Saturday, 19 June 2021 17:19

በውጥረትና በጫና ውስጥ የሚካሄድ ምርጫ

Written by  ትዕግስቱ በለጠ
Rate this item
(0 votes)

ብዙ የተፈራለትና የተሰጋለትን ያህል፣ ብዙ ተስፋም የተጣለበት 6ኛው አገራዊ  ምርጫ የፊታችን ሰኞ ይካሄዳል፡፡ ይህ የምርጫ ቀን የደረሰው በምጥ ነው ቢባል አልተጋነነም፡፡ መጀመሪያ ላይ በኮቪድ ወረርሽኝ ወደ አገር ውስጥ መግባት ሳቢያ ከብዙ ውዝግብና ንትርክ በኋላ ለዓመት ያህል ገደማ ተራዘመ፡፡ እነ ህወሃትና ሌሎች አክራሪ ቡድኖች፣ በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት ኢ-ህገ መንግስታዊ ነው በሚል ዕውቅና የመንፈግና የብሔራዊ አንድነት አሊያም የሽግግር መንግስት ምስረታ ሃሳብ መሰንዘር ጀመሩ፡፡ የዘንድሮ ብሔራዊ ምርጫ በምን ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚካሄድ አንዱ ማሳያው በሁለት ዙር መካሄዱ ነው፡፡ የፊታችን ሰኞ ሰኔ 14 እና በመጪው ጳጉሜ 1 ቀን 2013 ዓ.ም፡፡ ምርጫው በሁለት ዙር የሚካሄደው ለቅንጦት አይደለም፡፡ በፀጥታ ችግሮች፣ በሎጀስቲክ አለመሟላት በምርጫው ህትመት ጉድለት ሳቢያ ነው - በአንድ ጊዜ ለማካሄድ ያልተቻለው፡፡  
የዘንድሮ ምርጫ በየአካባቢው ብዙ ሺ ዜጎች በግጭትና በጥቃት ሳቢያ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለውና በየቦታው ተበትነው ባሉበት አገራዊ ሁኔታ ውስጥ  የሚከናወን ነው፡፡ ከታላቁ የህዳሴ ግድባችን ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ጋር በተያያዘ ግብጽና ሱዳን “የጎን ውጋት” በሆኑብን ፈታኝ ወቅት የሚደረግም  ምርጫ ነው፡፡ የድሮዋ ወዳጃችን ሱዳን  በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በህግ ማስከበር ዘመቻ መወጠራችንን አይታ፣ መሬታችንን በድፍረት ወርራ በያዘችበት ወቅት ላይ የሚካሄድም ነው-የዘንድሮ ምርጫ፡፡
ይሄ ብቻ ግን አይደለም፡፡  በሰሜናዊ የአገራችን ክፍል የተካሄደውን ጦርነት ተከተሎ፣ በተከሰቱ ሰብአዊ ቀውሶች ሰበብ፣ በዓለም አቀፍ  ጫናና በማዕቀብ ማስፈራሪያ ተወጥረን በምንገኝበት እልህ አስጨራሽ ሁኔታ ውስጥ የሚካሄድም ምርጫ ነው፡፡ እነ አሜሪካን የመሣሰሉ ሃያላን አገራት 6ኛው አገራዊ ምርጫው ዓለማቀፍ መስፈርቶችን አያሟላም በሚል ምርጫውን ዓለማቀፍ ተዓማኒነትና ተቀባይነት ለማሳጣት በትጋት በሚታትሩበት ወቅት የሚደረግ ምርጫም ነው፡፡  
 እውነት መናገር፣ ከዚህ ቀደም በመሰል ውጥረቶችና ጫናዎች ውስጥ የተካሄደ ምርጫ ስለመኖሩ አላውቅም፡፡ አዋቂዎችም ሲናገሩ አልሰማሁም፡፡ እንኳን በኢትዮጵያ በሌላም አገር መሰል ፈተናና ውጣ ውረዶች የበዙበት ምርጫ ተካሂዶ እንደሆነ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ በኛ አገር ግን እነሆ  ነገ በስቲያ ይካሄዳል፡፡ የምርጫው ሂደትም ቢሆን ተመሳሳይ ነው፡፡  በጦርነትና ግጭት ውስጥ ነው ያለፈው፡፡ እንዲያም ሆኖ ብዙዎች እንደ መሰከሩት ለክፉ የሚሰጥ አይደለም ሂደቱ፡፡ እርግጥ ነው እንደ አዲስ የተዋቀረው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የአቅም ውስንነቶች እንዳሉበት ይታወቃል፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ይሄንኑ ይናገራሉ፡፡ እርግጥ ነው ፓርቲዎች ለቦርዱ አቅርበው በቂ ምላሽና መፍትሄ ያላገኙ ችግሮች ሞልተዋል፡፡ እርግጥ ነው የምርጫው ቀንና  የመራጮች ምዝገባ የጊዜ ሰሌዳን  በተደጋጋሚ ቀይሯል ተራዝሟልም፡፡ እንዲያም ሆኖ  ግን ቦርዱ ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ ሁሉን ነገር ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር እየተወያየና እየተመካከረ ሲሰራና ሲወስን መቆየቱን መካድ አይቻልም፡፡ ለዚህም ነው ፓርቲዎች ቦርዱን አምርረው ሲወቅሱትና ሲከሱት የማይሰሙት፡፡ ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ያወድሱታል ያሞግሱታል ማለት ግን አይደለም፡፡ ቢያንስ ያምኑታል፡፡ በገለልተኝነቱና በግልፀኝነቱ ደግሞ ጥርጣሬ የላቸውም፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎችም ምስክርነታቸውን ሲሰጡም ተደምጠዋል፡፡
ባለፉት አምስት አገራዊ ምርጫዎች፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን በፍ/ቤት መክሰስ የሚታሰብም የሚታለምም አልነበረም፡፡ ቦርዱን መክሰስ ራሱን ኢህአዴግ መራሹን መንግስት እንደ መክሰስ የሚቆጠር ነበርና፡፡ በዘንድሮ ምርጫ ግን በወ/ሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ የሚመራው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተደጋጋሚ በተፎካካሪ ፓርቲዎች በፍ/ቤት ተከሰሶ ውሳኔዎቹን እንዲለውጥ ተገልጿል፡፡ ለአብነት ያህል “የባልደራስ” ክስ ይጠቀሳል፡፡ በርግጥ ይሄ ፍ/ቤቶቻችን የቱን ያህል ነፃና ገለልተኛ እየሆኑ እንደመጡም ማሳያ ጭምር  ነው፡፡
አብዛኞቹ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በዘንድሮ ምርጫ ላይ ተስፋና እምነት ያሳደሩት  የጠ/ሚኒስትሩን “በምርጫው ከተሸነፍን ለደቂቃ ማሰብ ሳያስፈልገን ሥልጣናችንን ለአሸናፊው ፓርቲ እናስረክባለን” የሚል ቃል ተማምነው ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአዲስ መልክ በገለልተኝነት እንዲዋቀር በመደረጉና የቀድሞ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የነበሩት ወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳ ቦርዱን እንዲመሩት በመሾማቸው ነው፡፡አሁን ቢያንስ  ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከመንግስት ጋር ተመሳጥሮ ኮሮጆ አይገለበጥም ብለው የሚያምኑ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተፈጥረዋል፡፡ ሙሉ በሙሉ አሸንፈው መንግስት ባይመሰርቱ እንኳ በፓርላማ ውስጥ ትርጉም ያለው መቀመጫ ሊያሸንፉ እንደሚችሉና መቶ በመቶ በገዢው ፓርቲ ተይዞ የከረመውን የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ድባብ ለመለወጥ አልመው በውድድሩ የሚሳተፉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡
 ምርጫው በአንጻራዊነት ነፃ ፍትሃዊና ሰላማዊ ሆኖ እስከተጠናቀቀ ድረስ የእኛ በምርጫው ማሸነፍና አለማሸነፍ ዋና ጉዳይ አይደለም፤ የዲሞክራሲ መሰረት መጣሉ ነው ለዘለቄታው የሚጠቅመው፤ በሚል ዓላማና ግብ  ከልባቸውየሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መኖራቸውም ትልቅ ተስፋ ያሳድራል- ጥቂት ቢሆኑም፡፡ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢዋ ወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳ ሰሞኑን በምርጫው ለሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ የምስጋና ቃላቸውን በፌስ ቡክ ገፃቸው አስተላልፈዋል፡፡ የምስጋናቸው ምክንያት ደግሞ  ፓርቲዎቹ እንደ ቀድሞ ጊዜ በምርጫ ክርክርና ቅስቀሳ ውቅት እርስ በርስ ጣት ሳይቀሳሰሩና “ዓይንህ ላፈር” ሳይባባሉ፣ ሂደቱን በሰለጠነ መንገድ ማጠናቀቃቸው ነው፡፡ ምስጋናው ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ድንቅ የለውጥ ጀማሮ ነው፡፡ በሌላ በኩል ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በጅማ ባካሄዱት የምርጫ ቅስቀሳ ማጠቃለያ ላይ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከብልጽግና ያልተናነሰ መልካም ዕድል እንዲገጥማቸው ምኞታቸውን መግለፃቸው የሥልጡን ፖለቲካ ምልክት ነው፡፡ የመተማመን ስሜት ይፈጥራል፡፡ ተፎካካሪዎችም ተመሳሳይ መልካም ምኞት ለገዢው ፓርቲ ቢያስተላልፉ በግሌ እወድ ነበር፡፡ ደግሞ ሁሉም ነገር ዛሬ ካልሆነ አይባልም፡፡
እንግዲህ በምርጫ ቦርድ የተሰየመው አራቱ የጥሞና ቀናት (ወቅት) ነገ ይጠናቀቃል፡፡ ሰኞ ምርጫው ይካሄዳል፡፡ ምርጫው በሰላም ተጠናቀቀ የሚባለው የምርጫ ውጤት በምርጫ ቦርድ ከተገለፀ በኋላና ፓርቲዎች በፀጋ ተቀብለውት ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ሲካሄድ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በውጤቱ ዙሪያ ችግሮችና አለመግባባቶች ቢኖሩም እንኳን በውይይትና በህጋዊ መንገድ ለመፍታት ይቻላል፡፡ ፍ/ቤቶች ለዚሁ ጉዳይ ዝግጁ መሆናቸው ተገልጿል፡፡ በዚሁ መልኩ ከቀጠልን በተደጋጋሚ እንደተገለፀው ምርጫው በእርግጥም በሰላም ይጠናቀቃል፡ እንደተባለውም ኢትዮጵያ ታሸንፋለች፡፡

Read 593 times