Monday, 28 June 2021 00:00

"ተደጋግፈው መቆም ያልቻሉ ተያይዘው ወደቁ"

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)


“እንግዳ ካልመጣ ሁሉ ሴት፤ ክረምት ካልገባ ሁሉ ቤት” ይላሉ አበው፡፡ የቤተሰቡ አባላት ሌላ ጣዕም ስለማያውቁ እመቤቲቱ የሰራቸውን ሁሉ አመስግነው ይመገባሉ። እሷም ብትሆን ቤተሰቡን ከአንድ አይነት ጣዕም ጋር አላምደዋለችና የሙያ ችግር ያለባት ሆና አትታይም፡፡ እንግዳው ግን አዲስ ስለሆነ ምን እንደሚጥመው አይታወቅም። ጓደዋ ምን እንደሚጎድለው ወለል ብሎ የሚታያትም በዚያን ጊዜ ነው፡፡ ሳር ቤትም እንዲሁ ብርሃን በቀላሉ ስለማያሳልፍ ደህና ነው ተብሎ ሊታመን፣ ክረምቱን ሊያወጣን ይችላል ተብሎ ተስፋ ሊጣልበትም ይችላል። በዝናቡ ጊዜ ግን ሁሉንም ነገሩ ሊያፈስና መቆሚያ መቀመጫ ሊከለክል ይችላል፡፡
በሀገራችን የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ በፓርቲም ሆነ በነጻነት ግንባር መደራጀት ከተጀመረ ጊዜ  አንስቶ ስናየው የኖርነው፣ እያንዳንዱ ድርጅት ጠንክሮ ሲወጣ ሳይሆን እርስ በርስ መገፋፋት እየተከሰተ፣ የተቋቋሙት እየፈራረሱ ሌላ አዳዲስ ድርጅት እየተፈለፈ ሲወጣ ነው፡፡ አልተመቸንም ብለው እራሳቸውን ነጥለው ያደረጁ ወገኖችም  ውስጥ ሌላ ያልተመቸው እየተፈጠረ፣ ይበልጥ  አዲስ ስብስብ እየተፈጠረ፣ ኃይል እየተበተነ ሲሄድ ነው የኖረው በፒለቲካ ጎራ፡፡
የሕወሃት ኢህአዴግ መንግሥት ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል እንደሚቻል በሕገ መንግሥት የታወቀ መብት በመሰጠቱ፣ ሰላማዊ ትግል ለማድረግ የተመሠረቱ ድርጅቶችንም የጠበቃቸው ይኸው የአማፂዎቹ መንገድ ነው፡፡ በእነሱ ዘንድም አብሮ ለትግል ተነስቶ አብሮ ትግልን ከዳር ማድረስ ታይቶ አይታወቅም፡፡
ለራሳቸውም ለዜጎችም ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት እንታገላለን ብለው የተደራጁ ወገኖች፤ በየቤታቸው የአባላቶቻቸውን ድምፅ ሲያፍኑ፣ በራቸውን ለውይይትና ለድርድር ዝግ ሲያደርጉ ደጋግመን ታዝበናል፡፡
የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት ጥያቄችንን አልተቀበልንም ያሉ የመአሕድ ወጣቶች፤ የኢትዮጵያዊያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲን (ኢዴፓን) መመሥረታቸው፣ አንድነት ለፍትሕና ለዲሞክራሲ (አንድነት) ፓርቲ “ከሕገ ደንቡ የወጣ አሠራር እየተከተለ ነው” ብለው ተቃውሞ ያነሱ ወገኖች “ዝም አንልም” በሚል ከድርጅቱ መሪዎች ጋር ከፍተኛ ግብግብ ውስጥ በመግባት ፤ጥረው ግረው አልሳካ ሲላቸው፣ ሰማያዊ ፓርቲን መመስረታቸው ሳይጠቀስ አይታለፍም፡፡
ይህ እየተበታተኑ የመሰብሰብ ልማድ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች ደካማ ከማድረጉም በላይ በስልጣን ላይ ያለው ገዥ ፓርቲ የሚገዳደረው እንዲያጣም አድርጓል፡፡ በሌላ በኩል  ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄውን የሚያነሳለት፣ መብቱን የሚሟገትለት በማጣቱ የተነሳ በሀገሩ ላይ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን የሚያስከብርለት፣ በሕግ የበላይነት የሚያምንና ለሕግ የሚገዛ መንግሥት ለማቆም የሚያደርገውን ትግል ያራዘመበት ሲሆን ህዝቡ የሚከፍለውን መስዋዕትነት ከልክ በላይ እንዳበዛበት መካድ አይቻልም፡፡
ለሕዝብ ጥያቄ መልስ ለማስገኘት በግንባር ቀደምትነት ብዙ መንገላታት፣ መታሰር መፈታት፣ መሰደድና የአካል ጉዳት የደረሰባቸው፣ ሕይወታቸውን ሳይቀር የገበሩ  ወገኖች እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ለእርሱ ከፍ ያለ አክብሮት አለኝ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የፓርቲ ፕሬዚዳንት፣ ዋና ፀሐፊ ወዘተ በመሆን ለሚገኘው ስም፣ ክብርና ልዩ ልዩ ጥቅም ልባቸውን የሰጡ፣ መለወጥና አዲስ ሃሳብ መቀበል የማይዳዳቸው፣ የፖለቲካ ትግል ሜዳውን የወረሩት በመሆኑ ሕዝብ ጤነኛውን ከበሽተኛው ለመለየት ከባድ እንደሚሆንበት መገንዘብ አያዳግትም፡፡
ወደ መነሻዬ ልመለስ፡፡ አንድ ነገር ኮሽ ባለ ቁጥር መግለጫ በማውጣት  ማንም የማይቀድማቸው፣ “ሕዝብ ከእኛ ጎን ነው” እያሉ የሚያደነቁሩን የፖለቲካ ፓርቲዎች  እንደሚሉት፤ በርግጥም ሕዝብ ከእነሱ ጋር መሆን አለመሆኑን የሚያረጋግጥልን በየአምስት ዓመቱ የሚካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ነው፡፡ በአዲሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ አዋጅ መሰረት፤ የሀገር አቀፍ ፓርቲ ሆነው ለመመዝገብ የ10ሺ ሰዎች ፊርማ፣ የክልል ፓርቲ ሆነው ለመመዝገብ የ4ሺ ሰዎች ፊርማ እንዲያቀርቡ የተገደዱና ይህን አሟልተው ለመመዝገብ የቻሉት ፓርቲዎች፤ ለሚወዳደሩባቸው ምክር ቤቶች በበቂ ቁጥር እጩ ተወዳዳሪ ለማቅረብ አለመቻላቸውን ስናይ፣ በትዝብት ራሳችንን እንድንይዝ ያስገድደናል፡፡
በተወዳደሩባቸው የምርጫ ክልሎች በሚገኙ የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች ውስጥም በበቂ ቁጥር ታዛቢ ለመመደብ አለመቻላቸው ሌላው የደካማነታቸው መገለጫ መሆኑን አለመታዘብ አንችልም፡፡
የ1992 ዓ.ም የተወካዮችና የክልል ምክር ቤት ምርጫ ከመካሄዱ ጥቂት ቀደም ብሎ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች “ተባበሩ ወይ ተሰባበሩ” የሚል ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ይሰጥ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ይህን ምክር ተቀብለው በ97 ምርጫ ለመወዳደር ተባብረው የቀረቡት ቅንጅትና ሕብረት፤ ከ150 በላይ የተወካዮች ምክር ቤት ወንበር ለማሸነፍ መቻላቸው አይዘነጋም፡፡
 ከዛሬ ሁለት ዓመት ግድም ጀምሮ “ተባበሩና አንድ ጠንካራ ኃይል ፍጠሩ” የሚለውን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተደጋጋሚ ውትወታ ፓርቲዎቹ አልተቀበሉትም፡፡ ያለመተባበርን ጎጂነት በትንሹም ቢሆን የተረዱት ኢዜማና ሕብርም ቢሆኑም፣ ህብረት ለመፍጠር ሲንደፋደፉ ያባከኑት ጊዜ አሁን ዋጋ እንዳስከፈላቸው መረዳት አያቅታቸውም ብዬ አስባለሁ፡፡  በነባር ፓርቲዎች ውስጥ ገብቶ ከማጠናከር ይልቅ በአዲስ ስም ብቅ ብቅ ያሉት ፓርቲዎችም ተያይዞ ለመውደቅ ማገልገላቸው ሚስጥር ሊሆን አይችልም። ሃሳቤን “ተደጋግፈው መቆም ያልቻሉ ተያይዘው ወደቁ” በሚል ብቋጨው ይቀለኛል፡፡
በዘንድሮ ምርጫ ያመጡት ውጤት አመርቂ ባይሆንም፣ ኢዜማና ባልደራስ እንዲሁም ነፃነትና እኩልነት የተባሉት ፓርቲዎች፣ አዳዲስ ፖለቲከኞቻችን ወደ ፖለቲካ መድረኩ በማምጣታቸው ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ ከዘንድሮ ምርጫ ተምሮ ለከርሞ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መትጋት ከሁሉም ፓርቲዎች ይጠበቃል፡፡
ለሁሉም ፈጣሪ ሰላሙን ያብዛልን!

Read 2331 times