Friday, 18 June 2021 00:00

ጣሊያናዊው “ከአየርና ከመንፈስ ሰራሁት” ያለው የምናብ ሃውልት 18 ሺህ ዶላር ተሸጠ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ጣሊያናዊው አርቲስት ሳልቫቶሬ ጋራኡ ከአየርና ከመንፈስ አዋህጄ ሰራሁት ያለውና ‹እኔ ነኝ› የሚል ስያሜ የሰጠው በአይን የማይታይ ምናባዊ ሃውልት 18 ሺህ ዶላር መሸጡን ዘ ኒውዮርክ ፖስት ባወጣው አስገራሚ ዜና አስነብቧል፡፡
ግዝፍ ነስቶ የቆመ ሳይሆን ከዚህ በፊት ከተለመደው በተለየ መልኩ ምናባዊ የሆነውን አነጋጋሪ ሃውልት በተመለከተ አርቲስቱ በሰጠው ማብራሪ፤ ‹ልታዩት ባትችሉም፤ ሃውልቱ ግን አለ› ሲል መናገሩን የጠቆመው ዘገባው፣ ሃውልቱ ጣሊያን ውስጥ በሚገኝ አንድ አደባባይ በተከለለ 5 ጫማ በ5 ጫማ ስፋት ያለው ቦታ ላይ እንደሚገኝ መናገሩንም ገልጧል፡፡
አርትራይት በተባለው የጣሊያን የስነጥበብ ስራዎች አጫራች ኩባንያ አማካይነት ለጨረታ የቀረበው ይህ አነጋጋሪ ሃውልት፣ ከከፍተኛ ፉክክር በኋላ በ18 ሺህ 300 ዶላር መሸጡን የጠቆመው ዘገባው፣ አሸናፊው ግለሰብ በአይን የማይታየው ምናባዊ ሃውልት ባለቤት መሆኑን የሚያረጋግጥ የምስክር ወረቀት እንደተሰጠው መነገሩንም ገልጧል፡፡
ጣሊያናዊው አርቲስት በዚህ አመት ብቻ የማይታይ ሃውልት ሲሰራ ይህ ሶስተኛ ጊዜው እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፣ ባለፈው የካቲት ወር በሚላን ከተማ መሰል ምናባዊ ሃውልት አቆምኩ በማለት ህዝቡን አደናግሮ እንደነበርም አስታውሷል፡፡
‹ባዶ ቦታ አጥሮ፣ የምን ሃውልት እያሉ ማደናገር ነው› በማለት ለተቹት ሰዎች፤ ‹ሃውልቱን ለማየት የሚችለው፣ ምናበ ሰፊ የሆነ ሰው ብቻ ነው› ሲል አስገራሚ ምላሹን የሰጠው ጣሊያናዊው አርቲስት፣ ባለፈው ሳምንትም ከኒውዮርኩ የአክሲዮን ገበያ አቅራቢያ አንድ ነጭ ክብ ቦታ ከልሎ ‹አፍሮዳይት ፒያንጄ› የተሰኘ ሃውልቴን ጎብኙልኝ ሲል ብዙዎችን ማደናገሩን አውስቷል፡፡



Read 3665 times