ እንዳለው፣ ከአለማችን 179 አገራት በሙስና መስፋፋት 30ኛ ደረጃን በያዘችው ናይጀሪያ ከፈረንጆች አመት 2011 እስከ 2015 ተጨማሪ 1.3 ትሪሊዮን የመንግስት ገንዘብ በህገወጥ መንገድ ከአገር እንዲወጣ መደረጉን በጥናት ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡

Read 2641 times
Administrator

Latest from Administrator