Saturday, 01 September 2012 11:38

ትዝታ ድክመቴ ነህ

Written by  ኪሩቤል ሳሙኤል
Rate this item
(3 votes)

አንዳንድ ፀሎቶች አሉ፡፡ የሚደማሙ፣ ለራሳቸው ነፍስ ዘርተው ራሳቸውን የሚገሉ፣ ለጥ ያለ ሜዳ ላይ እንደልብ መራወጥና መድረስ እየቻሉ የተራራው ግዝፈት ላይ መሆናቸውን የሚወጥሩ፡፡ ፀሎቶቹ በሙሉ የሚፀልዩት ባልደረሱ እየተባሉ ነው፡፡ መመኘትን እየቀረፁ ዝም ብለው ስድነትን የሚኖሩ፡፡ የሚቀርቡ ሆነው ተፈጥረው የሚርቁ፡፡ የትም ሳይሄዱ የማንንም ጥጊያ የማያስተናግዱ…የልብ ምጦች የሆኑ…አንዳንድ ፀሎቶች አሉ፡፡ እነዛን ፀሎቶች የሰማኋቸው ፀሐፊ ስለሆንኩ ብቻ ነው፡፡ መቀማትን በለመደው ኪነቴ ካየር ውስጥ ጠልፌ በወረቀት ለማስፈር የተሯሯጥኩትም ፀሐፊ ስለሆንኩ ብቻ ነው፡፡ ሂደቶች ለኔ ተፈጥረውልኛል፡፡ ሂደቶቹን እንደሰረገላ እየገረፍኳቸው በጽንፉ ውስጥ ማብቂያውን አመቻችቼ በሁኔታዎች አሳርፋቸዋለሁ፡፡ ይህን ማድረግ የቻልኩት ፀሐፊ ስለሆንኩ ብቻ ነው፡፡

ናትናኤል ተከራይቷት በተከራየችበት ቤቱ ውስጥ የሚያፈሰው የዘመን እንባውን ከትራሱ ላይ እያረጠበ እንዳይበሰብስበት የበፊት ፍቅሩን ያደርቃል፡፡ ማህሌት ጥላው ከሄደች ሁለት ሳምንት አልፏታል፡፡ ሁለቱ ሳምንታት በጊዜ እድሜ ውስጥ እንጂ እንደ ናትናኤል አቆጣጠርማ ማህሌት የሄደችው አጠገቡ ተቀምጣ በሀይለኛ ጡጫ የተጠለዘባትን ጉንጯን እያሻሸች ናትናኤልን በምታማርርበት ወቅት ላይ ነበር፡፡ ያኔ ነበር የሄደችው…ከማታዎቿ ጋር ሆና ናቲን እየናፈቀች ስትጠላው…እየወደደችው ከህሊናዋ እየተገፈፈ የሚሄደውን ትልቅ ፍቅር ስታደምጠው…እየመታት እንዲጋግማት ስትፀልይ…ያኔ …ያኔ ነበር የሄደችው፡፡

ዛሬ ላይ ናትናኤል ከቤቱ ተቀምጦ ማህሌት የቱጋ እየጠበቀችው እንደሆነ ያስባል፡፡ የፈለገውን ርቀት እየጋለበ ከፍጥነቱ ውስጥ ያለችውን ከነመዐዛዋ ያስባታል፡፡ ትልቁ ስህተቱ ግን ናቲ ማህሌትን ቤቱ ውስጥ ተቀምጦ ሌላ ቤት ያለችውን ውዱን መፈለጉ ላይ ነው፡፡ የትም ቢመላለስ ማህሌት ቤቱ ውስጥ እንደሌለች ያውቃል፡፡ ግን ቅርቡ ብትመስለው ነው፡፡ መጐዳት የሚጀምረው ከልቡ ስራስር ውስጥ ያን የሚያደርቅ ፈገግታዋን ይዛ እየኖረች መሆኑ ቢገባው ማታ ላይ ጋደም ብሎ ልቡን እያደመጠ የሆኑ መፍዘዞች ይፈዛል፡፡ ህሊናው ውስጥ ታዛዋን ጠልሳ ሁሌ ንጋት ላይ የምታበራ ልዕልት ተሸክሞ የትም መሄድ እንደማያስፈልገው ቢገባው ከገዛ ጓደኞቹ ጋር ሆኖ በዛች ልዕልት መታመሙን ቢወደው ነው፤ ማህሌት ቅርብ ናት፣ ትመጣለች እያለ ሊፈልጋት ከተቀመጠበት የማይነሳው፡፡

ማህሌት ግን የለችም፡፡ ሌላ ምዕራፍ ገለጣ ላይ ናት፡፡ ያሸነፋትንና ልጅነቷን የሚፈታተናትን የፍቅር ግዝፈት ላይ እየፎከረችበት ነበር…” እስከመቼ ልሸነፍልህ” እያለችው፡፡

ሲሳይ ጭልም ካለው መጠጥ ቤት ውስጥ ሆኖ የቀን ጀርባውን ይራገማል፡፡ ለምን እንደዚህ አይነት ሆንኩኝ እያለ፡፡ ያደገበት ባህሪውን እስኪዝል ድረስ ይሰድበዋል፡፡ ደረቅ ነኝ ይላል፡፡ ለራሱ ክብር እየሰጠው መሆኑ ነበር፡፡ ትርሲትን እየናፈቀ ነበር የሚጠጣው፡፡ እነዛን ቀናት እያስታወሰ…

እነዛ ቀናት እንደ አንዲት ክንፏ እንደተሸነፈባት ወፍ ሆኖ ከእግሯ ስር የተንደፋደፈባቸው ቀናት ነበሩ…ይወዳቸዋል፡፡ እነዛ ቀናት ውስጥ ህጐች ተጥሰዋል…ወንድ ልጅነት ውስጥ ያለው የልመና ውቅያኖስ ከነሙላቱ ለአንዲት የልቡ ላይ ንግስት ያፈሰሰባቸው ቀናት ናቸው፡፡ በየቀኑ ከምትሰራበት መስሪያ ቤት እየሄደ…ከመንገድ ቆማ ታክሲ ስትጠብቅ…ሰፈሯ ውስጥ…በሯን በቁልፍ ከፍታ ልትገባ ስትል በሯ ላይ ብቻ…ማታ ካልጋው ጋደም ብሎ ድርቅ እንዳለ…ህልሙን እየተለማመጠ (የጠፋውን ጠረኗ አሽትተኝ እያለው…) እየተኛ ይለምናት ነበር፡፡

ትርሲት ግን ልቧ በልመናው ብዛት ደንድኗል፡፡ የሴት ልጅ ነፍስ እነዛ የሚንቀሳቀሱትን የዛፍ ቅጠሎችን ይመስላል፡፡ ሀይለኛ ዶፍ ዝናብ በላያቸው ላይ ሲበረታባቸው አጐንብሰው ይሰሙታል…በስተመጨረሻ ግን ዝናቡን ራሱን አኩርፈውት እንዳጐነበሱ ዳግመኛ ላያዩት ይጠሉታል፡፡ እነዛ ነፍሶች ብዛትን ይፈራሉ፡፡ የተፈጠሩበት አላማ ትንሽ ተቀብለው ብዙ መስጠትን ብቻ እንዲለማመዱ ነው፡፡ ብዛት ግን ጥጋት አሳጥቶ ወደ ሌላ የህይወት ክፍተት ውስጥ ይሰነቅራቸዋል፡፡ የሚራመዱበት ላይ ማንም እንዲረግጥ ባይፈልጉም በሌላው ዳና ላይ መሰልጠን ልምዳቸው ነው፡፡ ሄደው የሚቆሙበት ቦታ ቢያስፈራቸው ነው መሰል ብቻቸውን መሰንበት ያስፈራቸዋል፡፡ ፍርሃት ይወስድና ከአንድ ጧሪ ነፍስ ጋር ያጠጋጋቸዋል፡፡ እንዳይበዛባቸው አድርገው እየተቀበሉ፣ ብዙ እየሰጡ ብዙ ይኖራሉ፡፡

ትርሲት ጥፋት ያጠፋች ያልመሰላት የተፈጥሮዋን ዜማ በትክክል እንዳዳመጠች ስታውቅ ነው፡፡ ሲሳይ ደግሞ ህጐችን ሁሉ ያስጣሰውን፤ አለሁልህ እኔን ከያዝክ የትም ታሸንፋለህ ያለውን የይቅርታን መንፈስ ስለተሸከመ ነው፡፡ የትም መራመዱን ሳይፈራ የሚለምደው፡፡ እስኪገባው ቅርቡ ማንም የለም፡፡ መቅረብ ይፈልጋል፡፡ ወደ ትርሲት፡፡

በሁለቱም ውስጥ ያለው መጠጋጋት ግን ቅኔ ቢያጣ፣ ብልጠት ቢያጣ፣ መተርጐምነት ቢያጣ፣ ወደ መለዘዝነቱ ነጉዷል፡፡ የሁለት ፍቅረኛሞች ፍቅር እኩል ሆኖ አያውቅም፡፡ ይህ ያልገባው ሲሳይ መስተካከል አለብን ብሎ ሰርክ ቢጠጋጋት ነው ትርሲት እንዳትገኝ ሆና ከውስጡ የጠፋችበት፡፡

ናትናኤል ለብርታት ከሆነኝ ብሎ ከዚህ ቀደም ከፍቅሩ ማህደር ላይ ካሰፈራቸው ሴቶች አንዲቷንስ ለምኖና አሳምኖ የታረቀበት ጊዜውን ቢያስታውስ ማንንም ሊያስታውስ አልቻለም፡፡ ናቲ ሴት ተለማምጦ አያውቅም፡፡ እንደፈለገ በአንደበቱ ቢዝል ግደፍ ብሎ ተቆጥቶት እሱ የማያውቀውን እሱነቱን ሰጥቶት አያውቅም፡፡ ይህ ሁሉ አዲስ ነገር ነው ለሱ፡፡ መለማመጥን መልመድ ሞት ውስጥ ያለን ጨካኝ ድምጽ እንደመጥራት ነው ለሱ፡፡ ረዥም ወራቶችን ካጠገቡ ርቃ ሌላ ህይወትን…እሱ የማያውቀውን የኑሮ ሂደት በሴትነቷ አየገፋች ያለችውን ማህሌት ሳያያትና ሳይደውልላት ቆይቶ ዛሬ ላይ ስቀዛው በዝቶበት ውሳኔ ላይ ተነጣጥሎ የጠፋችውን ሊመለከት ወደደ፡፡

መጀመሪያ በማሰቡ ውስጥ ሆኖ ያሳለፋቸውን የፍቅር ረቂቅነቶችን አሰላሰለ፡፡ የትዝታ ሃያል ደመና ውስጥ አገኛት፡፡ ይህች ሴት እውነትም እሱነቱን ተሸክማለት ሄዶት የማያውቀውን አስረግጣዋለች፡፡ አስሬ ሲሞት ትዝ አለው…አስሬ ግን ታስነሳዋለች…ማህሌት ትንሳኤው ነበረች፡፡ የመጨረሻው የፍቅር ፀበል አሁንም አልደረቀም፡፡ ልክ ሲያስታውሳት ነው ፀበሉ የሚታወሰው…ከበስተውስጡ ያለውን የወንድነትን ወግ የሚያባርርለት፡፡ አንዳንዴ ራሱን እየሰረቀና እየሸወደ ይቅር ሲላት በቀን ህልሙ ያያል፡፡ እሷም “እሺ ይቅር ብዬሃለሁ…የመቱኝ እጆችህን…የሰደቡኝ ቃላቶችህን…የተፀየፈኝ ፊትህን…የተቆጡኝ አይኖችህን…ጥለውኝ የሄዱ እግሮችህን…የማይተው ህልምህን ይቅር ብያችኋለሁ” ስትለው ይታየዋል፡፡ ይህ ሲሰማው ናቲ የሚፍረውን ያህል እያፈረ ተመልሶ ወደ ድሮነቱ፣ ወደ በፊቱ ወንድነቱ ይመለሳል፡፡

ዛሬ ግን ክፉ ህመም ተጠናውቶት እራሱን እየተቆጣ ነው፡፡ ልክ እሱነቱ ቁጣውን ሲሰማ ከተቀመጠበት ተነስቶ ይሄዳል፡፡ ረዥም ጉዞ ነበር…ማህሌትን በምን ይቅርታ ጠይቄያት መልሼ ወደ ቤቷ ልመልሳት የሚለው የተንዛዛ ውትወታው፡፡ በመጨረሻ ግን ለመነሳት ወሰነ፡፡ ሊመልሳት ሊወስን ከሆነ ከማንነቱ ጋር ታርቆ በደስታ ለብቻው ተፍለቀለቀ፡፡ መልሶ እንደሚያገኛት ሲያስብ…የማይታቀውን ይዞባት ሲመጣ ደንግጣ ስትጠጋውና ይዟት በፊት የነበሩበት ሲከትሙ ሲያስብ…ደግማ ስቃ ስታስቀው እያሰበ ከተቀመጠበት ተነስቶ መገስገሱን መረጠ፡፡

ከመንገድ ላይ እያለ ይናፍቃት ነበር፡፡ ሁሉም ነገር ያለው ልቡ ላይ ነው፤ ናፍቆቱም፣ ፍቅሩም፣ ትንሳኤውም፣ መደሰቱም…ሁሉም ነገር ያለው ልቡ ላይ ነው…እነዚያን ሃያል ስሜቶች ሲያስብ ልቡ በሀይል ይመታል፡፡ ከሷ ጋር ሳይደርስ የሚሞት እየመሰለው ለአፍታ ሰጋ…፡፡

ሲሳይ ጠዋት ላይ ሃንጐበሩ አናውዞት እየተነሳ የነፍሱን ከምታደምጥለት፣ ከሰፈሩ ራቅ ብላ ከበቀለች ዛፍ ሥር ሄዶ ተቀመጠ፡፡ የትም ቢሆን የሚጠብቃት ትርሲትን ሊያስባት ሞከረ፡፡ ከናፍቆቷ ካበደረችው እንጂ መናፈቅን የሚችለው አይመስለውም፡፡ ስንቴ ትራቀው?

ከዛች ዛፍ ስር እንደተቀመጠ ነፍሱ ስትቀደድ የሚሰማውን ያህል ሃያል የሆነ ድምጽ ከጀርባው ነዘረው፡፡

“ለምንድን ነው እስካሁን ያልመጣኸው?”

ትርሲት ነበረች…አይ ትርሲት…ትርሲት ነበረች፡፡

ሲሳይ ከመቅጽበት ከተቀመጠበት ተነስቶ የሚናገረውን ማሰብ ጀመረ፡፡ ግን አልተናገረም፡፡

“ለምንድን ነው እስካሁን ያልመጣኸው? መልስልኝ እንጂ? የምን ድፍረት ነው? ለዚህ ነው እስካሁን ስትፍቸረቸር የቆየኸው? ልመናህ ምንም ያህል ቢደብረኝ…ቢያንገሸግሸኝም የምሰጥህን እያበዛህ እንጂ ሌላ ምን እየሰራህ መሰለህ፡፡ ሰነፍ ነህ ሲሳይ፡፡”

ሲሳይ ትርሲት ደግማ ደጋግማ ልታምር ስትል አይቶ ደግሞ ደጋግሞ ወደዳት፡፡ በሀይል እየተራመደ ሄዶ ታዝቦት የሚንፈቀፈቀው ከንፈሯን በከንፈሩ ታረቀው፡፡ ለረዥም ደቂቃ በሀይል ተሳሳሙ፤ ሲሳሳሙ የከንፈሮቻቸው ልፊያ ቃላቶች ነበሩ፤ በነዛ ቃላቶች ታረቁ፡፡

ለአፍታ ሲሳይ ከመሳሳሙ ራሱን ትንፋሽ ሰጥቶት ቀና ብሎ ተመለከታት፣ እያለቀሰች ነበር፡፡ እንደእንባዎቿ የአይኖቿ ጥገኛ መሆኑን ወዲያው አወቀ፤ መናገር እንዳለበት ገባው…

“ህይወትና ሞት መሀል ሆኜ የምጠብቀው ክብር አልነበረም…በየመጠጥ ቤቶች እየገባሁ በብዙ የድራፍት አለንጋዎች ስግል የነበረው ለመርሳት ፈልጌ አልነበረም…ልቀርብሽ ባስብ ነው፣ ከራሴ ጋር ተቃርኜ የምታረቀው አንድ ቢኖር እሱም አንቺ ስለሆንሽ ነው፡፡ ከራሴ ሳልገኝ እነዚያን ወራቶች የጠፋሁት ስጠብቅሽ ነበር እኮ ትርሲት…በህልሜ…ስተነፍስ ብቻ ነበር የማስታውስሽ …ልቤ ሲመታ ብቻ…የአንቺ ፍቅር መኖሬን ተጣብቶ አንችን አድርጐኛል…ልሁንልሽ ትርሲቴ…ልሁንልሽ….”

እነዛ የአይኗ ላይ ቤተኛ እንባዎች ቁልቁል ዜማቸውን እያሰሙ መውረድን መረጡ፡፡ እንባዎቿ ሲስቁ በሲሳይ ነፍስ ውስጥ እንደ እረኛ ያገለግለው የነበረው የይቅር ባይነት መንፈስ አሸነፈ፡፡

ማህሌት ከሰል ነገር ይዛ ከመንገድ ስትሄድ ናቲ ከጀርባዋ ያያታል፡፡ የሆነ የሚያሯሩጠው ነገር አጋጠመው…በአፉ ተሯሯጠ፣ ጠራት…

“ማህሌት” ማህሌት ዞራ የተጣራውን በአይኖቿ አረጋገጠች፡፡

ያ ናትናኤል የተባለው የበፊት ፍቅረኛዋ ነበር፡፡ ልቧ አካባቢ የተቃጠለ ነገር ተሰማት፡፡ ወደ ሞት እየተሳበች መሰላት፡፡ ጭራሽ ካይኑ ላይ ፈገግታውን ስታየው…መናፈቁ ሲጋለጥበት ስታየው…ናትናኤል መሆኑን ስታይ ሩጪ እና አምልጪ የሚል የመንፈስ ንግሮሽ ውስጥ ከተመች፡፡ ቆማ ደርቃ ቀረች፡፡ ናቲ ፈገግታው ፊቱ ላይ እንደደረቀ ቀርቧት ቆመ፡፡ ማህሌት ፈራ ተባ እያለች የደመነፍሷን ተናገረች…

“ናቲ….ምን ልትሰራ መጣህ?”

ናቲ በአንዴው ፊቱ የአመድ ነፍስን ተሸከመ፡፡ ይህ ጥያቄ እንደማይመጥነው ያውቃል፡፡ ነፍስ እንድትዘራበት የተፈጠረችው ማህሌት ይህን ምስኪን ወንድ በጥያቄዋ ገደለችው፡፡ ዝም ብሎ አተኩሮ ተመለከታት፡፡ ይህንን አስተያየት ታውቀዋለች፡፡ ናቲ ሲናደድ ነው እንደዚህ የሚየያው…፡፡ ድንገት ፉጨት ነገር ከማህሌት ጀርባ ተሰማ፡፡ ማህሌት ዞራ ወደ ፉጨቱ ተመለከተች፤ ወደ ሶስት የሚጠጉ ወንዶች እጃቸውን ሲያውለበልቡላት ተመለከተች፡፡ ደንግጣ ከመቅጽበት ወደ ናቲ ዞረች፡፡ ናቲ ማመኑን ፈራው፤ ላትሄድ እንደሆነ ማመኑን ፈራው፡፡ በመደንገጥ ውስጥ ብቻ መቆየቱን ፈለገ፡፡ ማህሌት ግን የምታቆየው አይነት አይደለችም፡፡

“ናቲ መሄድ አለብኝ…”

ጥላው ልትሄድ ወደኋላዋ አፈገፈገች፡፡ ናቲ በቆመበት እያያት ከበስተውስጡ መሞት ጀመረ፡፡ የሞተ ነገር መቼስ አይንቀሳቀስ…

ማህሌት ጥላው ሄደች፡፡

ትዝታዎች ቢሰባሰቡ እስትንፋስ መሆን አይችሉም፡፡ ይህንን እኔ ፀሐፊው በመብቴ የተረጐምኩት የቀን ጀርባ ውስጥ ተደብቆ የሚፈነጭ ቅዠት ነው፡፡ ትዝታዎች ሸክም ናቸው እላለሁ፤ የሚተነብዩት ነገር የላቸውም…ተሩጦ ላይደረስባቸው፣ ዝገታቸው ላይለቅ…ትዝታዎች ሸክም ናቸው፡፡

 

 

 

Read 4298 times Last modified on Saturday, 01 September 2012 11:41