Sunday, 27 June 2021 16:48

16ኛው የአውሮፓ ዋንጫ በጥሎ ማለፍ ይቀጥላል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ቤልጅየም፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ፖርቱጋልና ስፔን ለዋንጫው ተጠብቀዋል
በምድብ ፉክክሩ 36 ጨዋታዎች ከ648,910 በላይ  ተመልካቾች ስታድዬም ገብተዋል


ዩሮ 2020 በጥሎ ማለፍ ምዕራፍ የሚቀጥል ሲሆን  ዛሬ በአምስተርዳም ዌልስ ከዴንማርክ እና በለንደን ደግሞ ጣሊያን ከኦስትሪያ፤ ነገ በቡዳፔስት ሆላንድ ከቼክ ሪፖብሊክ እና በሲቪያ ቤልጅዬም ከፖርቱጋል፤ ሰኞ  በኮፕንሃገን ክሮሽያ ከስፔን በቡካሬሰት ፈረንሳይ ከስውዘርላንድ፤ እንዲሁም ማክሰኞ በለንደን እንግሊዝ ከጀርመንና እና በግላስጎው ስዊድን ከዩክሬን ይገናኛሉ፡፡
የአውሮፓ ዋንጫው ከመጀመሩ በፊት ቤልጅየም፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ፖርቱጋልና ስፔን ዋንጫውን እንደሚያሸንፉ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ቤታፌር የተባለው የስፖርት ውርርድ ኩባንያ በሰራው ትንበያ ዋንጫውን ለፈረንሳይ የሰጠ ሲሆን በፍፃሜው  ጀርመንን 3ለ2 እንደምታሸንፍም ጠቅሷል፡፡ ግሬስ ኖት የምድብ ጨዋታዎች ከተጠናቀቁ በኋላ ይፋ ባደረገው ትንበያ ቤልጅዬም ዋንጫውን ለማሸነፍ 14 በመቶ ግምት በማግኘት ትመራለች፡፡ ፈረንሳይ 13፤ ጣሊያን 12፤ እንግሊዝ 11፤ ሆላንድ 8፤ ፖርቱጋል 7፤ ጀርመን 6፤ እንዲሁም ስፔን 6 በመቶ የማሸነፍ እድል ተሰጥቷቸዋል። ዘ አናሊስስ በሰራው ትንታኔ ደግሞ 20.5 በመቶ ዋንጫውን የማሸነፍ እድል የሰጠው ለፈረንሳይ ነው፡፡ ቤልጅዬም 15.7፤ ስፔን 11.3፤ ጀርመን 9.8፤ ፖርቱጋል  9.6 እንዲሁም ጣሊያን 7.6 በመቶ የሻምፒዮናነት ግምት አግኝተዋል፡፡
ባለፉት 15 የአውሮፓ ዋንጫዎች እያንዳንዳቸው ለ3 ጊዜያት ሻምፒዮን በመሆን የሚመሩት ጀርመንና ስፔን ናቸው። ፈረንሳይ ሁለት ጊዜ ሻምፒዮን በመሆን በሁለተኛ ደረጃ ስትከተል፤ ሆላንድ፣ ግሪክ፣ ጣሊያን፣ ዴንማርክና ፖርቱጋል እኩል አንዴ ዋንጫውን ያሸነፉ ናቸው፡፡
በCOVID-19 ወረርሽኝ በተፈጠረው እገዳ ምክንያት የውድድር አስተናጋጅ ከተሞች በስታድዬሞቻቸው በሙሉ አቅማቸው መሥራት አልቻሉም፡፡ UEFA እያንዳንዱ አስተናጋጅ ከአካባቢያቸው/ ከብሔራዊ መንግሥታቸው እና ከጤና ባለሥልጣኖቻቸው ጋር በመሆን የተመልካች ዕቅድን እንዲያዘጋጁ ከጠየቀ በኋላ ዩሮ 2020 ከፍተኛ ተመልካች ሊያስመዘግብ የበቃ የስፖርት ውድድር ሆኗል፡፡  የውድድሩ አስተናጋጅ ከተሞች በየስታድዬሞቻቸው ተመልካቾችን ለማስተናገድ ከ 25% እስከ 100% የሚደርስ አቅማቸውን ተጠቅመዋል፡፡አንዳንድ ከተሞች በአውሮፓ የእግር ኳስ ማህበር ከተሰጣቸው ፈቃድ  በላይ መጠቀማቸውን የዓለም ጤና ድርጅት ያወገዘው ቢሆንም ዩሮ 2020 ከጥሎ ማለፉ በኋላም በስታድዬም ሙሉ ድምቀት ኖሮት የሚቀጥል ይመስላል፡፡
ከጥሎ ማለፉ  በፊት በተደረጉት በምድብ ማጣርያ 36 ጨዋታዎች ላይ  በድምሩ ከ648,910 በላይ  ተመልካቾች ስታድዬም መግባት ችለዋል፡፡ በእያንዳንዱ ጨዋታ የስታድዬም ተመልካቾች ብዛት በአማካይ 18,025 ሆኖ ሲመዘገብ፤ ፈረንሳይ ከሃንጋሪ በቡዳፔስት ያደረጉት በ55,998 ከፍተኛ ተመልካች የታደመው ጨዋታ እንዲሁም ክሮሽያ ከቼክ ሪፖብሊክ በ5,607  ዝቅተኛ የተመልካች ብዛት ያስመዘገቡ ጨዋታዎች ሆነዋል፡፡
በምድብ ፉክክሩ ላይ በተደረጉት 36 ጨዋታዎች 94 ጎሎች የተመዘገቡ ሲሆን በኮከብ ግብ አግቢነት የሚመራው በ5 ጎሎች ክርስትያኖ ሮናልዶ ነው፡፡ በአውሮፓ ዋንጫውም የተለያዩ አዳዲስ ክብረወሰኖችን እያስመዘገበ ቀጥሏል። ትልቁ ክብረወሰን በፖርቱጋል ብሄራዊ ቡድን ማልያ ያስቆጠረው የጎል ብዛት 109 መድረሱ ሲሆን፤ ይህም በዓለም እግር ኳስ ታሪክ በከፍተኛ ግብ አግቢነት በ109 ጎሎች ክብረወሰን ከያዘው ኢራናዊው አሊ ደዪስ ጋር አስተካክሎታል፡፡ በ5 የአውሮፓ ዋንጫ ውድድሮች ላይ ሀገሩን ወክሎ በመሳተፍና ጎሎችን ከመረብ ያሳረፈ የመጀመሪያው ብቸኛው ተጫዋች መሆንም ችሏል፡፡ ጥሎ ማለፉ ከመጀመሩ በፊት በአውሮፓ ዋንጫው የያዛቸው ሌሎች ሪከርዶች በ11 ጎሎች የምንግዜም ከፍተኛው ግብ አግቢ፤ ብዙ የአውሮፓ ዋንጫ ጨዋታዎች በመሰለፍ በ24 ግጥሚያዎች 2063 ደቂቃዎችን በመጫወት ናቸው፡፡

Read 957 times