Sunday, 27 June 2021 17:19

ፅንሱ ተወልዷል፤ እንክብካቤ ግን ይፈልጋል!

Written by  ደስታ መብራቱ
Rate this item
(2 votes)

 "-ብልጽግናም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ይህንን ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ለመወጣት በምርጫ ዘመቻው ወቅት ከነበሩበት የተፎካካሪነትና በአንዳንድ ሁኔታም የባላንጣነት ስሜት በመውጣት የጋራ ሃገራዊ ባለአደራነት ስሜት ሊይዙ ይገባል። ይህንንም ለማሳካት የትብብር ጥረቶቻቸውን በምርጫው ክርክር ወቅት እየነጠሩ በወጡ የጋራ እሳቤዎች ላይ መገንባት ጠቃሚ ይሆናል።--"

    ከሃያኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ አንስቶ ሃገራችን ኢትዮጵያን ለዘመናት ተጭኖባት ከነበረው የአገዛዝ ሥርዓት ወደ ዲሞክራሲያዊ የህዝብ አስተዳደር ሥርዓት ለማሸጋገር ብርቱ ጥረት ተደርጓል፣ በርካታ መስዋዕትነትም ተከፍሏል። ባለፉት ሶስት ዓመታትም በሌላ የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ በማለፍ ላይ ትገኛለች። የዚህ የለውጥ ዕድል መጨናገፍ ሃገራዊ ቀጣይነትን አደጋ ውስጥ ይከታል ተብሎ ስለሚታመን ምናልባትም እንደ ሃገር የመጨረሻው የሽግግር ዕድል ሊሆን ይችላል ተብሎ ይነገራል።  የየትኛውንም ሃገር ታሪክ ስንመለከት፣ ከአገዛዝ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረግ ሽግግር አልጋ በአልጋ በሆነ ሁኔታ ውስጥ የተከናወነ ሳይሆን በብዙ ፈተና ውስጥ ያለፈና ከፍተኛ መስዋዕትነት የጠየቀ መሆኑን እንረዳለን። እነኚህ ፈተናዎች፣ የተለያዩ ቅርጽና ይዘት ይዘው የሚቀርቡ ቢመስሉም፣ በዋነኝነት ለዘመናት ስር ሰዶ በኖረው የአገዛዝ አስተሳሰብና በዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ መካከል የሚደረግ ትንቅንቅ ውጤቶች ናቸው። የዚህ ትንቅንቅ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ማዘንበል ዋነኛው መገለጫ ደግሞ ህዝቦች በነፃነት የሚያስተዳድሯቸውን መሪዎች ለመምረጥ የሚያስችላቸውን እርምጃ መጀመራቸው ነው። በ2010 የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ባለፉት ስድስት ወራት በሃገራችን በተካሄዱ አበይት የምርጫ ዝግጅቶችና ቅስቀሳዎች ታጅቦ ‘በስድስተኛው’ ሃገራዊው ምርጫ ተጠናቋል።
በምርጫ ዘመቻው የመጨረሻ ሳምንት፣ የተለያዩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የየራሳቸውን ቅድመ ምርጫ ግምገማ በማካሄድ የጋራ መግለጫ ሲሰጡ ተደምጠዋል። የእነኚህ ግምገማዎች ዋነኛ ትኩረት፣ በእጩና መራጮች ምዝገባ ወቅት ባጋጠሙ ችግሮችና በተለያዩ አካባቢዎች በደረሱባቸው እንግልቶችና ጥቃቶች ላይ ሲሆን በዚህ ላይ በመመርኮዝም የቅድመ ምርጫው ሂደት ‘ዝቅተኛ የሚባለውን የዲሞክራሲያዊ ምርጫ ሂደት የማያሟላ እንደነበር’ አጠቃለዋል።  በመሰረቱ፣ እነኚህን ጉድለቶች ማመላከቱ ለወደፊትም መሰል ስህተቶች እንዳይፈጸሙ ተገቢና ጠቃሚ እርምጃ ነው። ነገር ግን በዚህ ላይ ተመርኩዞ አጠቃላይ የቅድመ ምርጫውን ሂደት ማኮሰስና የምርጫውን ውጤት ተዓማኒነት አስቀድሞ ጥያቄ ውስጥ ማስገባት ከአገዛዝ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለሚደረገው ሽግግር ጠቃሚ አይደለም። ከዚህ ይልቅ፣ በቅድመ ምርጫ ወቅት ላጋጠሙ ፈተናዎች ዋነኛ መዋቅራዊ ምንጭ የሆኑትን በመለየት መድሃኒቱን በጋራ መሻት ላይ ማተኮሩ ይበጃል። በእኔ እይታ፣ ከላይ ለተጠቀሱት ችግሮች ዋነኛ ምንጮቹ ሁለት ናቸው። የመጀመሪያው፣ ሁሉም ፓርቲዎች ውስጥ ከአገዛዝ አስተሳሰብ ሙሉ ለሙሉ ያልተላቀቁ አባላቶችና አመራሮች መኖራቸው ነው። ይህ ችግር፣ በአንዳንድ የክልል ብልጽግና ፓርቲ መዋቅር ውስጥ ጎልቶ የሚታይ ቢመስልም፣ በሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ውስጥ ያለ መሆኑን የሚጠቁሙ ምልክቶችም አሉ። ስለዚህም፣ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ቆመናል የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ ይህንን የአገዛዝ አስተሳሰብ ከየድርጅቶቻቸው ውስጥ የማጽዳት ሃላፊነት ይኖርባቸዋል። ሁለተኛው የችግሮቹ ዋነኛ ምንጭ፣ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መፈጠር ዋነኛ መሰረት የሆኑት ተቋሞች በተሟላ አቅም ተደራጅተውና ጎልብተው አለመገኘታቸው ነው። ይህ ሁኔታ ላይ ከተጠቀሰው የአገዛዝ አስተሳሰብ ጋር ተዳምሮ በርካታ ፈተናዎችን ሊፈጥር እንደቻለ መገመት ይቻላል።
ይህ እንዳለ ሆኖ፣ ከላይ የተጠቀሰው የፖለቲካ ፓርቲዎች ግምገማ ትልቁ ድክመት በቅድመ ምርጫ ወቅት የነበሩትን ፈተናዎች ከመዘርዘር ባለፈ፣ ተቋማዊ መሰረቶችን በመፍጠር ረገድ ለታየው ለውጥ ተገቢውን እውቅና አለመስጠቱ ነው። ለምሳሌም ያህል፡ በተለያየ ወቅት የብልጽግና ፓርቲ በግልጽ ካራመዳቸው ፍላጎቶችና አቋሞች ተቃራኒ የሆኑ ውሳኔዎችን በመወሰንና ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በማሳተፍ ከገዢ ፓርቲው ተጽእኖ ነፃ መሆኑን ለማስመስከር የጣረ የምርጫ ቦርድ መኖር እውቅና ሊቸረው የሚገባ ለውጥ ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ፣ በተደጋጋሚ ምርጫ ቦርድ የሰጣቸውን ውሳኔዎች በፍርድ ቤት በተሻሩበት ወቅት የፍርድ ቤትን ውሳኔ ተቀብሎ ለመተግበር የሄደበት ርቀት፣ የቦርዱን ለህግ ተገዢነትና የፍርድ ተቋማትንም የነፃነት ድክ ድክ ጅማሮ የሚያመላክት ተስፋ ሰጪ ለውጥ ነው። እዚህ ላይ፣ የባልደራስ ለዕውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በምርጫ ቦርድ ውሳኔ ላይ ያለውን ቅሬታ በተደጋጋሚ ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ ያስመዘገበው ውጤት በሁሉም ፓርቲዎች እንደ ምሳሌ ሊወሰድ የሚገባው ነው።  በዚሁ የለውጥ ወቅት፣ በታሪካችን ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የሚከሰቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመመርመር የመንግሥታዊ አካላትን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ የሚጥረው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም የራሱን ድርሻ በማበርከት ላይ ይገኛል። ከላይ ከተጠቀሱት ተቋማዊ ለውጦች በተጨማሪ፣ በሃገሪቱ የሚገኙ የሚዲያ ተቋማት ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች  የምርጫ ቅስቀሳ በፍትሃዊነት እንዲያገለግሉ የተዘረጋው ሂደትና የሚዲያ ተቋማቱም ያደረጉት ጥረት እጅግ አበረታች ነበር ማለት ይቻላል። ለእነኚህ መሰረታዊ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ተቋማት ጅምር ጥረቶችና ውጤቶች እውቅና ሳይሰጡ፣ ባጋጠሙ እክሎችና ፈተናዎች ላይ ብቻ ተመርኩዞ ስለ ምርጫው ቅድመ ብያኔ ለመስጠት መሞከር የተፎካካሪ ፓርቲዎቹን ጥረት ጎዶሎ አድርጎታል።
በአጠቃላይ ባለፉት ስድስት ወራት የነበረው የምጥ ዘመን ከዚህ በላይ በተዘረዘሩት ፈታኝና ተስፋ ሰጪ ሂደቶች ውስጥ አልፎ ጨቅላው ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ተወልዷል ማለት ይቻላል። ነገር ግን፣ ይህ ጨቅላ ወደ ተሟላ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲያድግና እንዲጎለምስ ከተፈለገ፣ በህክምና ቋንቋ እንደሚባለው ልዩ የሆነ የጨቅላ እንክብካቤ (neonatal care) ያስፈልገዋል። የዚህ ደግም ዋነኛው ባለአደራዎች የፖለቲካው መሪ ተዋንያን የሆኑት የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው። ለዚህም የመጀመሪያው እርምጃ የምርጫውን አጠቃላይ ሂደት ጉድለቶች ብቻ ሳይሆን ጠቃሚ ውጤቶቹን፣ የተከናወነውን ብቻ ሳይሆን ቀሪ ሥራውን፤ ጨለማውን ብቻ ሳይሆን ብርሃኑን፣ ፈተናዎቹን ብቻ ሳይሆን ዕድሎቹን እውቅና መስጠትና በጠቃሚ ውጤቶቹና ዕድሎቹ ላይ ለመገንባትና የሚያስፈልጉ ቀሪ ሥራዎችን ለማከናወን መዘጋጀት ነው። ከዚህ በተጨማሪ፣ ይህ ምርጫ በጥቂት የፖለቲካ ቡድኖች ከሚፈጠር የሽግግር ሥርዓት ይልቅ በህዝብ ይሁንታ ላይ የተመረኮዘ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር የመጀመሪያው እርምጃ መሆኑን መገንዘብና ለሽግግሩ መሳካት አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀትን ይጠይቃል። በዚህ ረገድ፣ የምርጫው የመጨረሻ ውጤት ምንም ይሁን ምን፣  ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች የየራሳቸው ድርሻና ሃላፊነት ይኖርባቸዋል።  በተለይም በሥልጣን ላይ ያለው የብልጽግና ፓርቲ የሽግግር ሥርዓቱን በጠንካራ መሠረት ላይ በመትከል ረገድ ልዩ የታሪክ ሃላፊነት ይጠብቀዋል።
ብልጽግናም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ይህንን ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ለመወጣት በምርጫ ዘመቻው ወቅት ከነበሩበት የተፎካካሪነትና በአንዳንድ ሁኔታም የባላንጣነት ስሜት በመውጣት የጋራ ሃገራዊ ባለአደራነት ስሜት ሊይዙ ይገባል። ይህንንም ለማሳካት የትብብር ጥረቶቻቸውን በምርጫው ክርክር ወቅት እየነጠሩ በወጡ የጋራ እሳቤዎች ላይ መገንባት ጠቃሚ ይሆናል። ከእነዚህ የጋራ እሳቤዎች ወስጥ ቀዳሚው፣ ሃገራዊ መግባባትና አንድነትን ለማጠናከር የብሔራዊ መግባባት ውይይት አስፈላጊነት በሚመለከት የተደረሰው ተመሳሳይ አመለካከት ነው። የዚህን ጉዳይ አስፈላጊነት ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው ዘመቻ ወቅት በተለያየ አጽንኦት ሲያነሱት ተደምጠዋል። ስለዚህም፣ ሁሉንም ወገኖች አካታች የሆነ የብሔራዊ መግባባት ውይይት ማደራጀት የሽግግሩ ወቅት ቀዳሚው እርምጃ ሊሆን ይገባዋል። ይህንንም ለማሳካት በምርጫ ዘመቻው ወቅት ከነበረው የፓርቲን መርሃ ግብር (manifesto) ከሰማይ እንደወረደ ቅዱስ መጽሐፍ አድርጎ የማቅረብ አዝማሚያ መውጣትና ለሃገሪቱ የረዥም ዘመን ቀጣይነትና ለህዝቦቿ ሁለንተናዊ ደህንነትና ልማት የሚበጁ የመግባቢያ ሃሳቦች ላይ ማተኮር ያስፈልጋል።  
ሌላው ከምርጫ ክርክሮቹ የወጣው የጋራ ዕሳቤ፣ አሁን በስራ ላያ ያለውን ህገመንግሥት የማሻሻል አስፈላጊነት ነው። ይህ ጉዳይ በተለይም ከአንድ ዓመት በፊት ገኖ ይሰማ ከነበረው ህገመንግሥቱን እንዳለ የማስወገድ ወይም ምንም ሳይነካ አስጠብቆ መሄድ ጋር ተያይዞ ከነበረው ተቃራኒ አቋም አንፃር ሲታይ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው መነሻ ሃሳብ ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ ቀዳሚ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው የህገመንግሥቱን አጠቃላይ መንፈስና አተረጓጎሙን ለአገዛዝ ሥርዓት አመቺ እንዲሆን ያደረጉትን የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ቅኝቶች ለይቶ ማውጣትና ለዘመኑ የሚመጥኑ ማሻሻያዎችን ማድረግ ሊሆን ይገባዋል። በዚያው መጠን፣ በፖለቲካ ፓርቲ መርሃ ግብርና በህገ መንግሥት መካከል ያለውን ልዩነት ጠንቅቆ መረዳት የኢህአዴግን ስህተት ከመድገም ያድናል። በዚህ ሂደት ውስጥ፣ የግለሰብና የቡድን መብቶችን አጣጥሞ ማስከበር፣ ሃገራዊ አንድነትንና የብሔረሰቦችን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ማጣጣም፣ እና የፖለቲካና ማህበራዊ መብቶችን ከዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ልማት ጋር የሚያሳልጡ የመስተዳድር መዋቅሮችን መፍጠር አቢይ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው።
በመጨረሻም፣ ምንም እንኳን ከኢህአዴግ በተረከባቸው የአገዛዝ ውርስ እዳዎች በከፍተኛ ሁኔታ የተፈተነ ቢሆንም፣ ይህንን ተቋቁሞ ተስፋ ሰጪ የሆነ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ጅማሮ ላሳየን ለብልፅግና ፓርቲና ለለውጡ አመራር ተገቢውን እውቅና ልንሰጥ ይገባል። ከዚህ በተጨማሪ፣ ስር የሰደደ የአገዛዝ አስተሳሰብ በሰፈነበት ሃገር ውስጥ ያለውን ከባድ ፈተና ተጋፍጠው የዲሞክራሲያዊ ፉክክር ሜዳውን ፍትሃዊ ለማድረግ ለጣሩት ተቋማትና አመራሮቻቸው የሃገር ባለውለታ መሆናቸውን መመስከር ተገቢ ነው። ከሁሉም በላይ ግን፣ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን አልመው ፈታኝ በሆነ የለውጥ ሂደት ውስጥ የተሳተፉትን የፖለቲካ ፓርቲዎችና አመራሮቻቸውን እውቅና ልንሰጣቸውና ልናከብራቸው ይገባል። እስካሁን የተመጣበት መንገድ ፈታኝ የመሆኑን ያህል፣ ጨቅላውን የዲሞክራሲ ሥርዓት እንዲጎለብት፣ እንዲድህና እንዲሮጥ የማድረጉ ሥራ ይበልጥ ትዕግስትን፣ ዕውቀትንና ማስተዋልን የሚጠይቅ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ይህንን ሂደት የተሳካ ለማድረግ፣ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ፉክክር መለያው ከሆነ የተቃዋሚ ፖለቲካ ቅኝት፣ ትብብር መለያው ወደሆነ የሽግግር ፖለቲካ (transition politics) ቅኝት መሸጋገር ይኖርባቸዋል። መላው ህብረተሰብም፣ በተለይም ምሁራንና ወጣቱ፣ ለዚህ የሽግግር ሂደት ሰላማዊነትና ውጤታማነት የበኩሉን ድርሻ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል።  
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊው ደቡብ አፍሪካ በሚገኘው ስታለንቦሽ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ሲሆኑ የአፍሪካ ሳይንስ አካዳሚም አባል ናቸው።

Read 1414 times