Tuesday, 29 June 2021 00:00

ከአፍሪካ ህዝብ የተሟላ የኮሮና ክትባት የወሰደው 0.85% ብቻ ነው

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በአፍሪካ የመጀመሪያው የኮሮና ክትባት በደቡብ አፍሪካ ሊመረት ነው

   ከአፍሪካ አጠቃላይ ህዝብ እስካሁን ድረስ የኮሮና ክትባት የተከተበው 0.85 በመቶ ያህሉ ብቻ መሆኑን የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል ከሰሞኑ ባወጣው መረጃ ያስታወቀ ሲሆን ኦልአፍሪካን ኒውስ በበኩሉ፤ በአፍሪካ የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ ክትባት በደቡብ አፍሪካ ሊመረት እንደሆነ ዘግቧል፡፡
በአፍሪካ እስካለፈው ማክሰኞ ድረስ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን ሙሉ ለሙሉ የተከተቡት 10.2 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ወይም ከአህጉሪቱ አጠቃላይ ህዝብ 0.85 በመቶው ብቻ መሆኑን ያስታወቀው ማዕከሉ፣ በአለማቀፍ ደረጃ ከተመረተው የኮሮና ቫይረስ ክትባት አፍሪካ ያገኘችው ከ2 በመቶ በታች መሆኑንም በሳምንቱ መጀመሪያ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የአለም የጤና ድርጅት በበከሉ፤ በሶስተኛው ዙር የኮሮና ቫይረስ ማዕበል ክፉኛ እየተመታች በምትገኘው አፍሪካ የክትባት እጥረት አንገብጋቢ ደረጃ ላይ መድረሱንና ኡጋንዳና ዚምባቡዌን ጨምሮ ሰባት የአፍሪካ አገራት ክትባቶቻቸውን ተጠቅመው መጨረሳቸውን ያስታወቀ ሲሆን አልአይን በበኩሉ፤ በአለም ዙሪያ የሚገኙ 40 ያህል አገራት የመጀመሪያውን ዙር የኮሮና ቫይረስ ክትባቶች ለወሰዱ ዜጎቻቸው ሁለተኛውን ዙር ለመስጠት የክትባት እጥረት እንዳጋጠማቸው መነገሩን ዘግቧል፡፡
ዴልታ የተባለው አደገኛ የቫይረሱ ዝርያ ወደ 14 አገራት በተሰራጨባት አፍሪካ፣ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር ባለፈው ሰኞ ከ5.2 ሚሊዮን ማለፉንና የሟቾች ቁጥር ደግሞ ወደ 138 ሺህ መጠጋቱን የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል ባወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡
በሌላ የኮሮና ቫይረስ ዜና ደግሞ የአለም የጤና ድርጅት በአፍሪካ የመጀመሪያውን የኮሮና ቫይረስ እስከ አንድ አመት ጊዜ ውስጥ በደቡብ አፍሪካ ማምረት ለመጀመር ከአገሪቱ መንግስት ጋር እየተነጋገረ እንደሚገኝ የዘገበው ኦልአፍሪካን ኒውስ በበኩሉ፣ ሜሴንጀር አርኤንኤ በተባለ ቴክኖሎጂ ክትባት ለማምረት የተጀመረው ጥረት በከፍተኛ የክትባት እጥረት በርካታ ዜጎቻቸውን እያጡ ለሚገኙ የአፍሪካ አገራት ተስፋ ሰጪ ነው መባሉን አመልክቷል፡፡
ክትባቱ በአለም የጤና ድርጅት የበላይ አስተባባሪነት፣ ባዮቫክ በተባለ ኩባንያ ባለቤትነትና አፍሪጂን በተባለ ኩባንያ አምራችነት መመረት ይጀምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆመው ዘገባው፣ አፍሪካውያን ዩኒቨርሲቲዎችና የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያደርጉ መነገሩንም ገልጧል፡፡

Read 1990 times