Print this page
Sunday, 27 June 2021 17:12

ሰው ምን ይለናል በሉ!”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ከመስመር ወጣ ሲባል...“ኸረ አንቺ ልጅ ሰው ምን ይለኛል በይ! የሚባል ነገር ነበር። አሁን ነገሩ ሁሉ “ስለ ሰው፣ ስለ ሰው ቀድጄ ልልበሰው፣” ሆነና ወላ “ሰው ምን ይለኛል! የለ፣ ወላ ይሉኝታ የሚባል ነገር የለ። የእውነት እኮ የብዙዎቻችን ባህሪይ “ምን እየሆንን ነው?” የሚያሰኝ ነው፡፡ የምር እኮ አንደው “ሰው ምን ይለኛል?” ማለቱ እንኳን ቢቀር ትንሽዬዋ ይሉኝታ የሚሏት ነገር ድራሿ እየጠፋ ነው፡፡ አለ አይደል...ራስን የሚጎዳና ወደሞኝነት የሚጠጋ የራስ የሆነውን ከአፍ ላይ የሚያሰነጥቅ አይነት ይሉኝታ ሳይሆን ህብረተሰብን ከሚያስቀይምን ብሎም ሊጎዳ ከሚችሉ ባህሪያት እኮ የሚጠብቀን አንዱ ጊዜውንና ቦታውን የጠበቀ ይሉኝታ ነው፡፡
ቀደም ባሉት ዓመታት ነው አንድ የምናውቀው ሰው ነበር፡፡ በቃ ሲያዩት ምን አለፋችሁ...ትንሸድ ተበልቶ ብዙ የሚራገፈውን አይነት ሳይሆን ዘይት የሚባል ነገር የነካው ምግብ ከቀመሰ ሦስት የዓለም ዋንጫ ጨርሶ አራተኛውን የሚጠብቅ የሚመስል፡፡ ምን አለፋችሁ...ቅቤ የጠጣ ቅል የሚሉት አይነት ነው፤፡ እናላችሁ...የሆነ ምግበ ቤት ምናምን አንድም ሆናችሁ፣ ሰባትም ሆናችሁ ስትመገቡ ከደረሰ ከሰላምታ በፊት ወንበር ስቦ ቁፋሮ ይገባል፡፡ እናላችሁ...ሰላምታ የሚሰጠው ሁለት ሦስት ጊዜ ከጎረስ በኋላ ነው፡፡ “እሺ... እንዴት፣ እንዴት ይዟችኋል?” ይላል...እሱ ‘በግሬደር ስታይል’ ምግባችሁን እፍስ ሲያደርገው እናንተ የተራበ አንጀት ደግሞ ኩርምት! 
ምን መሰላችሁ... እንግዲህ ጨዋታም አይደል፣ ሰውየው እኮ... “እሱስ ምን ያድርግ፣ እየራበው ይሆናል...” እንዳይባል እንኳን ምግብ ምናምን ሊቸግረው ቀርቶ በየወሩ ድል ያለ ግብዣ ቢያደርግ ምኑም የማይነካበት አይነት ሰው ነው፡፡ አለ አይደል.... ተርፎት ተተትረፍርፎት ሌላውን መቀለብ የሚችል፡፡ ግን... በቃ ልማድ ሆኖበት ነው የሚባለው፡፡ ቤተሰብና ወዳጅ ዘመድ... “ኸረ እባክህ ሰው ምን ይለኛል በል!” ሲለው ስቆ ነው የሚያሳልፈው፡፡
(ስሙኝማ... እንዲህ አይነት ሰዎች እኮ ሰው በጎሪጥ እያያቸው መሆኑን እያወቁ፣ የቡና ዙሪያና የድራፍት ዙሪያ ዋና አጄንዳዎች መሆናቸውን ...እያወቁ እንደ አንድ ሰሞን የ‘ቦተሊካ አማርኛዋ’... አይሞቃቸው፣ አይበርዳቸው! የምር ግን...አንዳንዴ እኮ የሀገራችንን ሁኔታ እያየን እንዲህ አይነት አይሞቃቸው፣ አይበርዳቸው ሰዎች ምን ያህል የታደሉ ናቸው ትላላችሁ! የቸገረው ስንት ነገር ‘ያድርግ’ የለ! (ቂ...ቂ...ቂ...)
ምን አለ መሰላችሁ...የሆነ ለማድ ይኖራችሁመና “ኸረ እባክህ ሰው ምን ይለኛል በል!” እየተባለችሁም ትቀጥላላችሁ። እናላችሁ...ምን ይሆናል መሰላችሁ... ነገርዬው በህሪይ ይሆንና ወዳጅ ዘመድም መጨነቁን ይተዋል፡፡
እናማ... ብዙ “ኸረ እባካችሁ ሰው ምን ይለናል በሉ!” የሚያሰኙ ነገሮች መአት ናቸው፡፡
ጋባዦች፣ “ኸረ እባክችሁ ሰው ምን ይለናል በሉ!” ለሀምሳ ሰው ምግብ አዘጋጅታችሁ አምስት መቶ ሰው መጥራት ምን የሚሉት ሂሳብ ነው! በቃ ይሄ ቪዲዮ የሚሉት ነገር ካልቀረ ሰው እኮ ምሳ ተጋብዞ አይደለም ሊጠግብ በቂ ውሀ ሳያገኝ እየተመለሰ ነው፡፡
“አዳራሹ እንዴት እንደተጨናነቀ ይታይሀል? መተንፈሻ ሊያሳጡን እኮ ነው፡፡ ሰርግ ቤት ነው ስታዲየም!”
“ገና መች ሰው መጥቶ አለቀና!”
“ለመሆኑ ስንት ሰው ነው የጋበዙት?” 
“የሰማሁት ወደ አንድ ሺህ እንደሚጠጋ ነው፡፡”
“ሰዎቹ አብደዋል እንዴ! የቢፌውን ጠረዼዛ አይተኸዋል? መቶ ሰው ሳይደርሰው ምግቡ ባያልቅ ምን አለ በለኝ!”
“ጌታው፣ ሰዉ የተጋበዘው እንዲበላና እንዲጠጣ ሳይሆን ቪዲዮ እንዲያዳምቅ ነው፡፡”
 ለዚህ ጉዳይ መፍትሄ ሊሆን የሚችል ሀሳበ አለን... ለየሰዉ በሚላከው ግብዣ ወረቀቱ ላይ “የደስታችን ተካፋይ እንዲሆኑ...” የምትለዋ ሀረግ ጥገናዊ ለውጥ ይደረግላትና... “ግብዣችን ላይ በመገኘት እኛን አስደስተው እርሶ ይሳቀቁ...” በሚል ይስተካክልለን፡፡ ለብቻው መሳቀቅ ሰልችቶት ‘በጋራ መሳቀቅ’ የናፈቀው መሄድ ይችላል!
“አይገርምህም... ልክ ጠረዼዛው አጠገብ ስደርስ ምግቡ ሁሉ እልቅ አይል መሰለህ! በቃ አንጀቴ ሦስት ቦታ ብጥስ ሲል ይታወቀኛል፡፡” ቆይማ...አድማጩም እንዳይሳቀቅ አስቡለት እንጂ! ከፈለጋችሁ ጋባዣችሁን በምድርም ክሰሱት፣ በሰማይም አሳጡት እንጂ “እኔ ተሳቅቄማ ማንም አይቀራት!” ነገር አታድጉታ! አሁን ማን ይሙት ሦስት ቦታ ድረስ መቆራረጥ የሚችል አንጀት አለና ነው! አሀ...ልክ ነዋ! የስንቱ አንጀት ሦስት ሳምንት ሙሉ ሰሜን ዋልታ በረዶ ውስጥ ተቀብሮ የቆየ ‘ጮርናቄ’ መስሎ... አለ አይደል... ማጋነንምም ልክ ይኑረው ለማለት ነው፡፡
(ስሙኝማ... እንግዲህ ጨዋታም አይደል... የአንጀት ነገር ካነሳን አይቀር፣ “ውይ እሱ ሰውዬ፣ ሳየው እኮ አንጀቴን ብልት ነው የሚያደርገኝ!” የምትለዋ ‘ዲፕሎማሲያዊ’ ነገርዬ አሁን፣ አሁን ቀረች እንዴ!)
አንዳንድ የጥገናና የቴክኒክ የምትባሉት አይነት ሠራተኞች “ኸረ እባክችሁ ሰው ምን ይለናል በሉ!”
“ምጣድ ታድሳለቸሁ?”
“በደንብ፣ እንደውም በዋነኛት ምጣድ ነው የምናድሰው፡፡ ምን ሆኖብሽ ነው?”
ሀይሉ ቀንሶብኝ ነው፡፡ አንድ እንጀራ ለማውጣት ዓመት ነው የሚፈጀው፡፡"(አሁንም... ለአድማጩ ይታሰብለት፡፡ የፈለገ... “ጊዜ ዋጋ ያጣባት ሀገር እየመሰለች ነው...” ብንልም ለአንድ እንጀራ አንድ ዓመት! እስከሚቀጥለው የአውሮፓ ሀገራት እግር ኳስ ዋንጫ እኮ አራት ብቻ ልንጋገር ነው!)
“ነገ ጠዋት ተመልሰሽ ነይ፡፡” ‘ነገ ጠዋት’ ከች ይላል፡፡
“ምጣዱ ደረሰልኝ?”
“አዎ፡፡ እንዴት አለፋሽ መሰለሽ! ጊዜውን በሙሉ እሱ ላይ ነው የጨረስነው፡፡ ምን አደርጋችሁት ነው?” ‘እነሱ ሰዎች’ እኮ ቴረር ሲለቁባችሁ ለነገ ብሎ ነገር አያውቁም፡፡ ምጣዱ እኮ የሆነ ቦታ ላይ ሽቦ ተላቆ እሷኑ ቋጠር አድርገው ነው፡፡
“ሂሳብ ስንት መጣ?”
“ሁለት መቶ ሀምሳ ብር!”
“ምን”?
“እንደውም ለአንቺ ብለን ነው እንጂ በዚህ ዋጋ ሠርተን አናውቅም፡፡”
ቤት ወስዳ ስትሞከረው...ከአንደኛ ደረጃ ነጭ ጤፍ አንደኛ ደረጃ ሬንጅ የመሰለ ጥቁር እንጀራ አውጥቶላት እርፍ!
እናማ... ብዙ “ኸረ እባካችሁ ሰው ምን ይለናል በሉ!” የሚያሰኙ ነገሮች መአት ናቸው፡፡
እውቀት ከአቅማችሁ በላይ በዝቶባችሁ... የማናውቀው ነገር የለም አይነት የሚዳዳችሁ  አይዛክ ኒውተኖች “ኸረ እባክችሁ ሰው ምን ይለናል በሉ!” (ኒውተን “ሁሉን አውቃለሁ ይል ነበር...” ለማለት ሳይሆን እንደው...አለ አይደል... ‘ነገር በምሳሌ፤’ እንዲሆን ነው።) ስሙኝማ...እግረ መንገድ ከ‘ነገር በምሳሌ’ ተከትሎ የሚመጣው ‘ጠጅ በብርሌ’ የተተወው ጠጅ የሚመስል ነገር ‘ዩዝ ኤንድ ስሮው’ በሚመስል የላስቲክ ብርጭቆ በሚሰጥበት ዘመን ግፍ ይሆናል በሚል ነው። ከራስ ‘ኤክስፒሪየንስ’ በመነሳት ሳይሆን ከመረጃና ከማስረጃ ነው፡፡
እኔ የምለው...እንግዲህ ጨዋታም አይደል፣ እነእንትና ኑሮ እንዲህ በከፋበት ዘመን በየቀኑ ቢጫ በቢጫ የምትሆኑት እንደ ድሮው በስሙኒ ሁለት ብርሌ ጠጅ እንደገና ተጀመረ እንዴ! ግራ ያጋባላ! ኮሚክ እኮ ነው... ይሄኔ እኮ  መስከር የሚናፍቃቸው ወዳጆቻችን ይኖሩ ይሆናል፡፡ የሆነ ነገር እመኮ ምንም ነገሬ ሳትሉት የኖራችሁት ነገር ልታገኙት እንደማትችሉ ስታውቁ የሚናፍቃችሁ ለምንድነው? (እንትናዬ፣ እንዴት ይዞሻል! ሰላም ስልሽ ከብዙ ጊዜ በኋላ ነው፣ አይደል! አይ ምንም የተለየ የናፈቀኝ ነገር ኖሮ ሳይሆን ድንገት ብቻ ስምሽ አፌ ላይ ድቅን ቢልብኝ ነው!)
እናማ... ብዙ “ኸረ እባካችሁ ሰው ምን ይለናል በሉ!” የሚያሰኙ ነገሮች መአት ናቸው፡፡
ደህን ሰንበቱልኝማ!

Read 1347 times