Saturday, 19 June 2021 17:04

የኮሮና ቫይረስ ከክትባቱ በበለጠ ፍጥነት መሰራጨቱን ቀጥሏል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ወረርሽኙን ለማስቆም 70 በመቶ የአለም ህዝብ መከተብ ይኖርበታል የኮሮና ተጠቂዎች ቁጥር ለ7 ተከታታይ ሳምንታት መቀነስ አሳይቷል

            በመላው አለም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከክትባቱ በበለጠ ፍጥነት በመሰራጨት ላይ እንደሚገኝ የገለጸው የአለም የጤና ድርጅት፣ ያም ሆኖ ግን በአለማቀፍ ደረጃ አዳዲስ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር ባለፉት 7 ተከታታይ ሳምንታት መቀነስ  ማሳየቱ እንደ መልካም ዜና ሊወሰድ እንደሚችል አስታውቋል፡፡
በአለማችን ወረርሽኙ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ የአዳዲስ ተጠቂዎች ቁጥር ለረጅም ጊዜ በተከታታይነት የቀነሰው ባለፉት 7 ሳምንታት ነበር ያሉት የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ ይህ መልካም ዜና ቢሆንም የሟቾች ቁጥር ግን በተጠቂዎች ቁጥር መጠን ሊቀንስ አለመቻሉንና ቫይረሱ በተለይም አፍሪካን በመሳሰሉ እዚህ ግባ የማይባል የክትባትና የህክምና አቅርቦት የሌለባቸው የአለማችን ክፍሎች በፍጥነት በመሰራጨትና በርካቶችን በመግደል ላይ እንደሚገኝ በሳምንቱ መጀመሪያ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡
በቅርቡ የወጣ አንድ ጥናት፣ በጽኑ ከታመሙ የቫይረሱ ተጠቂዎች ብዛት ያላቸው ሰዎች ለሞት የሚዳረጉባት ቀዳሚዋ የአለማችን ክፍል አፍሪካ መሆኗን ማረጋገጡንም ዳይሬክተሩ አክለው ገልጸዋል፡፡
የቡድን ሰባት አገራት ከሰሞኑ ባካሄዱት ስብሰባ፣ መካከለኛና አነስተኛ ገቢ ላላቸው አገራት 870 ሚሊዮን የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን ለመለገስ መስማማታቸውን ያደነቁት ዳይሬክተሩ፤ ወረርሽኙን ለማስቆም እስከ መጪው አመት ከአጠቃላዩ የአለም ህዝብ ቢያንስ 70 በመቶውን መከተብ እንደሚገባና ለዚህም 11 ቢሊዮን ክትባቶች እንደሚያስፈልጉ አመልክተዋል፡፡
በእንግሊዝ ሳምንቱን አመታዊ ጉባኤያቸውን ያካሄዱት የቡድን 7 አገራት፣ ለደሃ ሀገራት ለመስጠት ቃል የገቡት 1 ቢሊዮን የሚጠጋ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ለአገራቱ በቀጥታ ወይም በአለም የጤና ድርጅት የክትባት ጥምረት ኮቫክስ በኩል እንዲደርስ ይደረጋል መባሉንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡በሌላ የኮሮና ቫይረስ ዜናም፣ በአሜሪካ በቫይረሱ ሳቢያ ለሞት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር ባለፈው ማክሰኞ ከ600 ሺህ ማለፉን የዘገበው የአሜሪካ ድምጽ፣ የተጠቂዎች ቁጥር በአንጻሩ ከ33.5 ሚሊዮን ማለፉ መነገሩን ገልጧል፡፡


Read 2980 times