Saturday, 19 June 2021 17:09

“ልባችሁን አዳምጡ...”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

 (ምስኪኑ ሀበሻ በምርጫው ጉዳይ አንድዬን ያማከረው)
                         
          እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ… እንደምንም፣ እንደምንም እዛች ቀን ላይ ተደረሰ አይደል! እያሰጉንም፣ እየሰጋንም፣ “ተከትሎት ምን ይመጣ ይሆን!” እያልንም፣ “ሁሉም ለበጎ ነው፣” እያልንም ይኸው እዚህ ተደርሷል፡፡ እንግዲህ የመልካም ነገሮች ዘመን፣ የእርጋታ ዘመን፣ የእፎይ መባያ ዘመን  መጀመሪያ ያድርግልንማ!
ምስኪን ሀበሻ፡– አንድዬ! አንድዬ!...ኸረ አንድዬ!
አንድዬ፡– የለሁም!
ምስኪን ሀበሻ፡– አንድዬ...“የለሁም” ብለህ ከተናገርክ እኮ አለህ ማለት ነው፡፡
አንድዬ፡– መኖሬን እኔ ነኝ የማውቀው አንተ!?ምስኪን ሀበሻ፡– አንድዬ፣ ይኸው እያወራሁህ አይደል እንዴ!
አንድዬ፡– እሺ አለሁ፡፡ ምን ላደርግ... ከእናንተ ጋር መከራከሩ ዋጋ ስሌለው.. ምን ነበር የምትሉት…አዎ እጄን ሰጥቻለሁ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡– ኸረ አንድዬ...
አንድዬ፡– ዋናው ነገር ክርክሩን ተወኝና እንዴት ከረምክ፣ ምስኪኑ?
ምስኪን ሀበሻ፡– አለሁ አንድዬ፣ መቼም የእኔም መኖር ከተባለና ቁጥር የሚገባ ከሆነ አለሁ ነው እንጂ ሌላ ምን ይባላል!
አንድዬ፡– ስለመኖርህ እርግጠኛ ነህ?
ምስኪን ሀበሻ፡– እንዴት አንድዬ፣ አልገባኝም፡፡ 
አንድዬ፡– እንዴት አንደሆነ እኔም አላውቀው፡፡ አለህም ልልህ፣ የለህምም ልልህ ቢቸግረኝ ነው፡፡ ለመኖርህ ማረጋገጫህ ምንድነው?
ምስኪን ሀበሻ፡– አንድዬ፣ ግራ አጋባኸኝ እኮ! ብኖር አይደል እንዴ አንተ ፊት የቆምኩት…
አንድዬ፡– አዎ፣ አካልህ ፊት ለፊቴ ቆሟል፡፡ እንደዛ ማለት ግን አንተ ነህ ማለት አይደለም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡– አንድዬ!
አንድዬ፡– ቢቸግረኝ እኮ ነው፡፡ እዚህ ሆኜ ቁልቁል ሳያችሁ፣ የላችሁም እንዳልል በሆነ ባልሆነው አንዳችሁ እንደ አምስት ሰው እየጮሃችሁ ስትነታረኩ እሰማለሁ፡፡ አላችሁ እንዳልል አእምሯችሁን ለተፈጠረበት ሥራ ስትጠቀሙበት ማየት ብጓጓም አልሆነልኝም፡፡ እና ካላሰባችሁ፣ ነገራችሁ ሁሉ የደመ ነፍስ ከሆነ ምኑን አላችሁት! አስረዳኛ ምስኪኑ...
ምስኪን ሀበሻ፡– ምኑን ላስረዳህ አንድዬ፣ ልክ ልካችንን እየነገርከን ምኑን ላስረዳህ፡፡
አንድዬ፡– አየህ አይደል! አየህልኝ አይደል! አሁን ልክ፣ ልክ መናገርን ምን አመጣው! ያልኩትን በአእምሮህ ሳይሆን በጆሮህ ብቻ ስላዳመጥክ ነው እንዲህ የመለስክልኝ፡፡ እስቲ ንገረኝ፣ ጆሯችሁና አእምሯችሁ ጠበኞች ናቸው እንዴ!?
ምስኪን ሀበሻ፡– እንዴት፣ አንድዬ?
አንድዬ፡– ማለቴ ጆሮ የሚያስተላልፈውን አእምሮ በሮቹን ከርችሞ አላስገባም የሚለው ለምንድነው?
ምስኪን ሀበሻ፡– ምኑን አወቄ፣ አንድዬ!
አንድዬ፡– በነገራችን ላይ እኔ ዘንድ በመጣህ ቁጥር አንድ ጊዜም ተቀመጥ ብዬህ አላውቅም፣ አይደል!
ምስኪን ሀበሻ፡– አንተ ፊት ቀርቤ እንዴት ብዬ ነው የምቀመጠው!
አንድዬ፡– ምናለበት! እኔ መቀመጥህ ደስ ካለኝ ተመችቶህ ብትቀመጥ ምን ችግር አለው!
ምስኪን ሀበሻ፡– አይ አንድዬ፣ እንደዚህ አይነት ነገር መቼም የሚሆን አይደለም፡፡ አንተ ተቀመጥ ብትለኝም እሺ ብዬ አልቀመጥም፡፡
አንድዬ፡– ባዝህስ! ተቀመጥ ብዬ ትእዛዝ ብሰጥህስ?
አንድዬ፡– አንድዬ፣ አስጨነቅኸኝ እኮ!
አንድዬ፡– ለነገሩ እኔም ተቀመጥ የሚለው ቃል ለምን ከአፌ እንዳልወጣ አሁን ትዝ አለኝ መሰለኝ...
ምስኪን ሀበሻ፡– አንድዬ፣ ለምንድነው?
አንድዬ፡– እናንተ የእቁብ ጸሀፊነትም ቢሆን ምንም ወንበር ላይ አንዴ ተመቻችታችሁ ከተቀመጣችሁ፣ አትለቁም ብዬ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡– ይህን ያህል ታዝበኸናል?
አንድዬ፡– እየው አንግዲህ! አዎ፣ ታዝቤያችኋለሁ ብል ሄደህ ትነግርና ምን ሀጢአት ብንሠራ ነው እያላችሁ ልታማርሩኝ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡– እ  አንድዬ፣ እኛ አንተን መለመናችን ነው እንጂ ማማረራችን አይደለም፡፡
አንድዬ፡– አየህ ዳር፣ ዳሯን እየዞርክ ነው፡፡ ከእናንተ ጋር ክርከር መጀመር…ተወው ብቻ፡፡ ለነገሩ ዛሬ ምን እግር ጣለህ?
ምስኪን ሀበሻ፡– ምን መሰለህ አንድዬ፣ ደስ ሊለኝ ይገባኝ እንደሁ፣ ሊከፋኝ ይገባኝ እንደሁ፣ ሊያስጨንቀኝ ይገባኝ እንደሁ፣ የራሱ ጉዳይ ብዬ ልተወው ይገባኝ እንደሁ ግራ የገባ ነገር ገጥሞኝ ነው፡፡
አንድዬ፡– ምን ያህል አስቸጋሪ ነገር ቢሆን ነው!
ምስኪን ሀበሻ፡– ከነገ ወዲያ ምርጫ ሊካሄድ እንደሆነ ሰምተሀል አይደል!፡፡
አንድዬ፡– ምነው፣ እኛ ሠላሳ ዓመት የመሩትን የእድር ሰብሳቢ ልታነሷቸው ነው እንዴ?
ምስኪን ሀበሻ፡– አንድዬ…
አንድዬ፡– ስቀልድ ነው፡፡ እኔ ዘንድ በመጣህ ቁጥር ፊትህን ሸብሽበህ ነው፡፡ ምናለ አንዳንዴ ተሳስተህ እንኳን ትንሽ ፈገግ ብትል!
ምስኪን ሀበሻ፡– እንዴት ብዬ አንድዬ! ምን ፈገግ የሚያሰኝ ነገር አለና ፈገግ ልበል!
አንድዬ፡– ስማኝማ፤ በውስጥ ጉዳያችን ምን ጥልቅ አደረገህ እንዳትለኝ እንጂ ምንም ፈገግ የሚያሰኝ ነገር የምታጡት በቃ ሁሉም ነገር መጥፎ ነው ብላችሁ ስለደመደማችሁ አይመስልህም!
ምስኪን ሀበሻ፡– እሱስ ልክ ነህ አንድዬ፣..
አንድዬ፡– ይልቅ ግራ አጋባኝ ስላልከው ምርጫ ..ምኑ ነው ይሄን ያህል ያስጨነቀህ?
ምስኪን ሀበሻ፡– አንድዬ፣  እኔ እንጃ፡፡ እንደው ዘና ብዬ በተስፋ ተሞልቼ ላስበው ስል የሆነ መጥቶ እንዲህ... ብቻ አንዴት ልበልህ አንድዬ፣ እንዲህ መጥቶ ይልብኝና ሁሉ ነገር ጨለማ ይሆንብኛል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ የሆነች ትንሽዬ ብርሀን ያየሁ ይመስለኛል፡፡ ብቻ...
አንድዬ፡– እኮ... ጨለማም፣ ብርሀንም ማድረጉ የእናንተ ፈንታ አይመስልህም!
ምስኪን ሀበሻ፡– እሱማ ነው፣ ግን ምን መሰለህ አንድዬ፣ ሁሉም ከእኛ በላይ ላሳር ባይ ሆነና ማንን ከማን መለየቱ ግራ ግብት የሚል ነው፡፡
አንድዬ፡– እንግዲሀ ረጋ ብለህ አስበህ ይሠሩልኛል የምትላቸውን መምረጥ ነዋ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡– እሱ ነው እኮ ችግሩ አንድዬ፣ አይደለም በሀገር በእድርና በእቁብ ይሠሩልናል ያልናቸው እየሠሩብን ነው ግራ የገባን፡፡
አንድዬ፡– እንግዲህ ሌላ አማራጭ ከሌለ መሞከሩ ነው እንጂ ምን ይደረጋል፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡– አንድዬ፣ እንደው ይሄ አጭበርባሪውን፣ ክፉውን ምናምኑን...ይሄ ሎሚ መስሎ የሚቀርበውን እምቧይ ሁሉ ከስልጣን  አርቅልን፡፡
አንድዬ፡– ጭራሽ ወደ እኔ አመጣኸውና አረፍከው! እዛው ተቻቻሉ እንጂ በትንሹ በትልቁ እኔ ምን ያገባኛል!
ምስኪን ሀበሻ፡– ቢሆንም አንድዬ...
አንድዬ፡– ደግሞስ እኔ ራሴ፣ ምን ነበር ሁን ያልከው....ሎሚ እየመሰላችሁኝ እምቧይ እየሆናችሁብኝ ተቸግሬያለሁ፤ ሌላ ጦስ ውስጥ ልትከተኝ ነው!
ምስኪን ሀበሻ፡– አንድዬ፣ አንተ እሺ ካላልከን ሌላ ወደ ማን ልንዞር ነው!
አንድዬ፡– አጭር መልስ ልስጥህ...ወደ ልባችሁ ዙሩ፡፡ ይኸው ነው፡፡ ደግሞ እኔ ጣልቃ ብገባ ሌላ ችግር ይመጣል፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡– ምን አይነት ችግር፣ አንድዬ?
አንድዬ፡– ምርጫው ተጭበርብሯል ይባላላ!
ምስኪን ሀበሻ፡– አንድዬ...
አንድዬ፡– ይልቅ አሁን ያልኩህን ስማ፡፡ እህ ብላችሁ ልባችሁን አዳምጡ...መልሱን ሁሉ እዛው ታገኙታላችሁ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡– እንሞክራለን፣ አንድዬ...
አንድዬ፡– ደግሞም... እስቲ ለሁሉ ነገር ረጋ በሉ፡፡ እኔም የምትሆኑትን አያለሁ፡፡ በል ደህና ግባ ምስኪኑ!
ምስኪን ሀበሻ፡– አሜን አንድዬ፣ አሜን!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1180 times