Thursday, 15 July 2021 00:00

የአመቱ ቀንደኛ የፕሬስ ቀበኛ መሪዎች ይፋ ተደረጉ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

    ኢሳያስ አፈወርቂ በአንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል


              ሪፖርተርስ ዊዛውት ቦርደርስ የተባለው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ተቋም፣ የፕሬስ ነጻነትን በማፈን አቻ አላገኘሁላቸውም ያላቸውን 37 የአለማች አገራት መሪዎችን ዝርዝር ባለፈው ሰኞ ይፋ ያደረገ ሲሆን የኤርትራው ኢሳያስ አፈወርቂ በአንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
የአዘርባጃኑ ፕሬዚዳንት ኢሃም አሊቭ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ፣ የሶርያው በሽር አልአሳድ፣ የቱርኬሚኒስታኑ ጉርባንጉሊ፣ የካሜሩኑ ፖል ቢያ፣ የብራዚሉ ጄር ቦልሶራኖ፣ የታይላንዱ ፕራዩት ቻኖቻ፣ የኩባው ሚጉኤል ዲያዝ ካኔል፣ የፊሊፒንሱ ሮድሪጎ ዱሬቴ፣ የቱርኩ ረሲብ ጣይብ ኤርዶጋን እንደ ቅደም ተከተላቸው፣ ከሶስተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውንም ተቋሙ አስታውቋል፡፡
በ2021 የፈረንጆች አመት የአለማችን የፕሬስ ቀበኛ መሪዎች ዝርዝር ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ አውሮፓዊና ሁለት ሴት የአገራት መሪዎች መካተታቸውን የጠቆመው የተቋሙ ሪፖርት፤ አንዳንዶቹ የአገራት መሪዎች ፕሬስን ሲያፍኑ ከ20 አመታት በላይ እንዳለፋቸውም አመልክቷል።
በዝርዝሩ ውስጥ ከተካተቱት ሌሎች የአለማችን አገራት መሪዎች መካከል የኡጋንዳው ዩሪ ሙሴቬኒ፣ የህንዱ ናሬንድራ ሞዲ፣ የፓኪስታኑ ኢንራን ካሃን፣ የሳዑዲ አረቢያው ቢን ሳልማን፣ የሩስያው ቭላድሚር ፑቲን፣ የቻይናው ዢ ጂፒንግ እንደሚገኙበት የጠቆመው መረጃው፣ የሃንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን በአለማችን የፕሬስ ቀበኞች ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ የመጀመሪያው አውሮፓዊ መሪ መሆናቸውንም ያሳያል፡፡
ተቀማጭነቱ በፈረንሳይ የሆነው ተቋሙ ባለፈው ሰኞ ሪፖርቱን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሯ ኢምራን ካሃን በዝርዝሩ ውስጥ የተካተቱባት ፓኪስታን ሪፖርቱን በይፋ ውድቅ ማድረጓንና ያለስራቸው ተወቀሱ ስትል ተቃውሞዋን ማሰማቷን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

Read 4481 times