Print this page
Wednesday, 30 June 2021 00:00

አማዞን የአለማችን ቁጥር አንድ ባለከፍተኛ ዋጋ የንግድ ምልክት ሆነ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

አሽጋባት ከአለማችን ከተሞች ለመጤዎች እጅግ ውዷ ተብላለች
የአሜሪካዊው ቢሊየነር ጄፍ ቤዞስ ኩባንያ አማዞን በአለማችን ኩባንያዎች የአመቱ የንግድ ምልክት ዋጋ ደረጃ በአንደኛነት የተቀመጠ ሲሆን፣ የኩባንያው የንግድ ምልክት ዋጋ 684 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ሰሞኑን የወጣ አለማቀፍ ሪፖርት አመልክቷል፡፡  
ካንታር ብራንድዝ የተባለው ተቋም ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው አመታዊ የ100 ምርጥ የአለማችን ኩባንያዎች የንግድ ምልክት ዋጋ ደረጃ ሪፖርት እንዳለው፤ የ100ዎቹ ኩባንያዎች ድምር ዋጋ 7.1 ትሪሊዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን የአማዞን የንግድ ምልክት ዋጋ ባለፈው አመት ከነበረበት የ64 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
ታዋቂው የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያ አፕል በ612 ቢሊዮን ዶላር የሁለተኛነት ደረጃን ሲይዝ፣ ጎግል በ458 ቢሊዮን ዶላር፣  ማይክሮሶፍት በ410 ቢሊዮን ዶላር፣ ቴንሰንት በ240 ቢሊዮን ዶላር፣ ፌስቡክ በ226.7 ቢሊዮን ዶላር፣ አሊባባ በ196.9 ቢሊዮን ዶላር፣ ቪዛ በ191.2 ቢሊዮን ዶላር፣ ማክዶናልድ በ154.9 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም ማስተርካርድ በ112.8 ቢሊዮን ዶላር እንደ ቅደም ተከተላቸው እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
የኤሌክትሪክ መኪኖችን በማምረት ዘርፍ የተሰማራው የአሜሪካው ኩባንያ ቴስላ ካለፈው አመት ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ያሳየ ቀዳሚው ኩባንያ ሲሆን ካምናው የ275 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 42.6 ቢሊዮን ዶላር የደረሰው ኩባንያው ከአለማችን መኪና አምራቾች በአንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
ከፍተኛ የንግድ ምልክት ዋጋ ካላቸው የአለማችን ምርጥ 100 ኩባንያዎች መካከል 74 በመቶው የአሜሪካ ኩባንያዎች ሲሆኑ፣  14 በመቶው የቻይና፣ 8 በመቶው ደግሞ የአውሮፓ ኩባንያዎች መሆናቸውን ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡ በሌላ አለማቀፍ ዜና ደግሞ፣ የቱርኬሚኒስታኗ ከተማ አሽጋባት ከሌሎች አገራት ለመጡ ነዋሪዎች  እጅግ ውድ የሆነች ቀዳሚዋ የአለማችን አገር መሆኗንና በአንጻሩ የካይሪጊስታን መዲና ቤሽኬክ እጅግ ርካሽዋ ከተማ መሆኗን ሜርሲየር የተባለው ተቋም ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው አለማቀፍ ጥናት ሪፖርት አስታውቋል፡፡
በአለም ዙሪያ የሚገኙ 209 ከተሞችን መኖሪያ ቤት፣ ትራንስፖርትና ምግብን ጨምሮ የ200 ሸቀጦችንና አገልግሎቶችን ዋጋ በማጥናት የፈረንጆች አመት 2021 ሪፖርቱን ባለፈው ረቡዕ ይፋ ያደረገው ተቋሙ፣ ከሌሎች አገራት ለመጡ ሰዎች እጅግ ውድ ናቸው ብሎ ከሁለተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ የሰጣቸው የአለማችን ከተሞች ሆንግ ኮንግ፣ ቤሩት፣ ቶክዮ፣ ዙሪክ፣ ሻንጋይ፣ ሲንጋፖር፣ ጄኔቫ፣ ቤጂንግ፣ እና በርን ናቸው፡፡
የካይሪጊስታን መዲና ቤሽኬክ በአንጻሩ በአመቱ ለውጭ አገራት ዜጎች እጅግ ርካሽ መሆኗ የተነገረላት ቀዳሚዋ የአለማችን ከተማ ስትሆን፣ ሉሳካ (ዛምቢያ)፣ ቲብሊሲ (ጂኦርጂያ)፣ ቱኒዝ (ቱኒዚያ)፣ ብራዚሊያ (ብራዚል)፣ ዊንድሆክ (ናሚቢያ)፣ ታሽኬንት (ኡስቤኪስታን)፣ ጋቦሮኔ (ቦትስዋና)፣ ካራቺ (ፓኪስታን) እና ባንጁል (ጋምቢያ) እንደ ቅደም ተከተላቸው ከሁለተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
ከ10ሩ እጅግ ውድ የአለማችን ከተሞች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የእስያ ከተሞች መሆናቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ከአሜሪካ ከተሞች መካከል ለመጤዎች እጅግ ውዷ ኒው ዮርክ ናት ብሏል፡፡

Read 6475 times
Administrator

Latest from Administrator