Tuesday, 15 June 2021 18:59

አለማቀፉ አጠቃላይ ሃብት ግማሽ ኳድሪሊዮን ዶላር ደርሷል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 አሜሪካውያን ቢሊየነሮች ለአመታት ምንም ግብር አለመክፈላቸው ተጋለጠ

            የአለማችን አጠቃላይ የተጣራ ሃብት 431 ትሪሊዮን ዶላር መድረሱን ወይም ወደ ግማሽ ኳድሪሊዮን ዶላር መጠጋቱን ፎርብስ መጽሄት ከትናንት በስቲያ ባወጣው ዘገባ አስነብቧል፡፡
ቦስተን ኮንሰልቲንግ ግሩፕ የተባለ ተቋም ያወጣውን አለማቀፍ የሃብት ሁኔታ ሪፖርት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ከአለማችን 431 ትሪሊዮን ዶላር ሃብት ውስጥ ከሩብ በላይ የሚሆነው ወይም 126 ትሪሊዮን የሚገመተው ሃብት የተያዘው ከ1 ሚሊዮን ዶላር በላይ የተጣራ ሃብት ባፈሩ ባለ ከፍተኛ ሃብት ሚሊየነሮች ነው፡፡
የአለማችን አጠቃላይ የተጣራ ሃብት በመጪዎቹ አራት አመታት ከ500 ትሪሊዮን ዶላር ወይም ከግማሽ ኳድሪሊዮን ያልፋል ተብሎ እንደሚገመት የጠቆመው ሪፖርቱ፣ በአለማችን ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ የተጣራ ሃብት ያፈሩ ባለ እጅግ ከፍተኛ ሃብት ሚሊየነሮች ቁጥር 60 ሺህ መድረሱንና እነዚህ ባለጸጎች በድምሩ 22 ትሪሊዮን ዶላር ሃብት መያዛቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ የቢዝነስ ዘገባ ደግሞ፣ ጄፍ ቤዞስ፣ ኤለን መስክና ዋረን ቡፌትን ጨምሮ በርካታ ስመጥር የአለማችን ቢሊየነሮች፣ ለረጅም አመታት ምንም አይነት የገቢ ግብር አለመክፈላቸውን የሚያረጋግጥ አንድ መረጃ ከሰሞኑ ይፋ መደረጉን ሲኤንቢሲ ኒውስ ዘግቧል፡፡
ፕሮፐብሊካ የተባለው ድረገጽ ከሰሞኑ ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ የአማዞኑ መስራች ጄፍ ቤዞስ እ.ኤ.አ በ2007 እና በ2011 አምስት ሳንቲም ግብር ለመንግስት ያልከፈሉ ሲሆን፣ የቴስላ ኩባንያ ባለቤት ቢሊየነሩ ኤለን መስክ በበኩላቸው በ2018 ምንም አይነት ግብር አልከፈሉም፡፡
የአሜሪካ 25 ታላላቅ ባለሃብቶች እ.ኤ.አ ከ2014 እስከ 2018 በነበሩት አመታት አጠቃላይ ሃብታቸው በ401 ቢሊዮን ዶላር ጭማሪ ቢያሳይም ባለሃብቶቹ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በገቢ ግብር መልክ የከፈሉት ግን 13.6 ቢሊዮን ዶላር ብቻ እንደነበር መረጃው አጋልጧል፡፡


Read 1197 times