Wednesday, 07 July 2021 19:17

የምን አስገዳጅ ውል ነው?!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

ሁለት መረጃዎች በማቅረብ ልጀምር፡፡ ሱልጣን ጀማል በሽር በማህበራዊ ሚዲያ “የዓባይ ንጉሶች” የተሰኘ ፕሮግራም አለው። በዚህ ፕሮግራም በመላው ዓለም በአረብኛ ቋንቋ በሚሰራጩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ስለ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የሚቀርቡ መረጃዎችና ውይይቶችን ወደ አማርኛ እየተረጎመ ለኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ያደርሳል፡፡ ሰሞኑን አቶ ግርማይ ኃይሌ ከተባሉ  ኤርትራዊ ጋር አንድ ልዩ ፕሮግራም አዘጋጅቶ ነበር፡፡ አቶ ግርማይ ኤርትራ ነፃነቷን ከተቀዳጀች በኋላ፣ ከዓለም ተገልላ በቆየችባቸው ዓመታት፣ ፊቷን ወደ ራሷ መልሳ፣ ከመቶ ሺህ  እስከ ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ  የሚይዙ 800 ግድቦችን መሥራቷን፣ በምግብም ራሷን እየቻለች መሆኗን ገልፀዋል፡፡ ከሁሉም ያስደሰተኝ “ክፉን አያምጣ እንጂ ድርቅ ቢከሰት ዝናብ ባይኖር ለመጠጥም ሆነ ለእርሻ ልናውለው የምንችለው፣ ለአምስት ዓመት የሚያገለግል የውሃ ክምችት አለን” የሚለው አነጋገራቸው ነው፡፡ እኛስ መቼ ይሆን ፊታችንን ወደ ራሳችን የምንመልሰው? ይህን አንድ ይበሉ፡፡
ሁለተኛው፤ ፕሮፌሰር አዳሙ ዋለልኝ Horn of Africa Insight በተባለ ድረ ገፅ ላይ ያወጡት ፅሁፍ ነው፡፡ "ከአዲስ አበባም ሆነ ከሱዳኑ የድንበር ከተማ ከጋላባት እጅግ ርቃ በምትገኘው፣ በበቅሎ ጀርባ ካልሆነ በስተቀር ከማይደረስባት በጎጃም ከምትገኘው ትንሿ መንደር፤ ዳንግላ ውስጥ  እ.ኤ.አ በ1925 ላይ እንግሊዝ ለምን ቆንስላ ከፈተች?" ሲሉ ፕሮፌሰር አዳሙ ይጠይቃሉ። “ግልገል አባይ ለዳንግላ በቅርብ ርቀት ላይ በመገኘቱ ነው” ሲሉም ራሳቸው ምላሽ ይሰጣሉ። ቆንስላውን የከፈተው እንግሊዛዊ ሜጀር አር.ኢ. ቸስማን፣ የእንግሊዝ ንግስት አማካሪ እንደነበር አውስተው፤ በአካባቢው ያለውን  የውኃ ሃብት እየተዘዋወረ ለስድስት ዓመታት ማጥናቱን ይገልፃሉ፡፡
በአባይ ውኃ (ናይል) ላይ እ.ኤ.አ በ1929 የተደረገው ስምምነት ከዚህ ጥናት በኋላ የመጣ መሆኑን የጠቆሙት ፕሮፌሰሩ፤ ውሉ ኢትዮጵያን ጨምሮ ኬኒያን፣ ታንዛኒያን፣ ሩዋንዳን፣ ብሩንዲን፣ ኡጋንዳንና ዲሞክራቲክ ኮንጎን በውኃ ሃብታቸው ላይ ምንም አይነት ተግባር እንዳይፈፅሙ መብት እንደነፈጋቸው አመልክተዋል፡፡
አያይዘውም፤ የቬና ስምምነት አንቀፅ 34 ሀ፤ “በአንድ ውል ውስጥ ያልፈረመ ወገን ውሉ መብት ሊሰጠው ወይም ግዴታ ሊጥልበት አይችልም” ቢባልም፣ ግብፅና ሱዳን ግን የ1929 ውሎቻቸውን በሌላው ላይ ግዴታ እንደሚጥል አድርገው እንደሚያዩ፣ ውድቅ ለማድረግም ፍላጎቱ እንደሌላቸው አስረድተዋል፡፡
እስራኤልና ግብጽ በመካከላቸው የነበረውን ጠበኝነት ለማስቀረት እ.ኤ.አ በ1978 ወደ ተፈራረሙት የካምፕ ዴቪድ ስምምነት ፊታቸውን አዙረዋል ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ በዚህ ወቅት ግብፅ ለእስራኤል የአባይን (ናይል) ውኃ ለመሸጥ መስማማቷን ያስረዳሉ፡፡ ይህ ውኃውን በስዊዝ ካናል አሳልፎ ለእስራኤል የማድረስ ሃሳብ እ.ኤ.አ በ1903 ግብጽን በጎበኘውና የፅዮናውያን እንቅስቃሴ መስራች በሆነው በቴድሮስ  ሄርዜል ቀርቦ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ የአሁኑ የአሜሪካና እስራኤል በህዳሴው ግድብና አሞላል ላይ ኢትዮጵያ አስገዳጅ ውል እንድትፈርም፣ ከዚያም አልፎ ግብፅ በግድቡ ላይ የፈላጭ ቆራጭነት (ቪቶ ፓወር) ሥልጣን እንድታገኝ የሚያደርጉት ጫና ያለምክንያት እንዳልሆነም አስረድተዋል፡፡
የእኔም ጉዳይ ግብጽና ሱዳን ደጋግመው የሚያነሱት ይህንኑ አስገዳጅ ውልን የሚመለከት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ምንም አይነት ውል ሳትገባ የመጀመሪያውን ዙር የህዳሴውን ግድብ ውኃ የመሙላት ተግባር ማከናወኗን፣ ግብፅ ኢትዮጵያን ከተፋሰሱ ሀገራት ለመነጠል የዲፕሎማቲክ ዘመቻ እንድትከፍት  ማነሳሳቱን አንዳንድ ፀሐፍት ይገልጻሉ፡፡ ግብፅ ከተለያዩ የአፍሪካ  አገራት ጋር ወታደራዊ ስምምነት ተፈራርማለች። ዓላማው ደግሞ ኢትዮጵያን ከጎረቤትና ከተፋሰሱ አገራት ለማግለል እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡
ግብፅ ከሱዳን ጋር የጀመረችው ግንኙነት ደግሞ ሱዳንን በቀጥታ የግብፅ ቃል አቀባይና ተወካይ አስመስሏታል፡፡ ሁለቱ አገሮች ከአራት ጊዜ በላይ ወታደራዊ ልምምድ ያደረጉ ሲሆን የመጨረሻው ልምምድ “የአባይ ጠባቂዎች” የሚል መጠሪያ የተሰጠው መሆኑ ይታወቃል። ልምምዱ  የሁለቱን አገሮች የምድር የአየርና የባህር ኃይል ያካተተ ነበር፡፡ መንግስታቱ የልምምዱን  አላማና ግብ ባይናገሩም፣ አንዳንድ ባለስልጣኖቻቸው ግን ለኢትዮጵያ “ትምህርት ለመስጠት” ነው ሲሉ መግለፃቸው ተዘግቧል፡፡
አሁን ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የህዳሴ ግድብ ውኃ ሙሌት የምታካሂድበት ቀን ተቃርቧል፡፡ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት “የግድቡ ሙሌት የአካባቢው ስጋት ነው” በሚል ለውይይት እንዲያቀርበው ሱዳን ጠይቃለች፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ ሁለቱ አገራት  (ግብፅና ሱዳን) በውኃ ሙሌቱ ላይ ከስምምነት እንዳይደረስ እንቅፋት መሆናቸውን፣ ለፀጥታው ምክር ቤት የማሳሰቢያ ደብዳቤ ልካለች፡፡
የግብፆችና የሱዳን ከድርድር ማፈግፈግ፣ ኢትዮጵያ በሌላው ላይ የከፋ ጉዳት እስካላደረሰች ድረስ በውኃ ሃብቷ የመጠቀም መብት እንዳላት ለማወቅና ለመቀበል አለመፍቀዳቸው ያመጣው እንጂ የኢትዮጵያ ለመስማማት ያለመፈለግ ውጤት እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡
ኢትዮጵያ እስከ አሁን አስገዳጅ ውል ላለመፈረም የፀና አቋም እንዳላት እያሳየች ሲሆን ግብፅና ሱዳን  በበኩላቸው፤ ወደ ተስፋ መቁረጥ እየገቡ ይመስላሉ፡፡ የሁለቱ ደጀን አገሮችም በኢትዮጵያ የአቋም ፅናት የተነሳ ነገሩን ተመልሰው ለማየት መገደዳቸውን ጠቋሚ ምልክቶች አሉ፡፡ “በአሁኑ ሙሌት ተስማሙና በዘላቂው ጉዳይ ጊዜ ወስዳችሁ ተደራደሩ” እያሉ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ግን “የምን አስገዳጅ ውል?!” ማለቷን በጽናት መቀጠል አለባት፡፡

Read 6941 times