Saturday, 01 September 2012 11:35

አነጋጋሪው ኢትዮጵያዊ እውቀት፣ ሀሳብና ተግባር

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(2 votes)

ዲያቆን ገረመው ሸዋዬ የተባሉ የቤተክርስቲያን መምህር ከአራት አመት በፊት በአንድ መድረክ ተጋብዘው በፅናት፣ በዓላማና በእምነት ዙሪያ ንግግር ሲያደርጉ “ኤልያስ በሰማይ አረገ” የሚለውን የመፅሐፍ ቅዱስ ቃል እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ኋላ ቀር አገራት የትምህርቱን ትርጉም ብቻ ይዘን ስንቀር፣ ሰለጠኑ የሚባሉት አገራት ግን ትምህርቱን ወደ ተግባር ለውጠው አውሮፕላን ሰርተው በሰማይ ላይ መብረር እንደሚቻል አሳዩ ብለው ነበር፡፡የዛሬ ሳምንት “የማዬት ፍሬ” በሚል ርእስ በእውቀቱ ስዩም በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ባስነበበው ፅሁፍ የዲያቆን ገረመው ሸዋዬን አባባል የሚያጠናክር ምሳሌ አቅርቧል፡፡

“አውሮፕላን የሰው ልጅ የመብረር ምኞት ያስገኘው የቴክኖሎጂ ፍሬ ነው፡፡ የጥንት ኢትዮጵያዊያን የመብረር ምኞታቸውን በስዕልና በተረት ተወጥተውታል፡፡ ባህላዊ ስዕላችንን ብታዩ በክንፍ የተሞሉ ሆነው ታገኙታላችሁ…

“አባቶቻችን (እናቶቻችንም) አስደናቂ ምናብ እንደነበራቸው አያጠራጥርም፡፡ የምናባቸውን ስዕል ወደ እውን ለመቀየር ግን ድፍረት የነበራቸው አይመስልም፡፡ ምናልባትም ትህትና ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ አድርጓቸው ይሆናል፡፡ በደመና ላይ የመጋለብ መብት ያላቸው መላዕክት እና እንደ ኤልያስ ያሉ መላእክት አከል ቅዱሳን ብቻ ናቸው ብለው የታቀቡ መሰለኝ፡፡”

ዳቪንቺ የበረራ መኪኖችን ንድፍ መስራት የቻለው “ኤልያስ በሰማይ አረገ” የሚለው ሃይማኖታዊ ትምህርት መሰረት አድርጐ ሊሆን እንደሚችል የሚያመለክተው የበእውቀቱ ስዩም ፅሁፍ፤ ይኸው ትምህርት መነሻ የሆናቸው የሚመስሉት ኢትዮጵያዊያን ያገኙትን እውቀት ዳቪንቺ የሞከረውን ያህል ወደ ተግባር ለመለወጥ ቢጥሩም ከዚያ በላይ እንዳይሄዱ ትህትና ሳይገታቸው አልቀረም ብሏል፡፡

ከዲያቆን ገረመው ሸዋዬ እና ከደራሲና ገጣሚ በእውቀቱ ስዩም ድምዳሜ ተቃራኒ የሆነ ሐሳብ የያዘ መፅሐፍ፤ በግንቦት ወር 2004 ዓ.ም ታትሞ ለአንባቢያን ቀርቧል፡፡ በ”አድሜሽ መፅሐፍት ንግድ ሥራ” ድርጅት ታትሞ የቀረበው መፅሐፍ “ምስጢረ ሰማያት” እና “ምስጢረ ኢትዮጵያ ፍልስፍና” የሚሉ ሁለት የተለያዩ ግን ተያያዥነት ያላቸው መፃሕፍት በአንድነት ቀርበውበታል፡፡

የመፅሐፉ የመጀመሪያ ክፍል በክርስትና ሃይማኖት አስተምሮት ላይ ተመስርቶ በብዛት ሰማያዊ ስለሆነ ነገሮች የቀረቡበት ሲሆን ፈጣሪ አምላክ፣ መላእክትና ፍጥረት የተሳሰሩበትን፣ የሚገናኙበትንና፣ የተዋቀሩበትን ሥርዓት ያመለክታል፡፡ የኢትዮጵያዊያንን እውቀትና ፍልስፍና ለመረዳት ሰማያዊ የሆነውን ምስጢርና አሰራርን ማወቅ ግድ ይላል በሚል ነው “ምስጢረ ሰማያት”ን የመፅሐፉ አካል አድርገው ያረቡት - ደራሲ ጤንነት ሰጠኝ፡፡

ኢትዮጵያዊያን በቅዱሳን መፃሕፍትና በሀይማኖታዊ አስተምሮት ላይ የተመሰረተ እውቀትና ፍልስፍና ነበራቸው ብቻ ሳይሆን፤ እውቀታቸውን በተግባር ፈትነው ዛሬ ለማመን ያስቸገሩ ወይም እንዴት ሊሰሩ እንደቻሉ ማብራሪያ የማይገኝላቸው እንደ አክሱም ሐውልት እና የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት መገንባታቸውን የሚጠቁመው መፅሐፉ፤ “ጥንት የነበሩ አባቶቻችን ታላቅ ህዝቦች እንደነበሩ በርካታ በእዚህ ዘመን የሚገኘው ትውልድ ያውቃል፡፡ ይህንን አላውቅም የሚሉ ቢኖሩ እንኳን እስከ እዚህ ዘመን ድረስ ተሸጋግሮ የመጣው ጥበባቸው ምስክር ሆኖ ይከሳቸዋል” ይላል፡፡

ደራሲው ስለ አገራዊ ሃሳብ፣ እውቀትና ፍልስፍና መኖርና አለመኖር ፍተሻ እንዲያደርጉ ያነሳሳቸው “በእኔና በአባቶቼ ጥበብ መካከል የነበረው መሰረት ስለተናጋ፣ ህሊናዬ በሁለት መንታ መንገዶች ላይ ቆሞ ይሞግተኛል፡፡ በአንድ በኩል ማፈሪያ ከሆነኝ ማንነቴ ለመሸሽ ስል ከፊቴ የቆሙትን ብርቱዎች እግር ተከትዬ መጓዝን እሻለሁ፡፡ በሌላ በኩል የአባቶችህን ቅጥር ትተህ ወዴት ትሄዳለህ? እያለ ህሊናዬ ሲሞግተኝ፣ ተመልሼ ‘የአባቶቼ የጥበብ ምንጭ ከየት ይገኛል? ወደ እዚህ ጥበብ የሚወስውን መንገድ ማን ይመራኛል?’” በሚል ላነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለማግኘት በገዳማት ዞረው፣ መፃሕፍትን ፈትሸው በምርመራቸው መጨረሻ የደረሱበትን ውጤት ነው በጥራዝ ሰንደው ያቀረቡት፡፡

ሰው የነፍስና የስጋ ባሕርያት ያሉት በመሆኑ ሁለቱ ባህሪያት ሁሌም እንደሚያታግሉት የሚያብራሩት የመፅሐፉ ደራሲ፤ ለስጋ ፍላጐቱ የተሸነፈ ክብሩን እንደሚያጣ፣ የነፍስ ባህርይው ጌታ መሆን የቻለ በታላቅነት እንደሚቆይ ያመለክታሉ፡፡ ነፍስ “ልወቅ፣ ልወቅ” የምትል ንባባዊት፣ “በነገሮች ሁሉ ጥንቁቅ ልሁን” የምትል ህያውነትና፣ “አሜን፣ አሜን” የምትል ልባዊነት የሚባሉ ሦስት ባህሪያት አሏትም ይላሉ፡፡

ከየት መጣን? ወዴትስ እንሄዳለን? የሚለውን ጥያቄ እንድንጠይቅ የሚያተጋን በነፍሳችን ውስጥ ያለው የንባባዊት ባህሪይን፣ ጠያቂነትና አለመርካት ሲያብራሩም “ንባባዊት የምንላት የነፍስ ባህርይ ካልያዘች ካልጨበጠች አታምንም፡፡ መንግስተ ሰማያት አለ ቢሏት፤ ከወዴት ይገኛል? ብላ መልስ ትጠይቃለች፡፡ በሰማያተ ሰማያት ትገኛለች ቢሏት፤ ማን አየ? ማን ደረሰበት? ብላ ደግማ መልሳ ትጠይቃለች፡፡ ስለዚህ ይህች የነፍስ ባህርይ ካላየሁ፣ ካልጨበጥኩ አላምንም የምትል ነች፡፡”

ማንነትን ለማወቅ በመጣሩ ሂደት በሰው ተፈጥሮ ውስጥ ያሉት ሦስቱ የነፍስ ባህርያትና የስጋ ፍላጐት የራሳቸው የሆነ አዎንታዊም አሉታዊም ሚና ይኖራቸዋል፡፡ ለሥጋ መሸነፍና የነፍስን ሦስቱን ባህሪያት በቅጡ አለመረዳት የጠፋ ማንነትን ለማግኘት፤ ያለ ማንነትን ለማስቀጠል እንቅፋት ሊሆን ይችላል በሚል ነው እነዚህን ትንታኔዎች ያቀረቡት፡፡

“የአባቶቼ የጥበብ ምንጩ ከየት ይገኛል? ወደ እዚህ ጥበብ የሚወስደውን መንገድ ማን ይመራኛል?” የሚል ንባባዊት ባህርይ ያሉት የነፍስ ጥያቄ የጠየቁት የመፅሐፉ አዘጋጅ፤ ወደዚህ ዘመን መሻገር ያልቻለው የቀድሞ ኢትዮጵያዊያን የሀሳብ፣ የእውቀትና የፍልስፍናቸው መሰረት የሆኑ ስድስት መሰረታዊ ነገሮችን ያስተዋውቃሉ፡፡

ቀዳሚው “ሥም” ነው፡፡ የግል፣ የቦታ፣ የአገር ሥማችንን ማሳወቅ፣ ማስጠራትና ታላቅ ማድረግ በቻልን መጠን ስማችን ብቻውን ከፊት እየቀደመ አሸናፊና ባለድል ያደርገናል፡፡ “ንጉስ ይህንን ስሩ፣ ይህንን አድርጉ ብሏል ተብሎ እሱ በሌለበት በስሙ ብቻ ሁሉም ነገር ተሰርቶ” የሚጠብቀው ቀድሞ በተገነባ እውቅና ምክንያት ነው፡፡ በተግባሩ ለነቀፌታ የሚዳረግ ሰውም ከስሙ መጉደፍ ጋር ብዙ ነገር ያጣል፡፡

ሁለተኛው “በረከት1 ሲሆን በአሁኑ ዘመን ካፒታል የሚለው ቃል በተሻለ ይገልፀዋል፡፡ “ባለፀጋ ወዳጆቹ ብዙ ናቸው” የሚለው ብሂል እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ አገር በብልፅግና ላይ መገኘት የሚችል ታዛዡ ወይም አገልጋዩ ብዙ ይሆናል፡፡

ሦስተኛው “ኃይል” ነው፡፡ በመፅሐፉ ለዚህ ቃል በተሰጠው ማብራሪያ “ሰው ከእሱ በላይ ኃያል ለሆነና ጉልበተኛ ለሆነ ወገን እራሱን አስገዝቶ ይኖራል” ይህ አባባል የመጠቀ እውቀትን (በአሁኑ ዘመን አባባል ቴክኖሎጂን) እንዲወክል የቀረበ ነው፡፡ የመፅሐፉ ደራሲ ከኢትዮጵያዊያን የፍልስፍና መሰረቶች አንዱ የሆነው “ኃይል” የጊዜና የግዝፈት ተፅእኖን መቋቋም ያስችላል ይላል፡፡ “ስለ ማረጋቸው” የተነገረላቸው ሰዎች በዚህ ኃየል የተጠቀሙ ናቸው ብቻ ብሎ አያበቃም፤ የአክሱም ሐውልትን ቀርፆ ማቆም የተቻለው ይህንኑ ኃይል (ቴክኖሎጂ) መጠቀም በመቻሉ ነው ይላል፡፡

አራተኛው “ስልጣን” ነው፡፡ ይህንንም ለዚህ ዘመን ቋንቋ ቅርብ ለማድረግ ፖለቲካ የሚለው ቃል በተሻለ ይገልፀዋል፡፡ ሁሉም የዓለም ሕዝብና አገራት በመንግሥታት እየተመሩ ቢሆንም በፖለቲካዊ አካሄዳቸው ከአገራቸው ያለፈ እውቅናና ተቀባይነት ያላቸው መንግሥታት አሉ፡፡ በጥንቱ ስልጣኔ ውስጥ ይህ ታሪክ በኢትዮጵያ ታይቶ ነበር ይላል - መፅሐፉ፡፡

የኢትዮጵያዊያን ፍልስፍና መሰረት ከሆኑት መነሻዎች አምስተኛው “ህብረት” ነው፡፡ ሃይማኖት፣ ባህል፣ ወግ… ለሚፈጥረው እሴት ሰዎች ሁሉ በጋራ የሚቀበሉት እንደ መንፈስ ያለ ረቂቅ ነገር ነው - ሕብረት፡፡

ስድስተኛውና የመጨረሻው “ጥበብ” ነው፡፡ ይህ “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው” ከሚለው ጀምሮ ተፈጥሯዊና አካባቢያዊ በሆኑ ነገሮች ላይ በመትጋት ለስኬት የሚያበቁ ብዙ ነገሮች በውስጡ ስለመያዙ… የደራሲ ጤንነት ሰጠኝ መፅሐፍ ያብራራል፡፡

ማንነታችንን ፈልገን ወደ መነሻችን እንመለስ የሚለው “ምስጢረ ሰማያት” እና “ምስጢረ ኢትዮጵያ ፍልስፍና” መፅሐፍ፤ የኢትዮጵያዊ ፍልስፍና መሰረቶች ናቸው የሚላቸው ስድስት መነሻዎች ላይ አፅንኦት ሰጥቶ ለማብራራት ከመሞከሩም ባሻገር የኢትዮጵያዊያን ስልጣኔ፣ ታሪክና መለያ አርማ ሳይቀር እንዴትና መቼ በሌሎች እንደተቀማ ሃይማኖታዊ እሳቤና አስተምሮትን በመደገፍ ምላሽ ሊሰጥ ሞክሯል፡፡

በዓለም ላይ ያሉ አገራት ለመንግሥታቸው በመለያነት የተለያዩ አራዊት፣ እንስሳትና አእዋፋትን አርማ ይጠቀማሉ፡፡ ኢትዮጵያ መለያዋ የነበረውን የንስር አሞራ አርማ ተቀምታ በአንበሳ እንድትጠቀም ታደርጋለች የሚለው መፅሃፉ፤ በአሁኑ የህዳሴው ዘመን አነጋጋሪነቱ አያጠራጥርም፡፡

 

 

 

Read 3056 times Last modified on Saturday, 01 September 2012 11:45