Sunday, 20 June 2021 00:00

በምርጫ ዋዜማ፣ “የጥሞና ጊዜ” ምን አመጣው?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

         -በጥሞና ካለፈልንም፣ “ተመስጌን” ነው፡፡ በፖለቲካ ጦስ ብዙ ሞትና መከራ፣በጥቂት ጊዜ አይተናል፡፡
         -አዳሜ፣የዘንድሮ ምርጫ፣በጣም ከባድ እንደሆነ፣ መዘዙም ለዓመታት ሊቀጥል እንደሚችል ትንሽ ገብቶታል፡፡ ትንሽም ተረጋግቷል፡፡
                
            የአራት ቀን ጥሞና! ሱባኤ ሊሆን ምን ቀረው? “ሱባኤ”፣ የሰባት ቀን ለማለት አይደል? ከምርጫ ቦርድ፣ የመጣው የ”ጥሞና” ጥሪ ግን፣ የ4 ቀን ነው - ከሐሙስ እስከ እሁድ። መቼም፣ “የመጣልን ጥሪ ወይስ የመጣብን ጥሪ?” የሚል ክርክር አንጀምርም።
“የጥሞና ስጦታ ነው ወይስ የጥሞና እዳ?” እያልን ብንወዛገብ፣ አለም ይታዘበናል። ማለቴ፣ የድንቅ  ክስተቶች መዝገብ ውስጥ እንዲፅፉልን ካልፈለግን በቀር!
ሲፅፉልን፣ ወይም ሲፅፉብን፣ “በጥሞና ጉዳይ ተበጣበጡ”፣ “በጥሞና ተራበሹ”፣ “የጥሞና ግርግር ተፈጠረ”፣… ምን አይነት ርዕስ ሊጠቀሙ እንደሚችሉ አስቡት። ለርዕስ የሚሆን “ምክረ ሃሳብ” ለማቅረብና ለመተባበር እንስማማለን?  የጥሞና ጉዳይ ካወዛገበን፣ የብጥብጥ ጉዳይ ያስማማን ይሆናል። ግን ከምር፣ ይሄ የጥሞና ነገር፣ ይመስጣልም፤ ይከነክናልም። በቅድሚያ፣….የጥሞና ስጦታ ወይስ ጥሞና እዳ ብለን እንዳንወዛገብ፣ በአሃዛዊ ስም እንጥራው። የአራት ቀን ጥሞና ስለሆነ፣ “ሩባኤ” እንበለው፡፡
 አሁን፣ጥያቄው ምንድነው? እስከዛሬ እንደለመድነው፣ የፖለቲካ ምርጫ፣ ተሟሙቆ ካልተፍለቀለቀ፤ ተጋግሞ ካልተንቀለቀለ፣ “ምርጫ” መስሎ አይታየንም። እንደ ኤርታሌ፣ አገሬው በምርጫ ትኩሳት ብቻ ሳይሆን፣ በምርጫ እቶን ሲንፈቀፈቅ ነው፤ ቅልጥ ያለ ድግስ ሆኖ በሞቅታ የሚታየን። አገር ካልተቀወጠ፣ ካልቀለጠ፣ ምኑ ምርጫ ሆነው? ከሞቅታ አልፎ ካልጦዘ፣ በጥሶ ካልፈነዳ፣ ቢያንስ ቢያንስ ካልገነፈለ፣ … ከንቱ ድካም፣ ፈዛዛ ደንዛዛ ድራማ ይሆንብናል- ለብዙዎቻችን። ነገሮች ተተራምሰው፣ብዙ ጥፋት እስኪዛመት ድረስ፣ ሆይ ሆይታ ሁካታ፣አደገኛ ሆነው አይታዩንም፡፡ ቀልድና ጨዋታ ይመስሉናል፡፡
ታዲያ፣ ከዚህ” ባህላችን” አንፃር፣ “የጥሞና ጥሪ” እንዴት ይታየናል? ባህልና ልማዳችንን አይቃረንም ወይ? የማያዋጣና የማያዛልቅ አጉል ባህል ነው፡፡ ግን ያው፤ “ሁሉም ባህል እኩል ነው፤ ሁሉም ባህል ክቡር ነው” የሚል ወገኛ የቅዥት ሃሳብ አለለን፡፡ ጥሞና፣ የግድ ካልሆነብን በቀር፣ለባህላችን አይጥምም፡፡
ከመነሻውም፣ የዘንድሮው የምርጫ ዘመቻ፣ ረጋ ደብዘዝ ቀዝቀዝ ያለ ነው። የኤርታሌ ምርጫ ሳይሆን፣ የሳይቤሪያ ምርጫ በሉት፡፡ ያን ያህል ቁጭ ብድግ የሚያሰኝ፣ የሚያቁነጠንጥ፣ የሚያስፈነጭ፣ የሚያስጨፍር፣ የሚያስፎክር ግለትና ጡዘት አልታየበትም።
 እርጋታ፣ ለአገር ለሰላም ጥሩ ሊሆን ይችላል። የብዙዎቻችን ፍላጎት ግን፣ … እንደ ዘንድሮ ከአይን ከጆሮ የማይገባ ቀዝቅቃዛ ምርጫ አልነበረም። በመጨረሻዋ ሳምንት፣ የምርጫ ዘመቻው ሞቅ ሞቅ ብሎ ነበር። በእርግጥ፣ የአብዛኞቹ ነዋሪዎች ስሜት፣ እምብዛም አልተነሳሳም። የፓርቲዎች የቅስቀሳ ጩኸት ግን፣ የማተኮስ የማቀጣጠል፣ የመፋጀት ስሜት ጀማምሮት ነበር። ምን ያደርጋል! ምርጫ ቦርድ መጣና፣ ቀዝቃዛ ውሃ ቸለሰበት- በአራት የጥሞና ቀናት።
ግን ለምን? ያው፣ የምርጫ የመጨረሻ ቀናት፣ ለምርጫ ቦርድ፣ እጅግ ፈታኝ፣ የጭንቅና የወከባ ቀናት ናቸው። በስራ ብዛት የተወጠረና ሃሳብ የገባው ወላጅ ወይም አስተማሪ፣ ምን እንደሚል አስቡት።
“አርፋችሁ አጥኑ። ፈተና ደርሷል። ጥሞና! ፀጥታ! በጥሞና አጥኑ!!”
አንድ ታሪክ አለ፡፡ ለምርጫ ትንብያ ስለሚጠቅም፣ በአጭሩ አንተርከው፡፡
ተማሪዎችና ልጆች፣ አርፈው ከተቀመጡ፣ ወላጅና አስተማሪ፣ አርፈው አስጨናቂ ስራ ላይ ማተኮር ይችላሉ። አንዱ አስተማሪ የፈጠረው ዘዴ፣ አስተማማኝ የጭካኔ ዘዴ ይመስላል። ከአንድ እስከ መቶ ድረስ ያሉ ቁጥሮችን ደምሩ አላቸው ተማሪዎቹን። ቀላል ይመስላል። ግን አይደለም።
“የጥሞና ጊዜ” ይሉሃል እንዲህ ነው። ተማሪዎች፤ የመደመር መሰላል ላይ በፀጥታ ሲንጠላጠሉ፣ አስተማሪያቸው፣ የራሱን ችግር ለማሰላሰልና ለመስራት በቂ ጊዜ ያገኛል። ምርጥ ዘዴ! የጥሞና ጊዜ! ደግነቱ ወይም “ክፋቱ”፣ አንድ ብልህ አስተዋይ ተማሪ፣ የራሱ ሌላ ዘዴ አገኘ።
በአጠቃላይ ሃምሳ ጊዜ 101 መሆኑ ነው። 5,050። ከዚህም በመነሳት፣ ትንሽ ጥረት በመጨመር አዲስ ቀመር ፈጥሯል- ብልሁ ተማሪ።
አንድ መቶ ተከታታይ ቁጥሮች… ይህንን ለሁለት ማካፈል። 50 ማለት ነው።
የመጀመሪያውና መጨረሻው ቁጥር መደመር። 101 ማለት ነው። ከዚያ ማባዛት ነው። 50 ሲባዛ በ101 ስንት ይሆናል?
5,00 5,00 ::
 የአስተዋዩ ታሪክ እንዲህ ተብሎ ተፅፏል፡፡
(በBrian Hayes)
A teacher … gave his class the tedious assignment of summing the first 100 integers. The teacher’s aim was to keep the kids quiet for half an hour, but one young pupil almost immediately produced an answer: The smart aleck was Carl Friedrich Gauss, who would go on to join the short list of greatest mathematicians ever.
እንዲህ ተከታታይ ቁጥሮችን ለመደመር የሚያገለግል ቀመር ለራሱ የፈጠረ ብልህ ተማሪ፣ የአለምን ታሪክ እየቀየረ እንደሆነ፣ በወቅቱ ላይገባው ይችላል። መነሻው ቀላል ቢመስልም፣  የተከታታይ ቁጥሮችን ጉዳይ፣ … ያልተማረ ሰው፣ ወደ ከፍተኛ የሂሳብ ደረጃ ማለፍ አይችልም፡፡ ወደ ከፍተኛ፣ የመረጃ ትንተናና የሳይንስ እርከን መሸጋገሪያ አያገኝም። አስተዋዮችና ብልሆች በምርምር እውቀትን እያገኙ፣ መፍትሄ ቀመር እየፈጠሩ ነው፤መሸጋገሪያ ድልድይ የሚገነቡልን። ስታትስቲክስ እና ካልኩለስ ምን ይውጣቸው ነበር? አብዛኛው የሳይንስ ትንተና፣ የምርጫ ትንቢያ፣ የቴክኖሎጂ ምርምር፣ ከባድ የጉልበት ስራ፣ ደካማ የግምት ስራ በሆነ ነበር።
የሆነ ሆኖ፣ አንዳንዴ፣ የጥሞና ጊዜ፣ ጥሩ ነው። ስራ የበዛበት ወላጅ ወይም አስተማሪ በሙሉ ትኩረት ለመስራት ጊዜ አገኛለሁ ብሎ፣ “ፀጥታ! ጥሞና!”
ብሎ ቢጮህ፣ ቢያስጠነቅቅ፣ አይፈረድበትም። ቢቸግረው ይሆናል። ሌሎቻችንስ?
ብልሁ ተማሪ እንዳደረገው፣ በየፊናችን የየራሳችን ቁም ነገር ላይ ማተኮር እንችላለን። ከፈለግን። ምርጫ ቦርድ፣ እንደ ተመኘው፣ የጥሞና ጊዜ አውጆብን፣ ስራው ከተቃናለት፣ … አንድ ቁም-ነገር ነው። ይሁንለታ።
በራሱ ስራ ላይ ተጠምዶ፣ ሌሎቻችን በየበኩላችን ብናውካካ፣ ብናወራ፣ ብንመካከር፣ ብንከራከር፣ ወይ ብንነታረክ፣ ምርጫ ቦርድ ምን ይጎድልበታል? በስራ ተጠምዶ፣ ለወሬና ለሁካታ ጊዜ አይኖረውም። ብዙ ወሬ፣ ብዙ ንትርክ፣ ሳይሰማ ያመልጠዋል። ከቤት እንዳትወጡ ተብለው የተከለከሉ ልጆች፣  ከግቢ ውጪ ጓደኞቻቸው እየተጫወቱ እየተጯጯሁ፣ … እንዴት እንደሚበግኑ አስቡት። እንኳን ጨዋታና ሆታ ይቅርና፣ ፀብና ዋይታ ብርቅ ሆኖ ይሰማቸዋል።
“አመለጠን” በሚል ስሜት ይንገበገባሉ፡፡ እናንተስ ብትሆኑ፣ወሬ ከሚያመልጣችሁ ይልቅ፣ ሰፈር መንደሩ ሁሉ፣ ወደየቤቱ ቢከተት፣ የጥሞና ሱባኤ ቢገባ አይሻልም?
 ሱባኤ ከታወጀ፣ እናንተ ስራ ላይ ብትሆኑም፣ ወሬ አመልጣችሁም። ታዲያ፣ ከማንም በላይ ፣ሰሞኑን በጣም ስራ የሚበዛበት ማን ነው? ምርጫ ቦርድ፡፡ የጥሞና አራት ቀናት (“ ሩባኤ”) ሰሞኑን ያወጀስ ማን ነው? የምርጫ ቦርድ ነው፡፡ እና ይሄ፣ የአጋጣሚ ጉዳይ ነው ትላላችሁ? ቦርዱ በስራ ብዛት ሲባትል፣ ብዙ ወሬና ውካታ እንዳያመልጠው፣ አስበ አይደለም? እሱ በሌለበት፣እኛ በሆታና በጭቅጭቅ አለማችንን እንዳንቀጭ፣ አስቦ አይደለም ልትሉ ነው?
ምርጫውም በእርጋታ፣ አገሩም በሰላም፣ ዜጎችም በጤና እንዲተርፉ እንዲሻገሩ በማሰብ ነው ልትሉ ነው? ይሁና፡፡ ከምርጫ አደጋ ለመትረፍ፣ የአደጋ ጊዜውን ለመሻገርና ለማምለጥ፣ … ሊሆን ይችላል። ግን ያለ ግርግር ያለ ረብሻ፣ ያለብጥብጥ፣ … ምርጫው ምኑ ምርጫ ይባላል?
ይልቅ በዚህ በጥሞና ጊዜ፣ ለየኛው ቦታ የትኛውን ፓርቲ፣ ለክልል ምክር ቤት የትኛዋን ፖለቲከኛ፣ ለፓርላማስ እከሌን ወይስ እከሊትን መምረጥ እንደሚገባ፣ መናገር ማውራት ያሰኛል።  የምርጫ ዘመቻ ለፓርቲዎችና ለፖለቲከኞች፣ ተከለከለ እንጂ፣ ሙያዊ ትንታኔና አልባሌ ወሬ አልተከለከለም። መብት ነው። ቢሆንም፣ ግድ የለም። ይቅር፡፡ ይሄኛውን ወይስ ያኛውን ፓርቲ፣ እገሌን ወይስ እገሊትን መምረጥ እንዳለብን፣ ለጊዜው ለዛሬ እናውራ። ወደፊት፣ ይደርሳል። ወዴት ይሄድብናል? ከምርጫው በኋላ፣ ጊዜ ሞልቷል። የአራት ቀን ሱባኤ መታገስ አይከብድም። እስቲ ምርጫ ቦርድ ደስ በለው።
ይልቅ፣ ማን እነማን፣ በየት እስከየት ድረስ እንደሚያሸንፉ ወይም እንደሚሸነፉ በአሃዝ፣ በመቶኛ፣ በቁጥር እንቅጩን ቁጭ ቁጭ እያደረግን ብንመለከት ይሻላል። ማለቴ ይሻል ነበር። የመረጃ ትንተና፣ ስታትስቲክስ፣ ቁጥርና አሃዝ፣ መደመርና ማባዛት ቅድም ጀማምረነዋል። ትንሽ ብንገፋበት፣ የምርጫውን ውጤት ከወዲሁ መተንበይ ያቅተናል?
ቁርጡን ከወዲሁ ማወቅ ይጠቅማል፡፡ ካልሆነም ዳር ዳርታው አዝማሚያው ገና ከዋዜማው መረዳት፣ ለሁሉም ይበጃል። በምርጫው ማግስት ላለመደናገጥ፣ ላለመደነቅ ይጠቅማል። ቀድሞ ያልታሰበና ያልተጠበቀ ድንገተኛ ቁጥር፣ ምን ያደርጋል?
 surprise,…በጣም የሚያምረው፣ በድርሰት ነው። በእውነት አለም ውስጥ፣ ያልታሰበ ድንገተኛ ቁጥር፣ ክውታና እልልታ፣ … surprise የሚሏቸው ነገሮች ሁሉ፣ የመረጃና የእውቀት እጥረት፣ የችሎታ እጦት፣ የቀመርና የስሌት ጉድለት ናቸው።
በነገራችን ላይ፣ ጥሞና ማለት፣…. ጽሞና፣ ብቻነት፣ ብቻ መሆን፣ ጸጥታ፣ እርጋታ፣ ማለት ነው ይላል የደስታ ተክለወልድ መዝገበ ቃላት።
የኪዳነወልድ የግዕዝ መዝገበ ቃላት በበኩሉ፣ “ጸመወ”፣ “ጾምዎ”፣ መጨመት፣ ፀጥ ዝም ማለት፣ አለመታወክ፣ ከማስተዋል ጋር ዝምተኛ ዳተኛ መሆን ማለት ነው ይላል። “ጽሙና”፣ ጭምትነት፣ ድካም፣ ጸጥታ፣ ትሕርምት፣ ጾም፣ ምናኔ፣ የገዳም ሥርዓት፣ ብችነት፣ …. በማለትም ይዘረዝራል።

Read 12746 times