Wednesday, 30 June 2021 00:00

የአሸናፊው መንግስት ቀዳሚ ተግባራት?!

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

የህግ ጠበቃውና ፖለቲከኛው አቶ ወንድሙ ኢብሣ፣ በታሪካዊው የ97 ምርጫ ላይ ተወዳድረው ፓርላማ ገብተው ነበር፡፡ በፕ/ር መረራ ጉዲና የሚመራው የኦፌኮ አባልም እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡ ፓርቲው ላለፉት 20 ዓመታት "ለሁሉም እኩል የምትሆን ኢትዮጵያን የመመሥረት" ዓላማን ይዞ ሲንቀሳቀስ እንደቆየና በለውጡ ማግስት ግን በጽንፈኛ ግለሰቦች ፍላጎት መጠለፉን ፖለቲከኛው ያስረዳሉ፡፡ ይህን ተከትሎም ኦፌኮ ከዘንድሮ አገር አቀፍ ምርጫ በተጽዕኖ መውጣቱን ይገልጻሉ፡፡ በዚህም እስካሁን ይዞት የመጣውን  መልካም ታሪኩን ማበላሸቱን ይናገራሉ፡፡ የህግ ጠበቃውና ፖለቲከኛው አቶ ወንድሙ ኢብሣ፤ ባለፈው ሰኞ በተካሄደው 6ኛ አገራዊ ምርጫ፣ በኦፌኮ አዲስ የፖለቲካ አቅጣጫ፣ በቀጣዩ ፓርላማና በአሸናፊው መንግስት ዙሪያ  ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል፡፡ እነሆ፡-


ኦፌኮ ከምርጫው በመውጣቱ ታሪኩን አበላሽቷል
ፓርላማው የተለያዩ ድምጾች የሚሰሙበት ይሆናል
የኦፌኮ ዓላማና ግብ በጽንፈኛ ግለሰቦች ተጠልፏል  

   ባለፈው ሰኞ የተደረገውን 6ኛ አገር አቀፍ ምርጫ እንዴት አገኙት?
በኢህአዴግ ዘመነ መንግስት ሲታወስ የሚኖረው በ97 ዓ.ም የተካሄደው ምርጫ ነው፡፡ ከዚያ በኋላም ሆነ በፊት የተደረጉ ምርጫዎች ሁሉ  የቀልድ ነበሩ፡፡ እኔ በ97ቱ ምርጫ አሸንፌ ፓርላማ ከገባሁ በኋላ በ2002 ከፓርላማ ስወጣ፣ አንድ ጋዜጠኛ፤ “ቀጣዩን ምርጫ እንዴት ታየዋለህ?” ብሎ ጠይቆኝ ነበር፡፡ እኔም በሰጠሁት ምላሽ፤ "ከዚህ በኋላ የሚኖረው ፓርላማ የኢህአዴግ ብዙ መመጻደቆች የሚደሰኮርበት ነው የሚሆነው" ብዬው ነበር፡፡ በእርግጥም የሆነውም እንደዚያው ነው፡፡
የዘንድሮው ምርጫ ያስታወሰኝ የ97ቱን ምርጫ ነው፡፡ በብዙ መልኩ ይመሳሰላል። በእርግጥ የያኔው ምርጫ ሲካሄድ አገሪቷ ከውስጥም ሆነ ከውጪ ምንም ዓይነት ጫና አልነበረባትም፡፡ ብዙው ሰው ሙሉ ትኩረቱን በምርጫው ላይ አድርጎ ነበር። በአንጻሩ የዘንድሮው ምርጫ ሃገሪቱ በበርካታ ጫናዎች ውስጥ ሆና የተደረገ ነው። በሃገር ውስጥ ጁንታዎች፣ በውጪ ደግሞ ሱዳንና ግብፅ እያደረጉት ያለው ጫና በግልፅ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ሃይሎች ኢትዮጵያን (ስትራቴጂካሊ) ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡
በሌላ በኩል፤ ይህን ምርጫ ቅቡልነት ለማሳጣት ያልተፈነቀለ ድንጋይ የለም፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ፓርላማ 547 ወንበር ነው ያለው፡፡ የትግራይ ክልል ከዚህ ውስጥ ድርሻው 38 ወንበር ነው፡፡ ነገር ግን የውጭ ሃይሎች ምርጫው በክልሉ አለመካሄዱን በማንሳት፣ ጫና ለማሳረፍና ምርጫውን ቅቡልነት ለማሳጣት ያደረጉት ሙከራ ያስገርማል፡፡ በአንጻሩ ጽንፈኛ ኃይሎች ዜጎችን፤ "ወጥታችሁ ብትመርጡ እንገድላችኋለን” እያሉ በሚያስፈራሩበት ድባብ ውስጥ የኢትዮጵያ ህዝብ ከዳር እስከ ዳር ወጥቶ ድምጹን የሰጠው፡፡ ምርጫው ህዝቡ ሉአላዊነትን የመረጠበትና ኢትዮጵያዊነትን ያነገሰበት ሂደት ነው፡፡
የሚገርምህ ነገር እኔ ቡራዩ ነው የምኖረው፤ የምርጫው ዕለት ማለዳ በ12 ሰዓት ነበር ከባለቤቴና ልጄ ጋር ወደ ምርጫ ጣቢያው የሄድኩት፡፡ ስንደርስ ህዝቡ ወጥቶ ተሰልፏል፡፡ እኔ ሰልፍ አስይዤ ተመለስኩ። ባለቤቴ ግን ቁርስም ምሳም ሳትበላ ውላ 10 ሰዓት ነው፣ ወረፋ ደርሶን መርጠን የገባነው። ህዝቡ ወዶና ፈቅዶ ተሰልፎ ያለ ምሳ ውሎ፣ ሉአላዊነቱን የመረጠበት ምርጫ ነው ማለት እንችላለን፡፡ ከ97ቱ ምርጫ  በበለጠ ኢትዮጵያዊያን አንድነትን የመረጡበት፣ በአንጻሩ ደግሞ ጽንፈኞች ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተሟሟቱበት ነው፡፡ ስለዚህ ለኔ ምርጫው የኢትዮጵያውያን ድምጽ ጎልቶ የተሰማበት፣ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት  ጅማሮ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
ምርጫው በተለይ በኦሮሚያ ክልል ዋነኞቹ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ራሳቸውን ከሂደቱ ባገለሉበት ሁኔታ የተካሄደ ነው በሚል ይተቻል፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
መቼም ከዚህ ቀደም ወደ 140 ገደማ ተቀላቢ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ በወ/ሪት ብርቱካን የሚመራው ምርጫ ቦርድ እነዚህን ፓርቲዎች አበጥሯል። ወደ 80 የሚደርሱ የውሸት ፓርቲዎችን  ሰርዟል፡፡ መጨረሻ ላይ የቀሩትም 53 ፓርቲዎች ናቸው፡፡ ከ53 ፓርቲዎች ውስጥ ደግሞ 14 ያህሉ በኦሮሚያ ላይ የሚወዳደሩ ናቸው፡፡ በእርግጥ እነዚህ ፓርቲዎች ሚዲያ ስለሌላቸው የተወሰኑ ፓርቲዎች ድምጽ ብቻ ነው ጎልቶ የሚሰማው፡፡ ለምሳሌ የኦነግንና የኦፌኮን መውሰድ ይቻላል፡፡ የኦነግ ጉዳይ እንደሚታወቀው፣ በ1983 ከህወኃት ጋር የመንግስት ስልጣን አግኝቶ የነበረ ቢሆንም፣ ሳይጠቀምበት ከሃገር ፈርጥጦ ወጥቷል፡፡ በቅርቡ ደግሞ በ2010 የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ከአስመራ ተጋብዞ ሲመጣ፣ በተዝረከረከ ሁኔታ ግማሹ በቦሌ፣ ግማሹ በባሌ ከገባ በኋላ "ማን ትጥቅ ይፈታል? ማን ያስፈታል?" የሚል ውዝግብ ውስጥ ነው የተዘፈቀው፡፡ ኦነግ በሚያደርገው የጦር እንቅስቃሴ በ40 አመት ታሪኩ አንድ ቀበሌ ይዞ አያውቅም፡፡ በምርጫም ሆነ በሃይል የትም መድረስ የማይችል ቡድን ነው፡፡ የኦነግ ጥንስስ የሆነውን መጫ እና ቱልማ ማህበርን የመሰረቱት እነ ጀነራል ታደሰ ብሩና ዋቆ ጉቱ፤ የኦሮሞን ህዝብ አናስገድልም የሚል ነበር አላማቸው፡፡ ጀነራል ዋቆ ደጋግሞ የሚለው ነገር ነበር፡፡ ይኸውም “የኃይለስላሴን መንግስት በአነስተኛ ኪሳራ ከቻልን እንለውጠዋለን፤ ካልቻልን  የሚለውጥ ትውልድ እናፈራበታለን” ይል ነበር፡፡
"በጦርነት ብቻ የኦሮሞን ህዝብ አስጨርሰን አንለውጥም" የሚል እምነት ነበራቸው፤ እነ ጀነራል ዋቆ ጉቱና ጀነራል ታደሰ ብሩ፡፡ የአሁኖቹ ግን “50 ሚሊዮን ኦሮሞን አስገድለን ስልጣን እንይዛለን” ብለው የሚያስቡ ናቸው፡፡ በአንጻሩ፤ የኦሮሞ  ፌደራሊስት ኮንግረስ እኔም የነበርኩበት ፓርቲ ነው፡፡ “ለሁላችንም በእኩል የምትሆን ኢትዮጵያን እንመሰርታለን; የሚል አላማ ያነገበ ፓርቲ ነበር፡፡ ላለፉት 20 ዓመታት በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ብቻ ሲታገል የዘለቀ ፓርቲ ነው፡፡ አሁን ነገሩ ሲገለጥ ለካ በጭንብል የተሸፈነ ነበር፡፡ ለሁላችንም የምትሆን ኢትዮጵያ ሳይሆን ለጥቂቶች የግል ኑሮ የምትሆን ኢትዮጵያን የመፍጠር አላማ  የሚያራምድ መሆኑ ታይቷል፡፡
አሁን ፓርቲው ወደ ኦነግነት የመጠጋት አዝማሚያ እየተስተዋለበት ነው፡፡ ዲቃላ የሚል ፖለቲካ በማራመድ ነው ጭንብሉን የገፈፈው፡፡ ይህ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስን የማይወክል አደገኛ አካሄድ ነው፡፡ ለውጡ ከመጣና አክቲቪስቶች ከተቀላቀሉት ወዲህ ፓርቲው አላማውን ለውጦ ለኦሮሞ ሳይሆን ለኦፌኮ ብቻ የምትሆን ኦሮሚያን መፍጠር አላማው አድርጎ የተነሳ ይመስላል። ኦሮሚያን በህጋዊም ሆነ በህገ-ወጥ መንገድ ከኢትዮጵያ የመነጠል አዝማሚያ ያለው እንቅስቃሴ ውስጥ ገብቷል፡፡ በነገራችን ላይ እነዚህ ሃይሎች ከምርጫው እንዳይወጡ በኦሮሞ አባገዳዎች ተለምነዋል፡፡ ነገር ግን አሻፈረን አሉ፡፡ ይሄ ደግሞ ህወኃቶች ከመንግስት ጋር አንተባበርም ብለው በእብሪት እንደተወጠሩት ዓይነት አካሄድ ነው፡፡ ስለዚህ በምርጫው ያልተሳተፉት በሌላ አላማ እንጂ በመንግስት ጫና ተገፍተው አይደለም፡፡ ከዚህ ቀደም በወያኔ ስርዓት በቀለ ገርባን ጨምሮ በርካታ ከፍተኛ አመራሮች ታስረው ነበር፡፡ በአሁኑ የታሰሩት የድርጅቱ አመራሮች በቀለ ገርባና ደጀኔ ጣፋ ናቸው፡፡ ሌሎቹ አዲስ የተቀላቀሉ ናቸው፤ ስድስት ወር እንኳ አልሆናቸውም። በዚያ ላይ የአመራርነት ቦታ የላቸውም፡፡ ኦፌኮ ከምርጫው የወጣው በአንድ ግለሰብ ተጽዕኖ ነው፤ ያውም አባል ከሆነ ገና 6 ወር ባልሞላው ግለሰብ ምክንያት፡፡ ፓርቲው ከዘንድሮ ምርጫ በመውጣቱ እስካሁን የመጣበትን ታሪክ አበላሽቷል፡፡  
በሌላ በኩል፤ ባለፉት በርካታ አመታት ከኦፌኮ ጋር ሲታገሉ እኔን ጨምሮ በርካታ ዋጋ የከፈሉ ታጋዮችን ልፋት ከንቱ ያደረገ ውሳኔ ነው፡፡ ፓርቲው ሙሉ ለሙሉ ለአንድ ግለሰብ ፍላጎት በመገዛት፣ የአንድን ግለሰብ ከእስር መውጣት አለመውጣት ትልቅ ነገር አድርጎ ነው ከምርጫው የወጣው፡፡ ለምሳሌ ባልደራስ ሊቀ መንበሩ እስክንድር ነጋ ታስሮበታል፡፡ ነገር ግን በፍትህ አደባባይ እጩ ሆኖ እንዲቀርብ ተሟግቶ አሸንፏል፡፡ ኦፌኮም እንኳን ተራ ካድሬ ቀርቶ ራሳቸው ፕ/ር መረራም ቢታሰሩበት፣ በተመሳሳይ መንገድ በህግ እየተሟገተ በምርጫው መሳተፍ ነው የነበረበት፡፡ እነሱ ያልገባቸው የኦሮሞ ህዝብ ለአንድ ግለሰብ አይሰግድም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ለአንድ ግለሰብ አይሰግድም፡፡ ለዚህ የአፄ ኃይለስላሴን ታሪክ ማስታወስ ይቻላል። የኢትዮጵያ ህዝብ ከግለሰቦች ጋር የተለየ አምልኮ የለውም፡፡ በመድረኩ ላይ ከሌሉ የሉም ነው፤ አለቀ፡፡ በወቅቱ እኔ የፓርቲው የህግ ኮሚቴ ሰብሳቢም ስለነበርኩ፣ ይሄ "ዲቃላ" ፖለቲካም ሆነ አካሄዱ ትክክል እንዳልሆነ አብዝቼ ተከራክሬአለሁ፡፡ ሆኖም መግባባት አልተቻለም:: የተወሰንን አባላት ጉዳዩን ተውነው፡፡ በነገራችን ላይ ኦፌኮ ከምርጫው የወጣው በራሱ ውሳኔ ብቻ አይደለም፡፡ ከውጪ እነ ብርሃነ መስቀል፣ እነ ኢታና ሃብቴ የሚባሉ ፅንፈኛ አክቲቪስቶች በሰጡት አመራር ነው፡፡ የኦፌኮ አመራር በፅንፈኞች በመወጠሩና ለግለሰቦች ያደረ በመሆኑ ምርጫውን አልፈልግም ብሎ ወጥቷል፡፡ ነገር ግን የኦሮሞ ህዝብ ምርጫውን ይፈልገው ነበር፡፡ ለዚህም ነው በኦሮሚያ 15 ሚሊዮን ህዝብ ተመዝግቦ የመረጠው፡፡
ኦነግ ከምርጫው መውጣቱ የተለመደ ነው፤ አያስደንቅም፡፡ የኦፌኮ ግን ትልቅ ታሪካዊ ስህተት ነው፣ በታሪኩ ላይ ጥቁር ነጥብ ነው ያሳረፈው፡፡ ህዝብም ውሳኔውን ተቃውሟል፡፡ የኦፌኮ እርምጃ ትክክል እንዳልሆነ ያሳየው ወጥቶ በመምረጥ ነው፡፡ እንግዲህ “አንዱ ገበያ ቢቀር ሌላ ገበያ መኖሩ አይቀርም” የሚባል ነገር አለ፡፡ አንድ ፓርቲ ቀረና ምርጫ ይቀራል ማለት አይቻልም፡፡ ቅንጅት እንኳ በ97 አመራሮቹ ሲታሰሩ በጎን ሌላ መዋቅር አዘጋጅቶ ነበር፤ በውጭ አገር ሆኖ ትግሉን አስቀጥሎ የሚመራ፡፡ ኦፌኮ ግን ከአንድ ግለሰብ ጋር ተጣብቆ ትልቅነቱን አጥቷል፡፡ ይሄ በጣም ያሳዝናል፡፡
አሳዛኙ ነገር ደግሞ አሁን ሚሊዮን ኦሮሞዎች፣ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን የመረጡትን ምርጫ አልቀበልም ብሎ  የሽግግር መንግስት ካልተመሰረተ የሚል ነገር ማምጣቱ፣ ከድጡ ወደ ማጡ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ኦፌኮ ራሱን ቆም ብሎ መመርመር አለበት፡፡ በዚህ ከቀጠለ ግን በጣም መጥፎ የታሪክ ሞት የሚሞት ፓርቲ  ነው የሚሆነው፡፡
ቀጣዩ ፓርላማ ምን መልክ ይኖረዋል ብለው ይጠብቃሉ?
ቀጣዩ ፓርላማ በእርግጠኝነት የኢትዮጵያን ህዝብ ቀልብ የሚስብ ይሆናል፡፡ የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል ይባላል፡፡ እስካሁን በውድድሩ የተሳተፉ ፓርቲዎች ምን ያህል የበሰሉና ታጋሽ እንደሆኑ ለህዝባቸው ያረጋግጣሉ፡፡  ፓርላማው የተለያዩ ድምጾች የሚሰሙበት ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡ በተለይ የሃገርን አንድነትና የኢትዮጵያን ቀጣይነት ሊያረጋግጡ የሚችሉ የህዝብ ተወካዮች በመድረኩ ይደምቃሉ ብዬ አምናለሁ። የህዝብ ብሶትና ችግር የሚደመጥበት፣ የህግ የበላይነት የሚረጋገጥበት ጠንካራ ክርክር የሚካሄድበት ፓርላማ እንደሚሆን አልጠራጠርም፡፡  
የአሸናፊው መንግስት ቀዳሚ ተግባራት ምን መሆን አለባቸው ይላሉ?
አንደኛ፤ ህገመንግስቱን የሚያሻሽል እንዲሆን እፈልጋለሁ፡፡ ሁለተኛ፤ አሁን በምርጫው የተሳተፉትንም ሆነ አኩርፈው ራሳቸውን ከምርጫው ያገለሉ ፓርቲዎችን ሰብስቦ ብሔራዊ መግባባትና እርቅ መፍጠር ጠቃሚ ነው፡፡ በሃገር ውስጥ ያሉና ያኮረፉ ሃይሎችን በሽማግሌዎች በማስጠየቅ ወደ እርቅ መድረክ እንዲመጡ ማግባባት ያስፈልጋል፡፡ ይህን የሚያመቻች ልዩ ኮሚሽን ቢቋቋም መልካም ነው፡፡ ሦስተኛ፤ የብልጽግና ፓርቲ ካሸነፈ በጀመረው መልካም የሃገር ግንባታ ስራ መቀጠል አለበት፡፡ የተጀመሩ አዳጊ ፕሮጀክቶችን እያስቀጠለ፣ ሙስናን እየታገለ፣  ልማትን የሚያሳድግ ስራ እንደሚሰራ አምናለሁ። ኢትዮጵያን ከሃብታም ወይም ተፅዕኖ ፈጣሪ ሃገሮች ተርታ የማሰለፍ  ራዕይን ተግባራዊ ለማድረግ ብርቱ ጥረትን ይጠይቃል። የጁንታና አሸባሪ ሃይሎችን ደጋፊና አጫፋሪዎች መስመር በማስያዝና የህግ  የበላይነትን  በማስከበር፣ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ማስቀጠል ይገባል፡፡ በብሔር ማንነት  መኩራት ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን ፅንፈኞችና ኢትዮጵያዊ ዜግነትን ለድርድር የሚያቀርቡ አካላት ላይ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ፣ የሃገርን አንድነት ማስቀጠል አለበት፡፡ አሸናፊው መንግስት እነዚህን ሶስት ጉዳዮች እንዲያስቀድም እሻለሁ፡፡ በሌላ በኩል፤ የመንግስት ስራ በቴክኖክራቶች ቢሰራ፣ ካድሬዎች የፖለቲካ ጉዳይ ላይ ብቻ ቢያተኩሩ እመኛለሁ፡፡ ከፓርቲ ውጪ የሆኑ ሰዎች የሚመሯቸው ተቋማትን መመስረትም ያስፈልጋል፡፡ አዲሱ መንግስት ይሄን ማድረግ ከቻለ ለኢትዮጵያ ህዝብ ባለውለታ ይሆናል፡፡  

    

Read 6310 times