Wednesday, 07 July 2021 19:13

ጦርነትን በጊዜ ይገቱታል - ዋናው አላማ ወደ ሰላምና ወደ ብልፅግና ነውና፡፡

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

 •  ጦርነት፣ አማራጭ እየጠፋ እንጂ፣ በተፈጥሮው፣ ሁሌም አጥፊ ነው። ኪሳራ የሌለው ጦርነት የለም። ሕይወትን ያረግፋል፤ አካልን ያጎድላል። ኑሮን   ይነቅላል፤ ንብረትን ያወድማል።
   • ጦርነት በጊዜ ካልቋጩት፣ ጭራና ቀንድ ያበቅላል። ጭፍን ጥላቻን ያራባል። ለሰው ሕይወት መስጠት የሚገባንን ክብር ያጎድፋል። ስነምግባርን ይሸረሽራል።
   • ጦርነት፣ በጊዜ ካልገቱት፣ በተፈጥሮው፣ ሁሌም ጥፋትን ይፈለፍላል። ከታሰበለት ጎዳና ከተያዘለት ቀጠሮ ውጭ፣ በሰበብ አስባቡ፣ መስመሩን ይስታል፤       
  •  ልጓሙን ሰብሮ፣ በራሱ ጊዜ ይሸመጥጣል። በዘፈቀደ እየተመዘዘ እየተጎተተ የመዛመት ባህርይ አለው - ጦርነት።
       ለጦርነት እልባት የመስጠት ጥበብና ፍላጎት፣ ትልቅ ሃላፊነት ነው። ጦርነት፣ “ክፍለ ጊዜው አለቀ፣ ቀነ ገደቡ አለፈ፣ 90 ደቂቃው ተጠናቀቀ” ተብሎ             አይደመደምም። ልባም ውሳኔና ተግባር ያስፈልገዋል - የጀግንነትም የእውቀትም፤ የብርታትም የአስተዋይነትም ውሳኔና ተግባር።
            
              “የጦርነት እቅድ፣ ከመጀመሪዋ ጥይት ያለፈ እድሜ የለውም” ይባላል። አዎ፣ የተጋነነ አባባል ነው። ነገር ግን፣ ቁምነገረኛ አባባል ነው። ሺ ጊዜ ተደጋግሞ የሚነገረው ያለምክንያት አይደለም። ለበርካታ ሺህ ዓመታት እየተደጋገመ የተከሰተና የታየ የጦርነት እውነታን የሚገልፅ፣ እየመላለሰ የሚያስታውስ አባባል ነው።
“የሰው ሃሳብ ከንቱ! አላማ፣ መርህ፣ ተግባርና እቅድ ሁሉ ከንቱ! ሁሉም እንደፍጥርጥሩ ይሁን” ለማለት አይደለም።
በተቃራኒው፣ የአላማ ጥራትንና የመርህ ቀናነትን፣ የተግባር እቅድንና ብርታትን፣... የሃሳብና የተግባር ብቃትን እንድናከብር፣ ቸል እንዳንል የሚያስተምር አባባል ነው። የቱን ያህል የህልውናና የስኬት ሃይል እንደሆኑ የሚያስገነዝብ አባባል ነው። የእቅድን ወሳኝነት አበክሮ ለማሳየት ይረዳል።
በተለይ፣ በጦርነት ጉዳይ ላይ፣ የተግባር ሁሉ ቀዳሚና በኩር ነው እቅድ። ይህም ብቻ አይደለም። ጦርነት ማለት፣ አንዴ አቅደው የሚገላገሉት ቀላል ነገር አለመሆኑን ያስረዳል - ቁምነገረኛው አባባል። ጦርነት፣ በተፈጥሮው፣…. በእንቅፋት፣ በእክል፣ በፈተና የተከበበ ነውና።
ደግሞስ፣ የጦርነት ያህል፣ ጥንቅቅ ያለ እቅድ የሚያስፈልገው ጉዳይ ምን አለ? ጦርነት፣ በጥሬው፣ የሞት ሽረት ጉዳይ አይደል?
እናም፣ ከጦር አወቃቀር ጅምሮ እስከ ዕለታዊ ስምሪት ድረስ፣ ሁሉም ነገር በህግና በሥርዓት፣ በእቅድና በጊዜ ሰሌዳ ሲከናወን እናያለን - በጦር ኃይል ውስጥ። ከጥቅል የመከላከያ ፖሊሲ ጀምሮ እስከ ስልጠናና የትጥቅ አይነት፣ ከጥቅል ስትራቴጂና ከጦርነት አዋጅ እስከ ዝርዝር የውጊያ እቅድ ድረስ፣ በቅጡ ይሰናዳል።
መነሻና መድረሻ እየተመደበለት፣ እርከንና መስመር እየተበጀለት፣ ቅድም ተከተል እየወጣለት በጊዜ ሰሌዳ ይሰደራል። በሀሳብ እየተሰላ፣ በፅሁፍ ይሰፍራል፣ በንድፍ ይቀረፃል። ለምን? የጦርነት ጉዳይ ነዋ። ጦርነት ደግሞ፣ በግልባጩ የሰላም ጉዳይ ነዋ። የህልውናና የእልቂት፣ የሞትና የህይወት ጉዳይ ነው።
ሞቃዲሾንና ሶሪያን ማየት ነው። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የፈራረሱና የተቃጠሉ የጀርመን ከተሞች፣ “ስታሊንግራድ” ተብላ የነበረችው ሳንትፒተርስበርን፣ የሀዋይ ፐርል ሀርበር፣ የጃፓን ሂሮሺማና ናጋሳኪ፣… እልቂቱና ውድመቱ ለሀሳብም ይዘገንናል።
የምድር ስር የቆሻሻ ትቦዎች ካልሆኑ በቀር፣ ምድር ላይ ምን ቀራቸው? እንኳን ሰው፣ በድንጋይ ላይ የተቀመጠ ድንጋይ፣ በቁም የተረፈ ግንብ የማይታይበት ጥላሸት፣ ፍርስራሽና አመድ ሆነዋል - ብዙ ከተሞች። ጨርሰው የጠፉና ከታሪክ መዝገብ የተሰረዙ ከተሞች ሞልተዋል - በጦርነት። አንዳንዶቹም ለትንሽ ነው የተረፉት። ሺዎች አልቀው፣ ከተሞቹም ሞተው ነው የተነሱት - እንደ ሮም የመሳሰሉት። ጥያቄ የለውም። የጦርነትን አጥፊነት፤ ዛሬም እያየን ነው፣ ጥንትም የታየ ነው። የዛሬ 800 ዓመት ገደማ፣ የቻይናዋ ቤጂንግ ከተማ በጦርነት ስትቃጠል፤ እሳቱ ለወር አልጠፋም።
አማራጭ ካልታጣ በቀር፣ የባሰ አደጋ ለመከላከል ሌላ ዘዴ ካልጠፋ በቀር፣ ጦርነት አስቀያሚም ዘግናኝም ነው። ዓላማ፣ ስትራቴጂ፣ እቅድ፣… በተሰኙ እልፍ ከባባድ ስራዎች የሚጨናነቀው ለምን ሆነና?
እንዲያም ሆኖ፣ ከውጥን ተነስቶ፣ በጥንቃቄ ተበጥሮ፣ በነጠላ በነጠላ ተፈትሎ የተሸመነው እቅድ፣ የጦርነት መባቻ ላይ፣ ፈተና ላይ ይወድቃል። አንዳንዴም፣ ገና በዋዜማው፣ በእክሎች የተወሳሰበ ሆኖ ያርፈዋል።
ጦርነትን የማያውቁ የዋህ ሰዎች፣ ወይም እልቂትን የሚናፍቁ ክፉ ሰዎች፣ ገና ከውጥኑ ነገር ያሳክራሉ፤ ያደፈርሳሉ። በተደናበረ ቅስቀሳ ወይም በዘፈቀደ ሆይሆይታ፣ ነገሮች ተወታትበው በየአቅጣጫ ያፈተልካሉ። በጦርነት መባቻ ደግሞ፣ ችግርን የሚወሳሰቡ ሳንካዎችና የተሳከሩ ውዥንብሮች ይበረክታሉ።
ተበጥሮ ፍንትው ብሎ በወረቀት ላይ የሚታየው የጦርነት እቅድ፣ የጦር ሜዳ ብዥታ ይውጠዋል።
የጦርነት ውሎና አዳር፣ ፍንትው ወለል ብሎ አይታይም። የጦርነቱ ውልብታዎችን ማየት ይቻል ይሆናል። ድቅድቅ ጨላማ ላይሆን ይችላል። ነገር ግን፣ ከብዥታ የሚያመልጥ ጦርነት የለም።
ከእልፍ አፈሙዞች የሚወጣ የጥይት እሩምታ፣ መድፎች የሚተፉት እሳት፣ የፍንዳታዎች ቦግታ፣ አሁንም አሁንም አካባቢውን ወገግ ያደርጉታል። ነገር ግን፣ የጦርነቱን መምጫና መድረሻ አጥርቶ ለማየት፣ ዙሪያ ገባውን በግልፅ ለመቃኘት አይጠቅሙም። በመብረቅ እንደሚናወጥ የውድቅት ሌሊት ውሽንፍር፤ ጦርነትም እንደዚያው ነው - በምልዓት የሚቃኙት አጥርተው የሚያዩት ነገር አይደለም።
“የጦርነት ጭጋግ” የሚለውን  አባባል አስተውሉ - “fog of war”።
የጥንቱ ዘመን፣ “የጦር አውድማ ትርምስ” ሊሆን ይችላል - የጦርነት ጭጋግ ማለት። የዘመናችን የሰማይና የምድር፣ የክፍለ ጦርና የብርጌድ፣ የከተማና የመንድር፣ የተራራና የሸንተረር፣ በደርዘን የጦር አውድማዎች የሚካሄድ ትንፋሽ የሚያሳጥር ዘመቻም፣ ከጭጋግ አያመልጥም።
ከዕለት ዕለት፣ ከሳምንት እስከ ወራት እየረገበ እያገረሸ፣ ጭራና ቀንዱ የሚወሳሰብ የሽምቅ ጦርነትም ሊሆን ይችላል - የጦርነት ጭጋግ ማለት። የጦርነት ሜዳ፣ ፍንትው ብሎ አይታይም። ከዚህም ይከፋል።
ጦርነት፣ አሲዳማ ጭጋግ ነው። ጊዜው እየረዘመ ሲሄድ ደግሞ፣ መውጫ መግቢያው የተምታታ ረግረግ ይሆናል። “quagmire” ይሉት የለ? ግን የጭቃ ሳይሆን የረመጥ ነው - የጦርነት ረግረግ። “አረንቋ” ሲሉ ገልፀውታል - አንድ የመንግስት ባለስልጣን። እውነት ነው። ማጥ፣ ረግረግ፣ አረንቋ፣. እያነደዱ የመንደድ ረመጥ ይሆናል - በጊዜ ያልተገታ ጦርነት።
በአጠቃላይ ምን ለማለት ነው?
አንደኛ ነገር፣ ሌላ አማራጭ መንገድ ያልተገኘለት የህልውና ጉዳይ ካልሆነ በቀር፤ ወይም እጅግ የባሱ አደጋዎችን ለመከላከል ሌላ ዘዴ ካልጠፋ በቀር፣ የጦርነት እሳት ክፉ ነው። ሁሌም፣ ዘግናኝ ጥፋቶችን ያስከትላል።
ሁለተኛ ነገር፣ ህልውናን ለመጠበቅና ክፉ አደጋዎችን ለመከላከል ሌላ ዘዴ ሲጠፋ፣ ወደ ጦርነት መግባት የግድ ሲሆን፣ ገና ከዋዜማው ነው ፈተናው። ከባድ ጥንቃቄንና አርቆ አስተዋይነትን አጥብቆ መያዝ ያስፈልጋል።
ጊዜያዊ ሆይሆይታንና ድንገተኛ የመደናበር ግርግሮችን፣ አንድ ሁለቴ ብቻ ሳይሆን፣ እለት በእለት መገሰፅና ማረቅ፣ ቀላል ስራ አይደለም። ከባድ ሃላፊነትና አድካሚ ስራ ነው። ሳይታክቱ ያልገሰፁትና ያልገሩት የስሜት ግርግር፣ የኋላ ኋላ፣ ለአሳዛኝ መዘዞችና ለተጨማሪ አስቀያሚ የችግር ሸከሞች ይዳርጋል።
ሶስተኛ ነገር፣ በትክክለኛና በግልጽ አላማ፣ ጥንቅቅ ጥርት ባለ ውጤታማ እቅድ፣ አቅጣጫውና እርምጃው፣ ፍጥነትና አድራሻው በስርዓት እየተመራም እንኳ፣ ጦርነት አስቸጋሪ ነው - በተፈጥሮው። ከስር ከላይ፣ ከግራና ከቀኝ እየተከታተሉ ስርዓቱን ካልተቆጣጠሩትማ፣ በራሱ ጊዜ የራሱ እጅና እግር ያወጣል፤ ልጓም በጥሶ ባላሰቡት አቅጣጫ፣ ወደ አልተላከበት ቦታ ይሄዳል።
ግን ደግሞ፣ ጦርነት፣ ለእለት ተእት ክትትል አይመችም። ጦርነት፣ በጊዜ እልባት ካልሰጡትና ካልገቱት፣ በራሱ ጊዜ፣ የራሱ ጭራና ቀንድ ያበቅላል። ወዲህና ወዲህ እየተምዘገዘገ አካባቢውን የሚያጭድ ጭራ፤ ወዲህና ወዲያ እየጋለበ እየተመመ የሚዋጋ ቀንድ፣ ለያዥ ለገራዥ ያስቸግራል።
ጦርነት አሲዳማ ጭጋግ ነው። ካቀዱለት አቅጣጫ አልፎ መሄድ አለመሄዱ፣ ከጠረጉለት ጎዳና መውጣት አለመውጣቱ፣ መንገድ መሳት አለመሳቱ፣ እለት በእለት ለመከታተል ያስቸግራል። በአሲዳማ ጭጋግ ውስጥ፣ ከስር ከስር ለማስተካከል ቀላል አይደለም።
ጦርነት፣ የረመጥ ረግረግ ከሆነ በኋላ ደግሞ፣ እረፍት አይሰጥም።
ለዚህም ነው፤ ለጦርነት እልባት የመስጠት ጥበብና ፍላጎት እጅግ አስፈላጊ የሚሆነው። የፍርሀት ወይም የሽንፈት ጉዳይ አይደለም።
የልባም ተግባር ነው። የጀግንነትም የእውቀትም፤ የብርታትም የአስተዋይነትም ተግባር ነው።
ወደፊት ከባድ ሀላፊነቶችን የመወጣት ዝግጁነትን፣ መነሻና ዘላቂ፣ የሰላምና የብልፅግና አላማዎችን ሳይዘነጉ በትጋት የመቀጠል ፅናትን ይጠይቃል - ጦርነትን የመቋጨት ጥረት።
የሀገር ሰላምን መጠበቅ፣ ህግና ስርዓትን ማፅናት፣ የዜጎች ነፃነትና መብትን ማስከበር፣ የህግ የበላይነትን ማደርጀት፣ ሰዎች ኑሮአቸውን ለማሻሻል የሚተጉበት የኢኮኖሚ ነፃነትን ማስፋፋት፣…. በጥቅሉ ለሀገር ስልጣኔ የሚስማማ ፖለቲካዊ ስርዓትን ማስፈን ነው - ትክክለኛው የፖለቲካ መነሻ ዓላማ፣ ትክክለኛ የሚያዛልቅ ፖለቲካዊ ዓላማ።
ለዚህ ሲባል፣ ማለትም የሀገርን ህልውናና ተስፋ ከጥፋት ለማዳን ሲባል፣ ሌላ አማራጭ የጠፋ ጊዜ፣ ወደ ጦርነት ይገባል - በእውቀትና በጀግንነት።
ለዚሁ ሲባል፣ ማለትም ትክክለኛዎቹን መነሻና ዘላቂ አላማዎችን፣ የሰላምና የብልፅግና አላማዎችን ለማሳካት ሲባል፤ ጦርነትን በጊዜ ለመግታትና ወደ እልባት ለማድረስ መትጋት ያስፈልጋል። በእውቀትና በጀግንነት።
አዎ፤ ከባድ ስራ ነው፤ ወደፊት ከባድ ሀላፊነቶችን የመወጣት ዝግጁትን ይጠይቃል - መጨረሻው የተቃና ያማረ እንዲሆን።
ኢትዮጵያ የመላ አፍሪካ የተስፋ ፋና፣ ከዚያም አልፋ፣ ለአፍሪካ ደማቅ ብርሃን የምትፈነጥቅ ምስራቃዊ የፀሀይ መውጫ መሆን የምትችል ሀገር ናት።
ለዚህም፣ ሰላምና እርጋታ ያስፈልጋታል።
ህግና ስርዓት የነገሰባት፣ የእያንዳንዱ ሰው ነፃነትና መብት የተከበረባት፣ ሰው እንደየ እውቀቱና እንደየ ብቃቱ በአድናቆትና በአርአያነት የሚታይባት፣ በብልጽግና ግስጋሴ የምትታወቅ ሀገር መሆን ይኖርባታል።
ከባድ ነው። ግን ይቻላል።

Read 1170 times