Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 01 September 2012 12:11

የያኔው ተማሪ ለገሰ ዜናዊ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ጊዜው 1966 መጨረሻ ላይ ሲሆን ዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ኮንግረስ የአመራር አባላትን የሚመርጥበት ወቅት ነበር፡፡ ሰሞኑን ህልፈተ ዜናቸው የተሰማው ጠቅላይ ሚ/ር መለስ ዜናዊ (የያኔው ተማሪ ለገሠ ዜናዊ) የሳይንስ ተማሪዎች እጩ ተመራጭ በመሆን ምስላቸው በየዛፉ ላይ ሳይቀር ተለጣጥፏል፡፡ በዘመኑ ከነበሩት አብዮተኞች  ተርታ በቀዳሚነት የሚሰለፉት መለስ ዜናዊ፤ ለምረጡኝ ቅስቀሳ ያደረጉት ንግግር ለየት ያለና ብዙዎችን አፍ ያስከተፈ እንደነበር ይነገርላቸዋል፡፡ ተወዳዳሪዎቹም ሆኑ የተማሪ እንቅስቃሴ አካል የነበሩት በሙሉ ይታወቁ የነበረው “Ism” በምትለው  ቃል ሲሆን ንግግሮቻቸው በሙሉ “Marxism, Socialism…” በሚል የታጀበ ነበር፡፡ “Ism”  በነገሠበት በዚያ ዘመን መለስ ንግግራቸውን በተለየ መንገድ ነበር ያቀረቡት፡፡ እንደ ሌሎቹ ጓደኞቼ እና አጋሮቼ “Marxism is…” በሚል ስለማርክሲዝም ምንነት አልነግራችሁም፤ አሉና ንግግራቸውን በ“Ism not” ጀመሩት፡፡

“ሁለት መልዕክቶችን ይዤላችሁ መጥቻለሁ” ያሉት መለስ ንግግራቸውን ሲጀምሩ፤ አንዲት የናዝሬት ስኩል ተማሪ ድሀን እንዴት እንደገለፀችው በመጥቀስ ሲሆን በመቀጠልም በወቅቱ በቀን ሶስት ጊዜ ስለሚነገር የሬዲዮ ማስታወቂያ ነው የተናገሩት፡፡ ተማሪው ሁሉ ታዲያ ፈዞ የመለስን ንግግር ያዳምጥ እንደነበር የሚያውቋቸው ያስታውሳሉ፡፡ የናዝሬት ስኩል ተማሪዋ ድሀን ስትገልፀው፤ “ትንሽ ቪላ ውስጥ የሚኖር፣  21 ኢንች ቴሌቪዥን፣ ቤቢ ፊያት መኪናና አንድ የቤት ሠራተኛና አንድ ዘበኛ ብቻ ያለው ነው” ማለቷን ተናግረው ሲጨርሱ ጭብጨባው ጦፈ፡፡ ጭብጨባው ሲረግብ ይህን የድህነት ትንታኔ ከትግራይና ከወሎ ረሀብተኞች ጋር አነፃጽሩት፣ ስጋቸው ተልሶ አጥንታቸው ከሚታየው፤ እዚሁ አራት ኪሎ ፓርላማችን ፊት ለፊት ከሰፈሩ ረሃብተኞች ጋር አስተያዩ አሉ - መለስ፡፡

ሁለተኛው የንግግራቸው ጭብጥ በወቅቱ በሬዲዮ በቀን ሶስት ጊዜ ማስታወቂያ ይተላለፍለት ስለነበር “አልካሴ ልዘር” የተባለ ቁንጣን ማስተንፈሽያ መድሃኒትን የተመለከተ ነበር፡፡ ምግብ በልተው ቁንጣን ሲይዝዎት ዘና የሚያደርግ፣ ምግብ እንዲንሸራሸርልዎትና ከቁንጣን እፎይ እንዲሉ የሚያደርግ አልካሴልዘር የሚለውንም ማስታወቂያ ከወሎ እና ከትግራይ ረሃብተኞች አንፃር እዩት ያሉት ተወዳዳሪው መለስ፤ “እኔ እዚህ የመጣሁት …Ism… ለማለት አይደለም” ብለዋል፡፡

“ልናገር የመጣሁት ሁለት መሬት የነኩና የተጨበጡ ማሳያዎችን ነው፤ ምክንያቱም ያለነዚህ ነገሮች “Ism” አይኖርም”፤ ረሀቡን የካደው ፓርላማችን የት ነው ያለው? እኔ ዛሬ እዚህ የማወራው ስለተማሪ ንቅናቄ ሳይሆን ስለወሎ እና ትግራይ ረሀብ ነው፡፡ የማወራው ስለሚሞቱ፤ ስለሚያልቁ ረሀብተኞች ነው፡፡ ይህን ፈተና ለመጋፈጥ እና ለዚህ መስዋዕትነት ለመክፈል ነው ከፊታችሁ የቆምኩት” አሉና ንግግራቸውን አሳረጉ፡፡ ጭብጨባው ቀለጠ፡፡ ተማሪው መለስም በዚህ ንግግራቸው የተማሪዎችን ቀልብ ማርከው የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ኮንግረስ የአመራር አባላት በመሆን ከተመረጡት ውስጥ አንዱ ሊሆኑ በቁ፡፡

 

 

Read 3121 times Last modified on Saturday, 01 September 2012 12:14