የፊልም ሽልማቱን ለማዘጋጀት የሰባት ወራት ጥናት ማካሄዳቸውን የገለፁት የኢትዮ ፊልምስ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ብርሃነ መዋ፤ የሽልማቱ ወጪ በሙሉ በድርጅታቸው እንደሚሸፈንና ባለፊልሞች ውድድር እንዲያሸንፉ ብቻ ሳይሆን የተሻለ ሥራ ይዘው ለሕብረተሰቡ እንዲቀርቡ ነው ጥረታችን ብሏል፡፡ የኢቢ ኤስ ቴሌቪዢን ጀነራል ማናጀር አቶ አማን ፍስሃ ጽዮን፤ ጣቢያቸው በፊልም ላይ የተሻለ ሽፋን እንደሚሰጥና ከኢትዮ ፊልምስ ጋር ተባብረው በመስራት ላይ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ ሀገር አቀፍ ፊልሞችን ብቻ የሚያስተናግደው የፊልም ሽልማት ምዝገባ በድረገጽ የተጀመረ ሲሆን ሽልማቱ ለአምስት ተከታታይ ዓመታት እንደሚካሄድ ለማወቅ ተችሏል፡፡ አዘጋጆቹ የአሸናፊ ፊልም ምርጫ ሂደትን ሲገልፁ፤ አንድ ሰው ከአንድ በመቶ በታች የሆነ ድምጽ ስለሚኖረው ሚዛናዊነቱ እንደሚጐላ ያላቸውን እምነት ተናግረዋል፡፡