Friday, 18 June 2021 00:00

በአለማችን 160 ሚ. ህጻናት የጉልበት ብዝበዛ ሰለባዎች ናቸው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በመላው አለም ከ5 እስከ 11 አመት ዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ህጻናት መካከል 10 በመቶ የሚሆኑት ወይም 160 ሚሊዮን ያህል ህጻናት ለእድሜያቸው በማይመጥን ስራ የጉልበት ብዝበዛ እየደረሰባቸው እንደሚገኙ ከሰሞኑ የወጣ አንድ አለማቀፍ ሪፖርት አስታውቋል፡፡
አለማቀፉ የህጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ እና በተመድ የሰራተኞች ድርጅት ከሰሞኑ ባወጡት ሪፖርት እንዳሉት፣ እስከ መጪው የፈረንጆች አመት 2022 መጨረሻ ድረስ ተጨማሪ 9 ሚሊዮን ያህል ህጻናት የጉልበት ብዝበዛ ሰለቦች ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ህጻናት በስፋት ለጉልበት ብዝበዛ ከሚዳረጉባቸው የስራ ዘርፎች መካከል የግብርናው ዘርፍ ቀዳሚነቱን እንደሚይዝ የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ከአጠቃላዩ የጉልበት ብዝበዛ ሰለቦች 70 በመቶው ወይም 112 ሚሊዮን ያህል የአለማችን ህጻናት በዘርፉ ተሰማርተው ለጉልበት ብዝበዛ መዳረጋቸውንና 20 በመቶው በአገልግሎት፣ 10 በመቶው ደግሞ በኢንዱስትሪው ዘርፍ እንደተሰማሩም ገልጧል፡፡
ህጻናት በብዛት ለከባድ የጉልበት ስራ ከተዳረጉባቸው የአለማችን አካባቢዎች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ከሰሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገራት መሆናቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ እድሜያቸው ከ5 እስከ 17 አመት ከሚሆናቸው የአገራቱ ህጻናት መካከል ሩብ ያህሉ የድርጊቱ ሰለቦች መሆናቸውንም አክሎ አስረድቷል፡፡
የጉልበት ብዝበዛ ሰለቦች የሆኑ ህጻናት ቁጥር ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ለመጀመሪያ ጊዜ ጭማሪ ያሳየው ባለፈው የፈረንጆች አመት 2020 መሆኑን ያስታወሰው ሪፖርቱ፣ ለዚህም በምክንያትነት ከተጠቀሱት መካከል የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንደሚገኝበትና ተጨማሪ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህጻናት ለአደጋው ተጋላጭ መሆናቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡


Read 817 times